የግድቡን መደራደሪያ ሰነድ የሚያዘጋጁትን ባለሞያዎች ያላግባባው ምንድን ነው?

ኢዜጋ ሪፖርተር

GERDMarch 14, 2020 (Ezega.com) -- አሜሪካ በህዳሴ ግድቡ ውሀ አሞላልና አለቃቀቅ እንዲሁም በድርቅ ማካካሻ መርሀ ግብር ላይ ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳንን ለማደራደር የሄደችበት መንገድ ኢትዮጵያን ያላስደሰተ ሆኖ ሂደቱ ተስተጓጉሏል። በአሜሪካና አለም ባንክ  የተዘጋጀው ሰነድ ከመፈረም የተረፈውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ ዋሽንግተን ለዚህ ጉዳይ አልሄድም በማለታቸው መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ አስነብቧል። አሜሪካ ያዘጋጀችው የስምምነት ሰነድ ላይ ኢትዮጵያ አልፈርምም ማለቷ ተገቢ ውሳኔ በመሆኑ ከበርካታ ዜጎች ይሁንታን ያገኘ ሲሆን መንግስትም ይህንን ሰነድ የሚተካና ለግብጽና ሱዳን የሚቀርብ አዲስ የስምምነት ሰነድ እያዘጋጀ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም በኢትዮጵያ በኩል እየተዘጋጀ ነው የተባለው የግድቡ የውሀ አያያዝና አለቃቀቅ ሰነድ በሚይዛቸው ይዘቶች ዙሪያ በውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለና በተዋቀረው የተደራዳሪዎች ቡድን አባላት መካከል አለመግባባቶች እንዳሉ ተዘግቧል። ዋዜማ ከታማኝ ምንጮች ተገኙ ባላቸው መረጃዎች መሰረት ዋናው የክርክሩ መነሻ ደግሞ ግድቡ ውሀ በሚሞላበት ጊዜ በየአመቱ መለቀቅ ያለበት ዝቅተኛው የውሀ መጠን ላይ ነው ተብሏል።

አብዛኞቹ የሰነዱ አዘጋጅ ቡድን አባላት ግድቡ በሚሞላበት ጊዜ በየአመቱ ወደ ታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መለቀቅ አለበት የሚሉት የውሀ መጠን 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ሲሆን ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ ደግሞ 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ይሁን የሚል አቋም እንዳላቸው ተስምቷል። የድርድር ሂደቱን በቅርበት የሚያውቁ ምንጮች እንደተናገሩት ከሆነ ኢትዮጵያ ግድቡን ስትሞላ በየአመቱ ወደታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዲለቀቅ መስማማት ያለባት 31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ እንጂ ከዚህ በላይ ወይም እንደሚባለው 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ መሆን የለበትም። እንደ ባለሞያዎቹ አስተያየት በኢትዮጵያ ከ1977 አ.ም ጀምሮ ለተወሰኑ አመታት ድርቅ ሲከሰት የአባይ ውሀ አመታዊ ፍሰት 31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ነበር። ያም ሆኖ ግብጽ ላይ በወቅቱ የተለየ ተጽእኖ አለማሳረፉ ተረጋግጧል። 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በሚለው መስማማት ግን የግድቡ ውሃ አሞላል ላይ ከፍተኛ መዘግየትን ያስከትላል። ግብጽ ግድቡ በሚሞላ ጊዜ ከፍ ያለ መጠን ያለው ውሀ ይለቀቅልኝ የምትለው ግድቡ ቶሎ እንዳይሞላ ነው የሚሉት ባለሞያዎቹ  ስለዚህ የዚህ ቁጥር አወሳሰን ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ።

የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ 37 ቢሊየን ሜትር ኩዩብ ላይ የቆሙበት ምክንያት መነሻው ሲብራራም አሜሪካና የአለም ባንክ የሶስትዮሽ ድርድር ውስጥ ገብተው አራት ስብሰባዎች እንዲደረጉ ሲወሰን ግብጽ ግድቡ ሲሞላ በየአመቱ 40 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ይለቀቅልኝ ስትል ኢትዮጵያ ደግሞ 31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ይሁን የሚል አቋም ላይ ነበረች። ታድያ ካርቱም ላይ የሱዳኑ ተወካይ በኢትዮጵያና ግብጽ መሀል ገብተው አማካዩ ላይ ማለትም በ35 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ አመታዊ ፍሰት ላይ እንዲስማሙ ያደርጋሉ። የግብጹ የውሀ ሚኒስትር መሀመድ አብደል አቲ ግን የድርድር ቡድኔ በ35 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ አልስማማም አለኝ ብለው ሀሳባቸውን ይቀይራሉ። ታዲያ አዲስ አበባ ላይ የቀጠለው ስብሰባ ላይም ይኸው ንትርክ አልቋጭ ስላለ የኢትዮጵያው ውሀ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ ከመቀመጫቸው ተነስተው "በ37 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ ተስማምተን እንጨባበጥ! ይሄን ሀሳቤን የኔ ቡድን ባይቀበለኝም ግን እንስማማ" ይላሉ። ግብጾች ግን 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ አመታዊ ፍሰትንም አንቀበልም አሉ። ይሄም የመጣው በኢትዮጵያ በኩል የአቋም መለሳለስ በተደጋጋሚ ስለታየ ግብጾች ይበልጥ የአቋም መለሳለስ እንዲኖር በመጠበቃቸው ነው ተብሏል። ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ ይህ ቁጥር ላይ የቆሙትም ሀገሪቱ በታዛቢዎች ፊት የያዘችው አቋም በመሆኑ ሀሳብ መቀየሩ ተገቢ አይደለም ብለው ስላሰቡ መሆኑ ተሰምቷል።

የህዳሴው ግድብ አንዴ ከተሞላ በኋላ በሚኖረው የረጅም ጊዜ የግድቡ ኦፕሬሽን ወቅት በየአመቱ የሚለቀቀው ውሀም ከዚህ ቀደም ሊፈረም ተቃርቦ እንደነበረው ሰነድ ኢትዮጵያን በተለያዩ ቁጥሮች ግዴታ ውስጥ የሚጥል ሳይሆን ግድቡ አንዴ ከሞላ በኋላ የሚኖር ትነትና ለሀገር ውስጥ የወደፊት ተጠቃሚዎች ሊውል የሚችለው ተቀናንሶ የተለያዩ ሁኔታዎችንም አገናዝቦ በመቶኛ ብቻ ነው መቀመጥ ያለበት ያሉት ባለሞያዎቹ ከዚህ በተረፈ የሰነዱ ዝግጅት በጠንካራ መግባባትና ሀገራዊ መንፈስ በመካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :