በሠላም ዓለሙ
February 11, 2020 (Ezega.com) -- ኮንትሮባንድ በገቢና በወጪ ምርቶች ላይ በመሰራፋት ኢትዮጵያን በዙሪያ መላስ እየጎዳት ነው፡፡ የወጪ ንግዷ ማሽቆልቆል ከጀመረ ዓመታት ያስቆጠረችው ኢትዮጵያ፤ ለዚህም ፊት ተጠቃሽ ምክንያት የኮንትሮባንድ ንግድ ነው፡፡ ለአብነት የ2011 በጀት ዓመት የግምሽ ዓመት አፈፃፀም ብንመለከት፤ የወጪ ንግድ ከ2010 ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ10 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስድስት ወራት አፈፃፀሙን ለህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት ሲያቀርብ አስታውቋል፡፡ ሀገሪቱ በ2010 በጀት ዓመት ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ከወጪ ንግዷ ብታገኝም፤ ይህ አሀዝ ታዲያ ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ የመጣውን የወጪ ንግድ አሳሳቢነትና አስጊነት አመላካች ነው፡፡
ለወጪ ንግድ ማሽቆልቆል ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ውስጥ ቀዳሚው በተለይም የግብርና ምርቶችን በጥራትና በስፋት ለገበያ አለማቅረብ ይሁን እንጂ፤ የኮንትሮባንድ ንግድ ለንግዱ ማነቆ የሆነ ቀንደኛና ሁለተኛው ምክንያት ሆኖ ይነገራል፡፡ ከሀገሪቱ የወጪ ምርቶች የኮንትሮባንድ ንግድ የማይነካካው ምርት አለመኖሩን የሚያምነው መንግስት፤ ከቁም እንስሳት ጀምሮ ለሀገሪቱ የወጪ ንግድ ትልቅ ድርሻ እስካላቸው ቡና፣ ወርቅና የቅባት እህሎች ድረስ የህገ ወጥ ንግዱ ሰለባ ስለመሆኑ ብሄራዊ ባንክ በተደጋጋሚ የሚያነሳው እንቅፋት ነው፡፡
የብሄራዊ ባንክ ዋና ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ የኮንትሮባንድ ንግድ ምን ያህል ህጋዊና ስርዓት ውስጥ ገብቷል የሚባለውን ንግድ እንደሚጎዳ ለማሳየት የአምስት ዓመታትን የወርቅ ንግድ በዋቢነት አንስተዋል፡፡ ዋና አዣዡ እንደሚሉት ኢትዮጵያ በ2006 ዓ.ም ከወርቅ ንግድ 430 ሚሊዮን ዶላር ታገኝ ነበር፡፡ ሆኖም ከአምስት ዓመታት በኋላ ሀገሪቱ በ2010 ዓ.ም የኮንትሮባንድ ንግድ በመጧጧፍ ምክንያት ከ90 በመቶ በላይ የወርቅ ገቢዋ እንዲያሽቆለቁል አድርጎ 32 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች የኮንትሮባንድ ንግድ ሁለት መልክ ያለው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከሀገር ከሚወጡ ምርቶ የሚገኘው ገንዘብ መልሶ ወደ ሀገር እንደሚገባ የሚጠቅሱት ባለሞያዎቹ፤ ይህም የኮንትሮባንድ ንግድ በሁለት ሠይፍ የተሳለ በመሆኑ ከባድ ነው ይላሉ፡፡ የኮንትሮባንድ ንግድ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ ነው፡፡ ህጋዊ የንግድ እንቅስቀሴዎችን በማከናወን መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ያህል ገቢ እንዳያገኝ በማድረጉ ረገድም ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም የሚሉት የዘርፉ ባለሞያወዎች፤ ፍትሀዊ ንግድ ውድድርንም ያቀጭጫል ይላሉ፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድ ሀገሬውን ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ የጠባሳው መጠንም እጁን ከምጣኔ ሀብቱ አሻግሮ በፖለቲካና በማህበራዊ ጉዳየች ስለመስደዱም ይነገራል፡፡ ተንታኞች ለድንበር ንግድ ተብሎ የተከፈተው ስርዓት ምጣኔ ሀብቱንና ግብር ከፋዩን ህጋዊ ነጋዴ የውድድር ሜዳውን ለየቅል አድርጎ እየጎዳ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ጠረፎች ወደ ውጭ የሚወጡ ምርቶችና በርካሽ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የኮንትሮባንድ ምርቶችና ሸቀጦች ታክስ ቢከፈልባቸው ኖሮ ተብሎ ሒሳቡ ቢሰላ፤ ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ ስለመሆኑ መገንዘብ ያስችላል፡፡
በህገ ወጥ ከሀገር ከሚወጡ ምርቶች የሚሰበሰብ ገንዘብ መልሶ ለመዋዕለ ነዋይ ፍሰት በሀገሪቱ ጥቅም ላይ አለመዋል ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡ በተለይ ለጦር መሳሪያ ግዥና ለጤና ደህንነት ስጋት የሆኑ ምርቶች በገፍ እንዲገቡም ስለማድረጉ ይነገራል፡፡
ባለፈው ዓመት በአንድ ቀን ሰባት ኪሎ ግራም ወርቅ በቁጥጥር ስር መዋሉ አይዘነጋም፡፡ የህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤትም ንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ የሶማሌ ክልልን ተዘዋውሮ ካጤና በኋላ፤ በክልል ብቻ በቀን አንድ ሽህ ስድስት መቶ የቁም እንስሳት በህገ ወጥ ድንበር እንደሚሻገሩ ይፋ አድርጓል፡፡ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቀንድ ከብት ባለቤት የሆነች ኢትዮጵ በዘርፉ ከስጋና ከቀንድ ከብት የተያዘው የወጪ ንግድ ዕቅድ በየዓመቱ እምብዛም አይሳካም፡፡ ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም በተለይ ወደ ውጪ በመላክ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ከእቅዷም ሆነ ካላት አቅም ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው። ለዘርፉ አፈፃፀም ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም የኮንትሮባንድ ንግዱ እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖ ግን ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ለአብነትም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤በ2011 በጀት ዓመት አስር ወራት የቁም እንስሳት፣ ሥጋ እና የሥጋ ተረፈ ምርት ወደ ውጪ በመላክ ከ113 ነጥብ 8ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። ወደ ውጪ የተላከው የቁም ከብት ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አስር ወራት ጋር ሲነፃፀር በ28 ነጥብ 71 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ ወደ ውጪ የተላከ ሥጋም በገቢ 6ነጥብ 27 በመቶ እና በእቅድ ከተያዘው አንጻር ደግሞ በ35ነጥብ67 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
በቁም ከብት ብቻ የተገኘው ገቢ 36ነጥብ 89ሚሊዮን ዶላር መሆኑንና ይህም የገቢ ዕቅዱን 30 ነጥብ47 ከመቶ ነው። አፈጻጸሙም ከ2010 ተመሳሳይ አስር ወራት ጋር ሲነፃፀር በተላከ መጠን 35 ነጥብ 67 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣በገቢ ግን 28ነጥብ 71 በመቶ ቅናሽ የታየበት ሆኗል። የዘርፉ ተዋንያን ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሀብቷ ከምታገኘው ገቢ ይልቅ ኬኒያ፣ ግብፅና ጅቡቲን የመሳሰሉ ሀገራት በህገ ወጥ መንገድ በገፍ ከሚወጡት እንስሳት የበለጠ ተጠቃሚ ናቸው፡፡
የማዕድን ምርቱ ላይም በሕገወጥ መንገድ የሚደረገው ግብይት እጎላ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ የከበሩ ማዕድኖች ህጋዊ ግብይቱን ተረማምዶ ከሚሄደው የበለጠው በኮንትሮባንድና ሕገወጥ በሆነ መንገድ እየሄደ ነው ስለመሆኑ መንግስትም ያምናል፡፡ በ2004 ዓ/ም ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፍ 600 ሚሊዮን ዶላር ታገኝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ሰባት ዓመታት አፈፃፀሙ ከዓመት ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡ በ2011 በጀት ዓመት የማዕድን የወጪ ንግድ በ15 እጥፍ ቀንሶ ሀገሪቱ 50 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ማግኘቷን የማዕድንና የነዳጅ ሚንስቴት ይናገራል፡፡
ለዘርፉ ዝቅተኛ የንግድ አፈፃፀም ህገ ወጥ ንግድ መጧጧፍ በምክንያትነት ይነሳል፡፡ በተለይም ወርቅ ከባህሪውና ካለው ከፍተኛ ዋጋ ጋር ተያይዞ ለኮንትሮባንድ ንግድ ተጋላጭ መሆኑን የሚናገረው ሚኒስቴሩ፤ የማዕድን ዘርፉን ህገ ወጦች ገንዘብን ለማሸሽም እየተጠቀሙበት መሆኑን በስጋት ይገልፃል፡፡
በአጠቃላይ የኮንትሮባንድ ንግድ የገንዘብና ውጭ ምንዛሬ ፖሊሲን፣ የሀገር ውስጥ አምራቹንና ነጋዴውንም እየጎዳ እንዲሁም ዳግም ወደ ምጣኔው ፈሰስ ሲደረግ ለመልካም ተግባር አለመዋል ወዘተ ተደማምሮ ጣጣውን ዙሪያ መለስ አድርጎታል፡፡
የኮንትሮባንድ መነኸሪያ እየሆነች የመጣችውን ሀገሪቷን ለመታደግ፣ በንግዱ ዘርፉ ጤናማ ተወዳዳሪ እንዲኖር እንዲሁም በኮንትሮባንድ ንግዱ የተገኘው ገንዘብ መልሶ ሀገር ውስጥ መግባትን ለመከላከልና ፤ የገቢዎች የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ይላል፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድ የሚያደርሰውን የምጣኔ ሀብት ጫና ተረድቻለው የሚለው ገቢዎች ሚኒስቴር 36 አዳዲስ የቁጥጥር ኬላዎችን መክፈቱን እና ከዚህ ቀደም ስልታዊ ያልሆኑና ያለቦታቸው የተቀመጡ ኬላዎችን ወደ ትክክለና ቦታቸው ማስተካከልን የመሰሉ የአደረጃጀት ስራዎች መሰራታቸውን ይናገራል፡፡
የድንበር ቁጥጥሩመወ ባለቤት እንዲያገኝና ጠንካራ ለማድረግ ጥናት ተካሂዶ አንድ ሽህ አራት መቶ የሚደርሱ የጉሙሩክ ፓሊሶች እንደሚስፈልጉ ተረጋግጧል፡፡ አሁን ላይ የጉሙሩክ ስርዓትንና የኬላ ቁጥርርን የሚያስፈፅሙ 600 ፖሊሶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መሰማራታቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በሀገሪቱ 94 የሚሆኑ ኬላዎች ቢኖሩም ታዲያ፤ በህገ ወጥ ንግድ በጉሙሩክ የቁጥጥር ሠራተኞች ሳይቀር በሠንሰለቱ የተተበተበና ስር የሰደደ መሆኑ ይነገራል፡፡ በሀገር ላይ ኪሳራው ወደር የለሽ እየሆነ የመጣው የኮንትሮባንድ ንግድ ስልቱንና መልኩን እየቀያየረ አልጨበጥም ስለማለቱ እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህም ለመንግስት በፈተና ላይ ፈተና ሆኖበታል፡፡
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን