አዳዲሶቹ አምባሳደሮች የተመደቡባቸው ሀገራት ታወቁ
ኢዜጋ ሪፖርተር
March 26, 2020 (Ezega.com) -- በቅርቡ ባልታሰበ ሁኔታ በጠቅላይ ሚንስትሩ ትእዛዝ ከተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ተነስተው በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአምባሳደርነት "የተሾሙ" ባለስልጣናት ጉዳይ በአጅጉ አነጋጋሪ ክስተት ሆኖ ቆይቷል። በተመሳሳይም ሀገሪቱ በተለይ በግብጽ ሱዳንና ቤልጂየም የነበሩ አምባሳደሮቿን እንዲመለሱ ያስተላለፈችው ጥሪም ብዙ ጥያቄዎችን ሲያስነሳ ቆይቷል። የውጭ ጉይ ሚንስቴር በዛሬው እለት ይፋ ያደረገው መረጃም አዳዲሶቹ አምባሳደሮች የተመደቡባቸውን ሀገራት ዝርዝር አሳውቋል። ኢትዮጵያን በተለያዩ ሀገራት የሚወክሉ ናቸው ተበለው "ሹመቱ" የተሰጣቸው 15 ባለስልጣናት ጉዳይ ከተሰማበት ካሳለፍነው የካቲት 24 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ስለ ሚመደቡባቸው ሀገራት በርካታ መላምቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል። ያም ሆኖ የውጭ ጉይ ሚንስቴር ይፋ ያደረገው ምደባ በሚከተለው መሰረት ሆኗል፦
በባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርነት የተመደቡ፦
1. አምባሳደር ብርሁኑ ፀጋዬ- አውስትራሊያ ካንቤራ
2. አምባሳደር ያለም ፀጋይ- ኩባ ሃቫና
3. አምባሳደር ሂሩት ዘመነ- ቤልጄም ብራሰልስ
4. አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ- ግብጽ ካይሮ
5. አምባሳደር ባጫ ጊና- ሞሮኮ ራባት
6. አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ- ሱዳን ካርቱም
7. አምባሳደር ምህረታብ ሙሉጌታ- ኤርትራ አስመራ
8. አምባሳደር ነብያት ጌታቸው - አልጀሪያ አልጀርስ እንዲሁም
9. አምባሳደር ተፈሪ መለስ -እንግሊዝ ለንደን እንዲሰሩ ተመድበዋል።
በአምባሳደርነት የተመደቡ
1. አምባሳደር አድጎ አምሳያ - ስዊድን ስቶክሆልም ምክትል ሚሲዮን መሪ
2. አምባሳደር ጀማል በከር - ባህሬን ማናማ ቆንስል ጄኔራል
3. አምባሳደር አብዱ ያሲን- ሳኡዲ አረቢያ ጄዳ ቆንስል ጄኔራል
4. አምባሳደር ለገሠ ገረመው - ካናዳ ኦታዋ ቆንስል ጄኔራል
5. አምባሳደር እየሩሳሌም አምደማርያም- የተባበሩት አረብ ኢሚሪቶች ዱባይ ቆንስል ጄኔራል
6. አምባሳደር ሽብሩ ማሞ- አሜሪካ ሚኒሶታ ቆንስል ጄኔራል እንዲሰሩ ተመድበዋል።
በዚህም መሰረት አምባሳደሮቹ በተመደቡባቸው ሀገራት የፕሮቶኮል አሰራር መሰረት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቆ በቅርቡ ወደ ምድብ ቦታቸው ተንቀሳቅሰው ስራቸውን በይፋ የሚጀምሩ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋራ በተያያዘ እየተካረረ ከመጣው ውዝግብ አንጻር በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ዲና ሙፍቲ መነሳት አነጋጋሪ የነበረ ሲሆን እርሳቸውን የተኩት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ ካላቸው ልምድ የተነሳ ሳይመደቡ እንዳልቀረ ተገምቷል። ዶ/ር ማርቆስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታነት ከመመደባቸው በፊት በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። በተጨማሪም "በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ" በሚል ቅጽል መጠሪያ የሚታወቁትና በቤልጂየም የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ግሩም አባይ እና በእንግሊዝ የሀገሪቱ አምባሳደር ፍስሀ ሻውል በአዲሱ ምደባ ውስጥ ያለመካተታቸው ቀድሞውንም እንደተጠበቀው ጠቅላይ ሚንስትሩን በዘርፉ እንዲያማክሩ ታስቦ ሊሆን ይችላል የሚለውን ጥርጣሬ አጠናክሮታል። በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚንስተሩ ካቢኔ ውስጥ ብቸኛዋ የህወሃት ተወካይ የነበሩት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚንስትሯ የያለም ጸጋዪ የኩባ ምደባም ሴትየዋን ከ"ስራ" ውጪ ከማድረግ የዘለለ አይደለም የሚሉ አስተያየቶችን አስከትሏል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን