የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 ሃገራት የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ
ኢዜጋ ሪፖርተር
March 20, 2020 (Ezega.com) -- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 ሃገራት የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከየትኛውም ሃገር ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ለ14 ቀናት በልዩ ማቆያ የመቆየት ግዴታ እንደተጣለባቸው እና በዚህ የ14 ቀናት ቆይታቸውም ወጪያቸውን ሙሉ በሙሉ ራሳቸው እንዲሸፍኑ መወሰኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ሀገራዊ ስጋቶችና በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማምሻውን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሰረት የህግ ታራሚዎችን በሚመልከት በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ቫይረሱ ከገባ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጠር በመሆኑ ህጻናትን የያዙ፣ የአመክሮ ጊዜያቸው የደረሰ እና ቀለል ያለ ክስ ያለባቸው ታራሚዎች በነጻ እንዲለቀቁ መወሰኑንም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ የምሽት መዝናኛ ክለቦች አገልግሎት እንዳይሰጡ ሙሉ ለሙሉ ተከልክሏል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ የእምነት ተቋማትን አስመልክተው በሰጡት መረጃም ቤተ እምነቶቹ ከሚሰበስቧቸው በርካታ ቁጥር ካላቸው ሰዎች አንጻር ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሊሆኑና ከፍተኛ ጉዳት ሊፈጠር ስለሚችል እንደየአምልኳቸው ሁኔታ የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያሳልፉም ከስምምነት መደረሱን ነው ያስታወቁት።
ቫይረሱ ከተከሰተ በኋላ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ማስከተሉን በመግለጫቸው ያስታወቁት አብይ አህመድ ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ በቫይረሱ መቀስቀስ ምክንያት ከ190 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማጣቱን ጠቅሰዋል። አየር መንገዱ አሁን ካቆማቸው በረራዎች ጋር በተያያዘም ኪሳራው ከእዚህም የከፋ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል። በተጨማሪም የወጪ ንግድ ዘርፉም በእጅጉ የተዳከመ ሲሆን በተለይም የሀገሪቱን የአበባ እና የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ተቀባይ የነበሩ ሃገራት ምርቶቹን መቀበል ሙሉ በሙሉ በማቆማቸው ዘርፉ መቀዛቀዙን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዘንድሮው ሃገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በተከሰቱት ሁኔታዎች ዙሪያ የራሱን ግምገማ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በእርሳቸው በኩል ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚታለፍ ከሆነ ሀገራዊው ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ቢካሄድ ጥሩ ነው የሚል አቋም እንዳላቸው ጠቁመዋል። ያም ሆኖ አጠቃላይ የመጨረሻ ውሳኔው ብሄራዊ ምርጫ ቦርዱ በሚያቀርበው የጥናት ውጤት ላይ በመመስረትና አስፈላጊውን ውይይት በማድረግ እንደሚተላለፍ አመላክተዋል። ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘም በውጭ ሃገራት ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን መገለል እና ጥቃት ያወገዙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቫይረሱ ቀለም፣ ጾታ እና ሃይማኖት የማይለይ መሆኑን በመገንዘብ ማንኛውም ሰው ከዚህ አይነቱ ድርጊት እንዲቆጠብ አሳስበዋል።
ህገ ወጥ ነጋዴዎችን በተመለከተ እንዲህ አይነት ዓለም አቀፍ ፈተና ሲገጥም ሰው ያለውን የሚያካፍልበት እንጂ ከሌላው የሚዘርፍበት ወቅት መሆን አይገባውም ከማለታቸው ባለፈ ህግን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ግን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የለይቶ ማቆየና የህክምና ቦታዎች ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልሎችም እየተደራጁ መሆኑን አውስተው ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየተገኘ ካለው ድጋፍ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም ከአሊባባው መስራች ጃክ ማ እና ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እንዲሁም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም በመጪው እሁድ ጠዋት የጃክ ማ ፋውንዴሽን ካደረገው የመመርመሪያ መሳሪያ እና የፊት ጭምብል ድጋፍ መካከል የተወሰነ ቁጥር ያለው አዲስ አበባ እንደሚገባ አስረድተዋል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን