ኢትዮጵያ የግድቡን ውኃ አሞላል የተመለከተውን አዲስ ሰነድ ይፋ አደረገች

ኢዜጋ ሪፖርተር

GERDMarch 30, 2020 (Ezega.com) -- ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በውኃ ለመሙላት የምትከተላቸውን ምዕራፎችና የአሞላል ሒደቶች አስመልክቶ ያዘጋጀችውን አዲስ ሰነድ ይፋ አደረገች። በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በሌሎች ተባባሪዎች ተዘጋጅቶ በሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ ይፋ የተደረገው ሰነድ እንደሚያመለክተው በመጪው ክረምት የመጀመርያው ዙር የመጀመርያ ምዕራፍ ሙሌት የሚከናወን ሲሆን በዚህም ገደቡ4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንዲይዝ ይደረጋል። የዚሁ የመጀመርያው ዙር ሙሌት ሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ በቀጣዩ ክረምት ማለትም በ2013 ዓ.ም. የዝናብ ወቅት ለሁለት ወይም ሦስት ወራት እንደሚከናወንና ግደቡ13.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በዚህ ወቅት እንዲይዝ ተደርጎ የመጀመርያው ዙር ሙሌት እንደሚጠናቀቅ ሰነዱ ያስረዳል። በዚህ ዙር የሚደረገው የውኃ ሙሌት በአጠቃለይ 18.4 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በግድቡ እንዲጠራቀምና የመጀመርያዎቹ ሁለት ተርባይኖች ኃይል እንዲያመነጩ እንዲሁም ሌሎቹ ተርባይኖች ላይ የኃይል ማመንጨት ሙከራ ለማድረግ እንደሚያስችል ሰነዱ ይገልጻል።

በመቀጠል ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌትም በተመመሳሳይ በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ እንደሚከናወን ይህም በግድቡ የሚጠራቀመው የውኃ መጠን 49.3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እስከሚደርስ የሚቀጥል መሆኑን ሰነዱ ያብራራል። በግድቡ የሚጠራቀመው ውኃ 49.3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ሲደርስ የታቀደውን የኃይል ማመንጨት ተግባር ማከናወን እንደሚችልና ሀገሪቱ ይህንን ከሁለት እስከ አምስት ዓመታት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ለመፈጸም ማቀዷን ያስረዳል። በግድቡ የሚጠራቀመው አጠቃላይ የውኃ መጠን 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንደሆነ የሚገልጸው ሰነዱ በሁለተኛው ዙር እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ 49.3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ከተሞላ በኋላ ቀሪው የውኃ መጠን በማንኛውም የዝናብ ወቅት እንዲሞላ እንደሚደረግ ያመልክታል።

የመጀመርያው ዙር የውሃ ሙሌት በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለተኛው ዙር በምዕራፎች የተከፋፈለው ሙሌትም በ2014 ዓ.ም. ክረምት ወቅት እንደሚጀምር ሰነዱ ያስቀምጣል። ሁለተኛው ዙር ሙሌት በሚጀመርበት ወቅት ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 31 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ብቻ ከሆነ ሁለተኛው ዙር ሙሌት ወደ ቀጣዩ ክረምት እንዲተላለፍ እንደሚደረግም ሰነዱ ያመለክታል። ከዚህም ባለፈ በሁሉም ምዕራፍ የሙሌት ሒደቶች የውሃ ሙሌት በሚከናወንበት ወቅት ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብና ከዚያ በታች ከሆነ ደግሞ የመጣው ውኃ ሳይያዝ በተርባይን ውስጥ ኃይል አመንጭቶ በቻ እንዲያልፍ እንደሚደረግ ተመላክቷል። ኢትዮጵያ ይኼንን የውኃ አሞላል ሒደት የቀረፀችው የታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳያደርስ በመጠንቀቅ መሆኑን የሚያመለክተው አዲሱ ሰነድ 'ኢትዮጵያ ራስ ወዳድና ለሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ግድ የሌላት ቢሆን ኖሮ' 49.3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆነውን የውኃ መጠን በሦስት ዓመታት ውስጥ እንዲሞላ ማድረግ ትችል እንደነበርም ይገልጻል።

በሰነዱ እንደተብራራው በግብፅ መንግሥት በኩል የተያዘው አቋምና በሀገሪቱ ሚዲያዎች የተከፈተው ዘመቻ የኢትዮጵያን በውኃው የመጠቀም መብት የሚክድ እንዲሁም ኢትዮጵያ አባል ባልሆነችበት የቅኝ ግዛት ውል እንድትገዛ ለመጫን ያለመ ነው። ያም ሆኖ 'ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብቷ በምንም ዓይነት ምክንያት የማይጣስ' እንደሆነ የሚገልጸው ሰነዱ "የህዳሴ ግድቡና በዓባይ ውኃ የመጠቀም ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሞትና ሽረት" መሆኑንም አመልክቷል። በመሆኑም የህዳሴ ግድቡ የወኃ አሞላል ቴክኒካዊ መረጃዎችን በማምታታት ጉዳዩን ፖለቲካዊ በማድረግ ኢትዮጵያን መጠምዘዝ መቼም ቢሆን ሊሳካ የማይችል ጥረት እንደሆነም ሰነዱ ያመለክታል።

ሪፖርተር በጉዳዩ ዙሪያ አነጋገርኳቸው ያላቸውና ስማቸው ያልተጠቀሰው የዘርፉ ባለሙያዎች በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ይፋ ባደረገው የውኃ አሞላል ምዕራፎችና የሙሌት ሥርዓቶች ሰነድ ላይ 18.4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ በግድቡ ከተያዘ በኋላ ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብና ከዚያ በታች ከሆነ ወሳኙ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት እንደማይጀመር መገለጹ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን ለቀጣይ ተከታታይ ዓመታት 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ቢሆን ሁለተኛው ዙር ሙሌት መቼና እንዴት ሊከናወን እንደሚችል አለመገለጹ ለተቀናቃኝ ወገኖች የውዝግብ በር እንደሚከፍትና ግድቡ ከግማሽ በታች በሆነ አቅሙ እንዲሠራ ወይም ቀድሞ የያዘውን ውኃ ጨርሶ ኃይል ማመንጨት የማይችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሊያደርገው እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :