በግድቡ ላይ የሚቃጣን ጥቃት መክተን አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን - የአየር ሃይል ዋና አዛዥ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Eth-Airforce-logoMarch 12, 2020 (Ezega.com) -- የኢፌዴሪ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ አየር ሃይሉ በቀጠናው በተለይም በግድቡ ላይ ከማንኛውም አካል የሚቃጣን የአየር ላይ ጥቃት ለመመከት ብሎም አስፈላጊውን አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። ኣዛዡ ይህንን ያሉት ከኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀኔራል አደም መሃመድ እና ከሌሎች የሰራዊቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋራ በመሆን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በጎበኙበት ወቅት ነው። በጉብኝቱ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል። በዚህ ወቅት የመከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ህዝቦች ሰላምና ሉዓላዊነት የማስከበር ተልዕኮውን ለመወጣት በላቀ ብቃት ላይ የሚገኝ መሆኑን ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሃመድ ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ ሀገራዊ ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ህዝብ እና መንግስት የሰጡትን ተልዕኮ በላቀ ብቃት እየተወጣ መሆኑን የገለጹት ጀኔራል አደም ከዚህም በተጨማሪ የሰራዊቱ አባላት ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየወሩ ከደመወዛቸው በመቆጠብ የዜግነት ድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን አንስተዋል። ጉብኝቱ መከላከያ ሰራዊቱ የህዳሴ ግድቡ የግንባታ ሂደት ያለበትን ሁኔታ በመረዳት በአሁኑ ወቅት ከተለያየ አቅጣጫ የሚነዛውን አሉባልታ ለመመከት ተነሳሽነት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑንም ሃላፊው ተናግረው የመከላከያ ሰራዊቱ ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ እንደመጣ ሁሉ ወደ ፊትም ይህንን ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚቃጣን ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት እና አስፈላጊውን አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት የኢፌዴሪ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው አየር ሃይሉ ለዚሁ ተልእኮ እያንዳንዷን ደቂቃ በንቃት እየተከታተለ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሀገር መከላከያ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የልዑካን ቡድን በሱዳን ጉብኝት ማድረጉ ተሰምቷል። የልዑካን ቡድኑ በጉብኝቱ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብደላ ሀምዶክ፣ ከሱዳን መከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ጀማለዲን ኦማር እና ከሱዳን ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ኡስማን መሐመድ ጋር ውይይቶችን ያካሄደ ሲሆን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ በመሆኑ ሀገሪቱ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዳላት በድጋሚ ማረጋገጧን በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል። ከዚህም ሌላ የልዑካን ቡድኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብደላ ሐምዶክ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የላኩትን መልዕክትም አድርሷል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ ያወገዙት የልዑካን ቡድኑ አባላት እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ወቅት ኢትዮጵያ ከሱዳን ጎን እንደምትቆም አረጋግጠው የሱዳን ሰላም እና ብልጽግና የኢትዮጵያ እንደሆነ ሁሉ የሱዳን ችግርም እንዲሁ የኢትዮጵያ ጭምር እንደሆነ መናገራቸው ተሰምቷል።

በተያያዘም ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ ያላትን አቋም ለማስረዳት ወደተለያዩ የዓለም ሀገራት ልኡካን ቡድኖችን ልካለች። በዚሁ መሰረት በፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የተመራ ከፍተኛ የሀገሪቱ የልኡካን ቡድን ወደ ኬንያ ናይሮቢ በማቅናት ኢትዮጵያ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ያላትን ግልጽ አቋም ለፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አስረድቷል ተብሏል። ሁለቱ መሪዎች ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ የጋራ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤትን ጠቅሶ የዘገበው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የመግለጫውን ዝርዝር ይዘት በተመለከተ ግን ያለው ነገር የለም ። በፕሬዚዳንቷ የሚመራው የልኡካን ቡድን በቀጣይም በሌሎቹ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ተመሳሳይ ጉብኝት በማድረግ የኢትዮጵያን አቋም እንደሚያስረዳ ተነግሯል።

በተመሳሳይ በቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድንም ከዛሬ ጀምሮ በአውሮፓ በመገኘት ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ያላትን ግልጽ አቋም የሚያብራራ መሆኑ ተሰምቷል። ልኡኩ በቆይታው ከአውሮፓ ህብረት ፕሬዚዳንት፣ ከፈረንሳይ እንዲሁም ከሌሎች የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር በመገናኘት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን አቋም ለማስረዳት ያቀደ ሲሆን በቀጣይም ተመሳሳይ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን በአሜሪካ እና በሌሎች ሀገሮች በመዘዋወር ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያላትን ግልጽ አቋም እንደሚያስረዳ መንግስት አስታውቋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :