ኮሮናና የምጣኔ ሀብት ጠባሳ

በሠላም ዓለሙ

COVID-19March 25, 2020 (Ezega.com) -- ዓለም (ምዕራባዊያኑ) የ2020 አዲስ ዓመታቸውን እንደተመኙት በአዲስ መንፈስና ራዕይ አልተቀበሉትም፡፡ በታህሳስ ወር የምድር የምስቅልቅሏ እጣ ፈንታ ሀ ብሎ ተጀመረ፡፡ የዚህ ክፍለ ዘመን ቀውስ ከወራት በፊት በቻይና ሁቤ ግዛት ሁዋን በተሰኘች ከተማ በተከሰተ ቫይረስ ይሆናል ብሎ የተነበየ አለ ብሎ ደፍሮ መናገር አይቻልም፡፡ በዓለም የጤና ድርጅት ኖቭል ኮሮና (ኮቪድ-19) የሚል ሳይንሳዊ መጠሪያ የተሰጠው ቫይረሱ ወረርሽኝ ሆኗል፡፡ ዛሬ ከ194 በላይ የዓለም አገሮች ላይ የደረሰው ቫይረሱ፤ የዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ እስከወጣበት ድረስ በተገኘ መረጃ 19 ሽህ የሚሆኑ ሠዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡ 424 ሽህ ዜጎችም በዓለም የጤና ድርጅት የጤና ቀውስ ሲባል በተፈረጀው ቫይረስ ተይዘዋል፡፡

ቫይረሱ በተቀሰቀሰበት ሰሞን በርካታ አገሮች ከቻይና ጋር ያላቸውን ግንኙነት የቀነሱ ቢሆንም፣ በዚህ ዓለም አንድ በሆነችበት ዘመን ድንበርን ዘግቶ መቀመጥ ከቫይረሱ ስርጭት የሚያስጥል ሆኖ አልተገኘም፡፡ የቫይረሱ ስርጭት ከተርታው ዜጋ አልፎ የተለያዩ አገራት ባለሥልጣናትን ሳይቀር እያጠቃ ይገኛል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመዋጋት 675 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዚህ ምላሽ የሚሆን የ15 ሚሊዮን ዶላር ልገሳ አድርጓል፡፡

ኮሮና ቫይረስ ከጤና ቀውስነት አልፎ በርካታ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራዎችን እያስከተለ ይገኛል፡፡ በቫይረሱ ስርጭት ሥጋት ምክንያት ዓለም ዓቀፍ ስብሰባዎች፣ ጉባኤዎች፣ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ጨምሮ ትልልቅ ስፖርታዊ ውድድሮችም እየተሰረዙ ይገኛሉ፡፡ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የበርካታ አገራት ምጣኔ ሀብት መንገራገጭ እየገጠመው ነው፡፡ የዓለም የአክስዮን ገበያ በ17 በመቶ ማሽቆልቆል አሳይቷል፤

የነዳጅ ገበያው ከዚያ የተለየ አይደለም፡፡ የቱሪዝም፣ የሆቴል፣ የፊልም ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጽዕኖ ካረፈባቸው ዘርፎች መሀከል ይጠቀሳሉ፡፡ ከአሜሪካ ጥቅል ምርት 7 በመቶ ድርሻ የሚይዘው የቱሪዝም እና መዝናኛ ኢንዱስትሪ በቀደሙት ዓመታት ከነበረው ዕድገት በ10 በመቶ ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ሲ.ኤን.ኤን በዘገባው ገልጿል፡፡ የዓለም ግንባር ቀደሙ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ሆሊውድ ፕሮዳክኖቹ መሰረዝ፣ ሲኒማ ቤቶች መዘጋትና የፊልሞች ምርቃት በመሰረዙ ምክንያት በዚህ ዓመት አምስት ቢሊዮን ዶላር ያጣል ተብሎ ተገምቷል፡፡

ኮሮና እና የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ (ኬዝ) ይፋ ካደረገችበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዳለች፤ በመውሰድም ላይ ነች፡፡ እስከ መጋቢት 15፤ 2012 ዓ/ም ድረስ ከጤና ሚኒስቴር በተገኘ መረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሠዎች ቁጥር 12 ደርሷል፡፡ በሽህዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በለይቶ ማቆያ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ በአገሪቱ ያለው የቫይረሱ ስርጭት በማህበረሱ ድንጋጤን ፈጥሯል፡፡ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ከዋጋቸው በላይ መሸጥን ጨምሮ ህገ ወጥ ተግባራትም ተስተውለዋል፡፡

ኮቪድ 19 ቫይረስ በኢትዮጵያ ጥላውን ያጠላባቸው ዘርፎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ በተለይም የቸገልግሎት ዘርፉ የተጎዳ ሲሆን፤ ሁነቶችን በማሰናዳት የተዋጣት የነበረችው አዲስ አበባ፤ ከፍተኛ ገቢ የምታጣ ይሆናል፡፡ የዚህ ዘርፍ ትልቁ ክፋይና ዋልታ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቫይረሱ ከተስፋፋ በኋላ ወደ 30 አገራት ያደርግ የነበረውን በረራ አቁሟል፡፡ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ባለውለታ ነው የሚባልለት አየር መንገዱ፤ ሠራተኞቹን (ኮንትራት) ለመበተን መገደዱም እየተነገረ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መጋቢት 11 በሰጡት መግለጫ ቫይረሱ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫና ማስከተሉንም አስታውቀዋል። ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አየር መንገዱ በቫይረሱ መቀስቀስ ምክንያት ከ190 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማጣቱን ተናግረዋል። የወጪ ንግድ ዘርፉን በተለይም የአበባ እና የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ተቀባይ አገራት ምርቶቹን መቀበል በማቆማቸው ዘርፉ መቀዛቀዙንም እንዲሁ። የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች የንግድ እንቅስቃሴውን መቀዛቀዝ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የምርት እጥረት እንዲገጥም ሊያደርግ እንደሚችል እያስጠነቀቁ ናቸው፡፡ ይህም የዋጋ ንረትን ያስከትላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል፡፡ በትናንሽ ዘርፎች ላይ የተስተዋለውም ጫና በተለይም ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን የሚጎዳ ነው፡፡ ዜጎች ካለ እቅዳቸው ቫይረሱን ለመከላከል ሲሉ ከቁጠባቸው ገንዘብን በማውጣት ግዥዎችን ይፈፅማሉ፡፡

አገሪቱ ቫይረሱን ለመከላከል የመደበችው አምስት ቢሊዮን ብር የመንግስትን ወጪ ከፍ ያደርጋል፡፡ ይህን ለመሸፈን የሚወሰደው እርምጃ ከሁለት አሀዝ ከፍ ያለውን የዋግ ግሽበት ሊያሳድግ ይችላል የሚል ስጋትንም ደቅኗል፡፡ በሌላ ጎን ገንዘቡ (ለቫይረሱ መከላከያ የተመደበው) ፤ ቫይረሱ ባይከሰት ለሌላ ግልጋሎት ቢውል ሊያስገኝ የሚችለው ጠቀሜታ ትልቅ ነበር፡፡

በአጠቃላይ ኮሮና ቫይረስ በምጣኔ ሀብት ላይ አለመረጋጋትን ፈጥሯል፡፡ መንግስትም በገበያው ላይ ጣልቃ በመግባት ወጪዎችን እያወጣ ነው፡፡ የዘርፉ ባለሞያዎች እንደዚህ አይነት ያልተወጠኑ ወጭዎች ጥቅል ምጣኔ ሀብቱን ያዛባሉ ይላሉ፡፡ ከቅላላ ሀገራዊ ምርቷ (GDP) 50 በመቶ የውጭ እዳ እንደሆነ የሚነገርላት ኢትዮጵያ፤ ቀውሱ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ ብድርና እርዳታን ለማግኘት ያዳግታታል፡፡

ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እና በአፍሪካ የሚያስከትለውን ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ለመቀነስ የሚያስችል ባለ ሶስት ነጥብ የድጋፍ ምክረ ሀሳብ ለቡድን 20 አባል ሀገራት አቅርባለች፡፡ ቫይረሱ በአፍሪካ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል ያለው ምክረ ሀሳቡ፥ በተለይም በዓለም ደረጃ የወጪ ንግድ መጠን መቀነስ፣ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች መንገራገጭ እና የጉዞ እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ክፉኛ መጎዳት እንዲሁም ከኢትዮጵያ አንፃር ከአገሪቱ የአገልግሎት ወጪ ንግድ ውስጥ ሁለት ሶስተኛውን ገቢ የሚያመጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያጋጠመው የበረራ ኢንዱስትሪ መቀዛቀዝ በኢኮኖሚዋ ላይ ስጋትን ደቅኗል ብሏል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ቡድን 20ን 150 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል ብላለች፡፡ የገንዘብ ድጋፉም የውጭ ምንዛሬ አቅምን እና የሴፍቲ ኔት መርሃ ግብሮችን ለማጠናከር የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

ኮሮና በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ሊያሳርፈው የሚችለው ጠባሳ እስካሁን ይህ ነው ተብሎ በአሀዝ ባይገለፅም፤ ከፍተኛ እንደሚሆን ግን ከወዲሁ ተሰግቷል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :