ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዙ የነበሩ 64 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ህይወታቸው አለፈ

ኢዜጋ ሪፖርተር

64-dead-EthiopiansMarch 24, 2020 (Ezega.com) -- ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ በጭነት መኪና በተጫነ ኮንቴነር ውስጥ ሲጓዙ የነበሩ 64 ኢትዮጵያዊያን ህይወት መለፉ ታወቀ። በሞዛምቢክ ምዕራባዊ ግዛት በምትገኘው ቴቴ በተባለችው ክፍለሃገር ውስጥ በተገኘው ተሽከርካሪ ውስጥ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 14 የሚሆኑ ሰዎች በህይወት ተገኝተዋል ተብሏል። የቴቴ ክፍለ ሃገር የጤና ባለስልጣን የሆኑት ካርላ ሞሴ አንደተናገሩት "የሞዛምቢክ የኢሚግሬሽን አገልግሎት ሰራተኞች የጭነት መኪናውን ሞአትዜ በተባለችው የግዛቲቱ ከተማ ውስጥ አስቁመው ሲፈትሹ ነው ሟቾቹን ያገኙት"ብለዋል። ቢቢሲ እንደዘገበው ባለስልጣኗ በጭነት መኪናው ላይ የተሳፈሩት ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸው በምን ምክንያት ሊያልፍ እንደቻለ ምርመራ እየተደረገ ነው ያሉ ሲሆን ነገር ግን አየር በማጣት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።

የሞዛምቢክ ብሔራዊ ኢሚግሬሽን አገልግሎት ቃል አቀባይ የሆኑት አሜሊያ ደሪዬሮ እንደተናገሩት ሟቾቹን ያሳፈረው የጭነት መኪና ሾፌር እንዲቆም ሲጠየቅ ፍላጎት አልነበረውም ብለዋል። ጨምረውም የኢሚግሬሽን ሰራተኞቹ ከመኪናው ውስጥ ድምጽ በመስማታቸው ስደተኞች በውስጡ ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ እንዳረባቸውና እንዲቆም እንዳረጉ ገልጸዋል። ይህ የሞዛምቢክ ክፍለ ግዛት ወደ ደቡብ አፍሪካ በሕገ ወጥ መንገድ ስደተኞች በስፋት የሚዘዋወሩበት አንዱ ቦታ መሆኑ ይታወቃል። በህይወት የተረፉት 14ቱ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንደተደረገላቸው ቃል አቀባይዋ ጨምረው ተናግረዋል።

በተያያዘም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዙ ህይወታቸው ባለፈው ኢትዮጵያውያን ምክኒያት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት እንዳሉት "በርካታ ሰዎች ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዙ ህይወታቸው ማለፉን በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ሆኜ ሰምቻለሁ ከእነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያውንያን እንደሚገኙም ተረድቻለሁ” ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም የሟቾችን ማንነት እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ለማጣራት ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ በደረሰው አሰቃቂ አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ ለሟች ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል። የሟቾቹን ብዛት እና መሰል ዝርዝር መረጃዎች በቀጣይ እንደሚያሳውቅ የገለጸው ሚኒስቴሩ በጉዳዩ ዙሪያ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በሞዛምቢክ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።

ከኮሮና ቫየረስ ወቅታዊ ስርጭት ጎን ለጎን በበርካታ የአፍሪካ መገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ የዋለው ይህ አሰቃቂ ዜና ከተሰማ ጀምሮ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል። ክስተቱን የበለጠ ዘግናኝ ያደረገው ኮነቴነሩ ሲከፈት የነበረውን አሳዛኝ ሁኔታ በምስል ያስቀሩ አካላት ምስሉን በማህበራዊ ትስስር ገጾች መልቀቃቸው ነው። ድርጊቱን የፈጸሙት በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ የሞዛምቢክ ዜጎች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ የተነገረ ሲሆን ምስሉ በተለይ በሟቾቹ ቤተሰቦች ላይ ሊፈጥር የሚችለውን የስነ ልቦና ቀውስ ከግምት በማስገባት ፌስቡክ ምስሉን እንዲያነሳ በርካታ ኢትዮጵያውያን እየጠየቁ ይገኛሉ።  

በሌላ በኩል መረጃው ኢትዮጵያውያኑን በእዚህ መልክ በኮንቴነር ውስጥ በማጓጓዝ ለዘግናኙ ህልፈት የዳረጉት የመኪናው አሽከርካሪና ሌሎች ህገ ወጥ ደላሎች እንዲሁም ተባባሪዎች ስለ መያዝ አለ መያዛቸው ያለው ነገር የለም።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :