የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ገመናው ሲገለጥ

በሠላም ዓለሙ

/Inflation-ethiopiaMarch 2, 2020 (Ezega.com) -- የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በተለይም ባለፉት ዓመታት በርካታ ይበል የሚያሰኙ ነገሮች ተብለውለታል፡፡ በሁለት አሀዝ አድጓል፤ ተመንድጓል፤ ይህም ሀገሪቷን በፈጣን እድገት ላይ ያለች ቀዳሚ ሀገር አሰኝቷቷል የሚሉ የመንግስት መግለጫዎች ባለፉት ዓመታት ተሰምተዋል፡፡ ይሁን እንጂ እውነታኛ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት አፈፃፀም መንግስት እንደሚለው አይደልም ሲሉ በጥናታቸው ምርመራ ደረጉ የዘርፉ ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡ እድገትን ከልማት ጋር አንድ አድርጎ የመሳል ጥንውትንም ባለሞያዎቹ ነቅሰው ያወጣሉ፡፡

የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት በጥቅሉ እድገት ቢኖረውም ከዋጋ ግሽበት፣ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ከገቢና ወጪ ንግድ ሚዛን መዛባት እንዲሁም ከውጭ የእዳ ጫና ጋር ሲመረመር እውነታው ከዚህ የራቀ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህም በመሆኑ ምጣኔ ሀብቱ “የተናጋ ነው” ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሆኑት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ፡፡ የጥቅል ምጣኔ ሀብት ፖሊሲ እና “በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ የመንግስት ሚና” በሚል ርዕስ ከወራት በፊት በተካሄደ ውይይት ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር አለማየሁ፤ የኢትዮጵያ ያለፉት ዓመታት የምጣኔ ሀብት እድገት በአብዛኛው በብድርና በገንዘብ ማተም የመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ መንግስት እንደሚለው ድህነት አልቀነሰም፤ በሀብታምና በደሀ መካከል ያለው ሠፊ ልዩነት በተባለው ልክ አልጠበበም ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚጠቅሱት ተመራማሪው፤ የ11 ዓመታትን የምጣኔ ሀብት የእድገት አፈፃፀም ለአብነት ያነሳሉ፡፡ በእነዚህ ዓመታት በመንግስት አሀዝ ምጣኔ ሀብቱ በአማካኝ በ10 ነጥብ አራት በመቶ አድጓል ቢባልም፤ ይህ እድገት የተጋነነ ነው፤ ከስድስት በመቶ አይዘልም፤ የእድገት ምንጩም የተሳሳተ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር አለማየሁ፡፡

ለምጣኔ ሀብቱ መናጋት ፕሮፌሰር አለማየሁ የተለያዩ ምክንቶችን የሚጠቅሱ ሲሆን፤ ባለፉት ዓመታት ተመዝግቧል የሚባለው እድገት በአብዛኛው በብድርና በገንዘብ ማተም የመጣ መሆኑን በቀዳሚነት ይጠቅሳሉ፡፡ አስከ መጋቢት ወር 2011 ድረስ ከብሄራዊ ባንክና ከገንዘብ ሚኒስቴር በተገኘ መረጃ 26 ቢሊዮን ዶላር (የአይ ኤም ኤፍን የሦስት ቢሊዮን ዶላር ብድር ሳጥጨምር) የውጭ የብድር እዳ ናላዋን የሚያዞራት ኢትዮጵያ፤ የሀገር ውስጥ ብድሯም ከዚህ የማይተናነስ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የውጩም የሀገር ውስጡም ብድር ተደምሮ ኢትዮጵያ 52 ቢሊዮን ዶላር ባለእዳ ናት፡፡ ይህም በብር ሲተመን (እስከ አለፈው ዓመት ድረስ)  ያልተከፈለ የሀገር ውስጥና የውጭ ብድሮች ዕዳ 1 ነጥብ 5 ትሪሊን ብር ነው፡፡

ገንዘቡንም በተበደረችው ልክ ለልማት አለማዋሏን የሚነሱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ፤ ለዚህም መንግስት የጠራ የንድፈ ሀሳብ መሠረት አልነበረውም ይላሉ፡፡ ምጣኔ ሀብቱን የሚመራው ግብርናው እና ይህን ክፍላተ ምጣኔ ሀብት ከሌላው ዘርፍ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ እምብዛም አለመደረጉን በማሳያነት ያነሳሉ፡፡

ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በዝውውር ውስጥ የነበረ የኢትዮጵያ የገንዘብ ኖት 68 ቢሊየን ብር እንደነበር የሚያስታውሱት ፕሮፌሰሩ፤ አሁን ይህ መጠን 740 ቢሊየን ብር መድረሱን ይናገራሉ፡፡ የገንዘብ ኖት መጠኑ በየዓመቱ በ27 በመቶ ሲያድግ ቆይቷልም ባይ ናቸው፡፡ የገንዘብ ኖት እድገቱ መሆን የነበረበት አራት እና አምስት እጥፍ የበለጠ እንደሆነ ፕሮፌሰር አለማየሁ ይገልፃሉ፡፡

ካለፉት 10 እና 15 ዓመታት ወዲህ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብቱ እድገት እንዳሳየ ሲነገር ቢኖርም መዋቅራዊ ለውጥ ግን አላመጣም ይላሉ ፕሮፌሰር አለማየሁ፡፡ ይህም ምርታማነት እንዳይጎለብት አድርጓል አለፍ ሲልም ስራ አጥነትንና ድህነትን እንዲቀንስ አላደረገም ሲሉም ትችታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

ሌላው በውይይት መድረኩ ተሳተፉት የምጣኔ ሀብት ባለሞያ ዶ/ር ቴዎድሮስ መኮንን፤ በኢትዮጵያ እድገት ቢኖርም ወደ ልማት መቀየርና ማስቀጠል ላይ ጉድለት መኖሩን ያነሳሉ፡፡ ሀገሪቱ በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የገጠማት የውጭ ምንዛሬ እጦት እና ከሁለት አሀዝ የተሻገረው የዋጋ ግሽበት የጥቅል ምጣኔ ሀብት ወይም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ስለማስከተሉ ይናገራሉ፡፡ ይህም እድገት ቢኖርም እንኳ ከእድገት መጠቀም እንዳይቻል አድርጓል ሲሉ፤ የተጠቃሚነት ክፍተት ያነሳሉ፡፡

እድገትና ልማት የሚለያዩ ጉዳዮች መሆናቸውን የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ያሰምሩበታል፡፡ በኢትዮጵያ ማህበረሰቡ የሚያነሳውን “እድገት ካለ ለምን ተጠቃሚ አልሆንም?” የሚል እሮሮዎችን በአብነት ያነሳሉ፡፡ እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል መጥቷል ከሚባለው እድገት ተጠቃሚ እንዳይሆን ለምጣኔ ሀብት እድገት ማነቆ የሆኑትን ለምሳሌም በወጪ ንግድ ላይ ሳይሆን በውጭ ብድር ላይ የተመሰረተ የመሠረተ ልማት ግንባት፣ ስራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበት ተፅዕኖን ያነሳሉ፡፡ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት የተሻለ እድገት ቢኖረውም ማህበረሰቡ ከተፈጠረው እድገት ተጠቃሚ ለመሆን ስራዎች ይቀራሉ ሲሉም ለጉዳዩ መፍትሄና ትኩረት እንደሚያሻው ይናገራሉ፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት መዋዕለ ነዋይ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ያለው ድርሻ 40 በመቶ ሲሆን በሀገሪቱ ቁጠባ ደግሞ 22 በመቶ ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ሰፋ ያለ ልዩነት መንግስት ለገንዘብ አቅርቦት ፊቱን ወደ ብድር እንዲያዞር ማድረጉን ፕሮፌሰር አለማየሁ ይናገራሉ፡፡

ለዚህም የመንግስት ሚና የልማታዊ መንግስት ርዕዮተ ዓለምን እየተከተለ የሠለጠነ የሠው ኃይል አልነበረውም የሚሉት ተመራማሪው፤ ፖለቲካውም ኢ-ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልንና ድህነትን አስከትሏል ይላሉ፡፡

ከዚህ ጤናማ አይደለም ከሚባለው ምጣኔ ሀብት ለማገገምና ለመውጣት መንግስት የፋይናንስ ማሻሻያ ማድረግ አለበት የሚሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ የገቢና የወጪ ንግድ ስርዓትን እንዲሁም የገንዘብ ልቀት መጠኑን ማስተካከል አስፈላጊ ነው፤ ይህንንም ለማድረግ ጠንካራ ተቋማትና እውቀትን መሠረት ደረጉ ፖሊሲዎች ያስፈልጋሉ ይላሉ፡፡

በምጣኔ ሀብቱ የግልና የመንግስት የሚሉ ጎራዎችን ማፍረስ ያስፈልጋል ሲሉ የመፍትሄ ምክረ ሀሳባቸውን የሚናገሩት ፕሮፌሰር አለማየሁ፤ ሁለቱ ክፍላተ ምጣኔ ሀብቶች ተመጋጋቢና ጤናማ ፉክክር ሊያደርጉ የሚችሉ መሆን አለባቸው ይላሉ፡፡ ከዚህ በኋላም ሀገሪቱ በቅይጥ ምጣኔ ሀብት መመራት አለባት ሲሉ፤ በ2012 ዓ/ም ከሰባት በመቶ አድገት ወደ ዘጠኝ በመቶ ምጣኔ ሀብቱን አሳድጋለሁ ብሎ ላቀደው መንግስት ይመክራሉ፡፡

መንግስት አሁን ላይ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎችን እያካሄድኩ ነው ይላል፡፡ የዚህ ማሻሻያ አንድ እርምጃ የሆነውና ከተዘፈቀበት የእዳ ጫና ለመውጣት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ፤ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉና በከፊል ለግሉ ዘርፍ ማዘዋወር ይጠቀሳል፤ ምንም እንኳ እርምጃው ከወዲሁ ትችት ቢበዛበትም፡፡ ስራ አጥነትና ድህነትን ለመቀነስ እንዲሁም እያማረረ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር መንግስት ትከረት አድርጌያለሁ እያለ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የምግብ ዋጋ ንረት በስድስት ኣመታት ውስጥ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የመንግስት የበጀት ጉድለት 97 ቢሊዮን ብር ሆኖ የሀገሪቱን ጠቅላላ ምርት አራት በመቶ ድርሻም ይዟል፡፡ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ መፍትሄ እያገኘ ነው ቢባልም በተለይም የግል የንግድ ድርጅቶች በእጥረቱ ከስራ እየወጡ ሲሆኑ፤ የግንባታ ዘርፉ ላይ ጫናው መበርታቱም ይነገራል፡፡

በእነዚህ ፈተናዎች ተጠምዶና በፖለቲካ ትኩሳት መሀል ሆኖ ማሻሻያ እደረገ ያለው መንግስት (ለምሳሌ፣ ፕራይቬታይዜሽንና ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ) ምን ያህል ውጤታማ ይሆን? የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ብቻም ሳይሆን የመቶ ሚሊዮኖች የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :