የኢትዮጵያ ወታደሮች የኬንያን ድንበር አልፈው በመግባት 5 ንጹሃንን ገድለዋል - የኬንያ ባለስልጣናት

ኢዜጋ ሪፖርተር

Moyale-KenyaMarch 15, 2020 (Ezega.com) -- በኬንያዋ ማርሳቢት ግዛት ውስጥ በምትገኘው ሞያሌ ከተማ ልዩ ቦታው ሴሲ በተባለ መንድር በድንገት ወረራ የፈጸሙ የኢትዮጵያ ወታደሮች 5 ንጹሃን ዜጎችን ተኩሰው ገድለዋል ሲሉ የሀገሪቱ በርካታ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ወታደሮቹ ግድያውን የፈጸሙት የአካባቢው ነዋሪዎች በኢትዮጵያ ጥቃት ፈጽመው የሸሹ የተቃዋሚ ቡድን አባላትን ሸሽገዋል በሚል ምክኒያት መሆኑን የአይን እማኞችን ጠቅሰው ዘ ስታርና ዘ ስታንዳርድ የተባሉት የሀገሪቱ ጋዜጦች አስነብበዋል። ከትናንት በስቲያ ከምሽቱ 3:30 ላይ ወታደሮቹ የአንድ መኖሪያ ቤትን በር ገንጥለው በመግባት በቤቱ ውስጥ የነበሩ ባልና ሚስትን የገደሉ ሲሆን ከደቂቃዎች በኋላም እነዚሁ ታጣቂዎች በአካባቢው ሌሎች 2ሴቶችን መግደላቸው ተሰምቷል። በዛው እለት ከእነዚህ ግድያዎች ቀደም ብሎም በመንደሯ በሚገኝ የአውሮፐላን ማረፊያ ሜዳ አካባቢ ወደ መኖሪያ ቤቱ በመሄድ ላይ የነበረ አንድ በእድሜ የገፋ የአካባቢው ነዋሪ በወታደሮቹ መገደሉን የጋዜጦቹ መረጃ  ያመለክታል።

የተፈጸመው ግድያ በሞያሌና በሌሎች የሁለቱ ሀገራት ድንበር ከተሞች በሚኖሩ ነዋሪዎች ዘንድ ፍርሃት በመፍጠሩ በተለይ ከአርብ እለት አንስቶ በርካታ ኬንያውያን አካባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋልም ተብሏል። ጥቃቱን ተከትሎ የማርሳቢት ግዛት የደህንነት ሃላፊዎች በጉዳዩ ዙሪያ ዝግ ስብሰባ ማድረጋቸውን የዘገቡት ጋዜጦቹ ያንን ተከትሎም ሃላፊዎቹ ግድያውን አውግዘዋል ብለዋል። በተጨማሪም የግዛቲቱ ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ፓትሪክ ሙማሊ ሁኔታውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸውን አስነብበዋል። ከዚህም ባለፈ የማርሳቢት ግዛት ገዢ ሞሃሙድ አሊ እና ሴናተር ጎዳና ሃርጉራ በሀገሪቱ መንግስት ደረጃ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የጋራ ምክክር በማድረግ እንደነዚህ አይነት ህገ ወጥ ተግባራት በአስቸኳይ እንዲቆሙ እንሰራለን ማለታቸው ተስምቷል።

ጥቃቱ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በናይሮቢ ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከመከሩ ከሰአታት በኋላ መፈጸሙ ነገሩን አስገራሚ እንዳደረገውም ተዘግቧል። መሪዎቹ በውይይታቸው በሁለቱ ሀገራት የድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ማስቆም በሚቻልበት መንገድ ዙሪያም ምክክር አድርገዋል ተብሏል።

በግድያው ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን የተሰጠ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ የለም። ይሁን እንጂ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በቅርቡ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ሰራዊቱ በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ እና ቦረና አካባቢዎች ታጥቆ በሚንቀሳቀስ ኃይል ላይ እርምጃ እየወሰድ መሆኑን ገልጸው ነበር "በምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ ህዝቡን እያስገደዱ ቡና እያስመጡ ወደ ኬንያ አሻግረው ይሸጡ ነበር ሕዝብ ሲንገላታ ቆይቷል። ይህ የሆነው ደግሞ መንግሥት ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት የኃይል እርምጃ ሳይወስድ በመቅረቱ ነበር። ኦፕሬሽን ካካሄድን በኋላ ሁለቱም ጉጂዎች ነጻ ወጥተዋል። አሁን መደበቂያ ሲያጡ ወደ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ድንበር ሸሽተዋል።"በማለት እያካሄዱት የሚገኘው ወታደራዊ እርምጃ ውጤት ማምጣቱን ማብራራታቸው ይታወሳል። ከእዚህ የምክትል ኢታማዦር ሹሙ መረጃ አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ ወታደሮች ታጣቂ ሃይሎችን ታስጠልላላችሁ በሚል ግድያ ፈጽመዋል የሚለው የኬንያውያኑ ክስ ለእውነት የቀረበ መሆኑን መናገር ይቻላል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :