በአለም አቀፍ የወንጀል ቡድን ወደ ኢትዮጵያ የገባ የጦር መሳሪያ መያዙ ተነገረ
ኢዜጋ ሪፖርተር
March 11, 2020 (Ezega.com) -- የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በአለም አቀፍ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ቡድን አማካኝነት በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በሽፋን የገባ ሁለት ኮንቴነር ህገወጥ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረጉን አስታወቀ። ተቋሙ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ መሰረት መነሻውን ከቱርክ ሜርሲን ወደብ ያደረገው ህገወጥ የጦር መሳሪያው በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በሽፋን ገብቶ በቁጥጥር ስር የዋለው በወደቡ ለአምስት ወራት ያህል በድብቅ ተቀመጦ በረቀቀ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ከገበ በኋላ ነው። ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ህገወጥ የጦር መሳሪያውን በተመለከተ የመረጃ ጥቆማ ካገኘበት ወቅት አንስቶ ለረጅም ግዜ አስፈላጊውን ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁሞ ህገወጥ የጦር መሳሪያው በምን መልኩ፣ እንዴትና በማን ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችል ለመለየት ልዩ የኦፕሬሽን ስራ ሲያካሂድ መቆየቱን አስረድቷል።
ግምታቸው ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የሆኑ 501 እሽግ ካርቶኖች ከ18 ሺህ በላይ ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች ጋር መያዛቸውን የጠቆመው መግለጫው ለሽፋን እንዲያገለግሉ ታስቦ የተዘጋጁና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በውስጣቸው የያዙ 229 እሽግ ካርቶኖችም ጭምር በቁጥጥር ስር ውለዋል። ይህ ሁለት ኮንቴነር ህገወጥ የጦር መሳሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ቢሰራጭ ኖሮ በሀገርና በህዝብ ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋና ስጋት ይደቅን እንደነበር የገለፀው መግለጫው የጦር መሳሪያውን በቁጥጥር ስር የማዋል ኦፕሬሽኑ በስኬት በመጠናቀቁ ምክንያት ሀገርና ህዝብን ከተደቀነበት ጥፋት የመታደግ ተልዕኮውን በአግባቡ መወጣት ተችሏል። ሀገሪቷንና ህዝቦቿን ወደ ትርምስ ለማስገባት የተወጠነውን ሴራ ለማክሸፍ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያውን በቁጥጥር ስር ከማዋል ጀምሮ ከኢትዮጵያ ውጪ በሌሎች ሀገራት የተዘረጉ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችን መረብ በማሰስ ለመበጣጠስ የሚያስችሉ ኦፕሬሽኖችን በብቃት ለመወጣት መቻሉን መግለጫው ጠቁሟል።
በሀገር ውስጥ በተካሄደው ኦፕሬሽንም ወደ አገሪቱ የገባውን የጦር መሳሪያ ተቀብለው በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለማሰራጨት የተዘጋጁ 24 ተጠርጣሪዎችን የጦር መሣሪያውን ለመረከብ በዝግጅት ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጎ ምርምረው በሚመለከተው አካል መቀጠሉን መግለጫው አመልክቷል። ብሄራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ድንበር ተሸጋሪ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችን እና የጦር መሳሪያውን በቁጥጥር እንዲውል ከማድረጉም በተጨማሪ ከጅቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከሊቢያ፣ ከቱርክ እና ከአሜሪካ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ድንበር አቋርጠው ወደ ሀገር ውስጥ ያስገቡ እና ያልተያዙ አለምአቀፍ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የክትትልና የቁጥጥር ስራው መጠናከሩን በመግለጫው አስታውቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም 7 የተለያዩ ሃገራት ዜግነት ያላቸው የውጭ ተጠርጣሪዎች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥም 2 የሱዳን ዜግነት ያለቸው ተጠርጣሪዎች ከሱዳን የመረጃ ተቋም ጋር መረጃ በመለዋወጥ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። ሌሎች በቁጥጥር ስር ያለውሉ ተጠርጣሪዎችን ከሊቢያ፣ ከጁቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከቱርክና ከአሜሪካ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር መረጃ በመለዋወጥ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሰር ለማዋል የትብብር ስራ መጀመሩንም አገልግሎቱ መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። "በከፍተኛ ክትትል እና የተቀናጀ ኦፕሬሽን" በቁጥጥር ስር የዋለው የጦር መሳሪያ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን በማባባስ እና ከፍተኛ እልቂት ለመፍጠር ሲባል የተዘጋጀ መሆኑን የገለፀው ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ይህን እኩይ ተልእኮ በተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ቀን ከሌሊት ክትትልና ቁርጥኝነት ማክሸፉ መቻሉን አመልክቷል።
ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት የጦር መሳሪያው በቁጥጥር ስር እንዲውል በወሰዳቸው እርምጃዎች የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የፌደራል፣ የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች ላደረጉት ከፍተኛ ድጋፍ ምሰጋና አቅርቧል። የህብረተሰቡም የተለመደ ትብብርና ድጋፍ ለኦፕሬሽኑ መሳካት ከፍተኛ ሚና እንደነበርውም አክሎ ገልጿል። በቀጣይም ህብረሰተሰቡ እየረቀቀ እና አየተባባሰ የመጣውንና ሀገርንና ህዝብን ሰላም የሚያናጋውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ወንጀል ለመካለካል በሚደረገው ጥረት ወስጥ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን