ኢትዮጵያ በኮሮና ምክኒያት ሁሉንም ድንበሮቿን ለሰዎች ዝውውር ዘጋች

ኢዜጋ ሪፖርተር

Ethiopia-BorderMarch 23, 2020 (Ezega.com) -- መንግስት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሁሉም የሃገሪቱ ድንበሮች ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ለሰዎች ዝውውር ዝግ መደረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ። የድንበር መዘጋቱ የሎጅስቲክስ አቅርቦት ለማዳረስ የሚደረገውን ተግባር  እንደማያካትትም ተሰምቷል ከዚህ ውጪ ያሉትን ግን ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት በድንበር አካባቢ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ ይገታል ተብሏል። በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የተገመገሙ ሲሆን ማህበረሰቡ ከንክኪ ተራርቆ እንዲንቀሳቀስ የተላለፈው መልዕክት ባለፉት ቀናት በአግባቡ እየተፈጸመ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል። አንደርሳቸው አባባል ባለፉት ቀናት በተለይ ቅዳሜ እና እሁድ በነበሩ የእምነት ተቋማት መርሃ ግብሮች ላይም በቂ የመከላከል እርምጃ እንዳልተወሰደ ተገምግሟል። በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች በቀጣይ ምዕመኖቻቸውን ከማስተማር ባለፈ በተግባር እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ተላልፏል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈ ሰዎችን በአንድ ቦታ የሚያሰባስቡ መጠጥ ቤቶች፣ የምሽት መዝናኛዎች እንዲሁም ጫት ቤቶች አካባቢም በቂ ጥንቃቄ ባለመደረጉ በቀጣይ የፀጥታ ሃይሉ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድም አቅጣጫ ተቀምጧል ተብሏል።

በተጨማሪም የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሰዎችን ንክኪ ለመቀነስ እንደየመስሪያ ቤቶቹ ሁኔታ እየታየ ከፊል ሰራተኞች ከቤታቸው ሆነው ስራቸውን የሚሰሩበት መንገድ እንዲመቻች መግባባት ላይ ተደርሷል ያሉት  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቫይረሱ በኢትዮጵያ እስካሁን በ11 ሰዎች ላይ ብቻ የተገኘ ቢሆንም በቀጣዮቹ ቀናት በመቶዎች ሊያድግ ስለሚችል ሁሉም ሰው ጥንቃቄ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት በሃገር አቀፍ ደረጃ ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ተመድቦ ስራ እየተሰራ መሆኑም ተነግሯል። በቀጣይም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ሃብት የማሰባሰብ ስራው ይቀጥላልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ከዚህ ሌላ የዓለም ባንክ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለመታደግ በፍጥነት 100 ቢሊየን ዶላር መመደብ ካልቻሉ የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ይገባልም ብለዋል። ለዚህም የቡድን 20 አባል ሃገራትን ጨምሮ ከሌሎች ለጋሽ ሃገራትና ተቋማት ጋር በመሪዎች ደረጃ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝም አውስተዋል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ከቫይረሱ ስርጭት ጋር በተያያዘ በርካታ ውሳኔዎችን አስተላልፋለች። ''ቋሚ ሲኖዶስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሠረተ እምነትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ ለሁሉም ካህናትና ለሕዝበ እግዚአብሔር ደኅንነት" ሲባል ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከልም፦

የእርስ በርስ መሳሳም ቀርቶ ራስን ዝቅ በማድረግ እጅ በመንሳት እንዲፈጸም፣ ወረርሽኙ በሰዎች መሰባሰብ የሚስፋፋ ስለሆነ ማናቸውም መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት፣ ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች እና ምዕመናን የሚሳተፉባቸው ታላላቅ መርሐ ግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጡ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ሆነ አሰፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ እጆቻንን በመታጠብና ዘርዘር ብሎ በመቆም ሥርዓተ አምልኮ እንዲፈጸም፣ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በቅዳሴና በማኅሌት ታስበው ክብረ በዓላቱ በሌላ ጊዜ እንዲከበሩ፣ የጉንፋን ምልክት ያለባቸው ለሌሎች እንዳያስተላልፉ በቤታቸው በጥንቃቄ ተለይተው በጸሎትና በሕክምና እንዲቆዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎትም በልዩ ሁኔታ እንዲያገኙ፣ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የተስፋ ልዑክ በመሆን እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተደራጅቶ ተልዕኮውን በአስቸኳይ እንዲጀምር፣ በቤተ መቅደስ ቀዳስያን በሆኑት ልዑካን ብቻ ሥርዓተ ቅዳሴው እንዲፈጸምና ሌሎች አገልጋዮች በቅድስቱ ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያገለግሉ፣ በዕለቱ ለሚቆርቡ ምዕመናን ለአረጋውያን፣ ለወጣቶችና ለሕፃናት የፈረቃ ተራ በማዘጋጀት ቆራቢዎች ብቻ ወደ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያስቀድሱ፣ ሌሎች ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ቢያንስ ሁለት የትልቅ ሰው እርምጃ ያህል በመራራቅ ቆመው እንዲያስቀድሱ፣ የቅዳሴ ጠበል በየግል መጠቀሚያ ምእመናን በየቆሙበት ቦታ በጥንቃቄ እንዲሰጥ የሚሉት ይገኙበታል።

ከዚህ በተጨማሪም ''ወረርሽኙ ከዓለም እንዲጠፋ ካህናት ብቻ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምኅረትና በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ እጣን በማድረስ ማዕጠንት እንዲፈጽሙ ትእዛዝ ያስተላለፈው ቅዱስ ሲኖዶስ ምዕመናንም ራሳቸውን እየጠበቁ በቫይረሱ የተጠቁና አገግመው የወጡ ወገኖችና በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ከሃይማኖትና ከምግባር የወጣ መገለልና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በክርስቲያናዊ ፍቅርና በኢትጵያዊ ጨዋነት እንክብካቤ እንዲያደረጉላቸው አሳስቧል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :