ኢትዮጵያ በግዛቷ የሚገኝ 600 ኪ.ሜ.ካሬ መሬት ለሱዳን ልትሰጥ መሆኑ ተሰማ
ኢዜጋ ሪፖርተር
April 17, 2020 (Ezega.com) -- የኢትዮጵያ መንግስት ከጎረቤት ሱዳን ጋራ ከሰሞኑ ባደረገው ድርድር ሁለቱ ሀገራት በሚዋሰኑበት ድንበር አካባቢ ለአመታት 'ይገባኛል' በሚል ሲወዛገቡበት የነበረውን ሰፊና ለም የእርሻ መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት መስማማቱን የተለያዩ ምንጮች ዘግበዋል። አሻርቅ አል-አውሳት የተሰኘው የሱዳን ተነባቢ ጋዜጣ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ውሳኔው በሁለት ሳምንታት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል። ጋዜጣው ማንነታቸው እንዲገለጽ ካልፈለጉ እማኞች አገኘሁት ባለው መረጃ ላይ እንደጠቀሰው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀነራል አደም መሀመድ ከሱዳን መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ሲመክሩ ሰንብተዋል። በዚህም መሰረት ሁለቱ ሀገራት ወታደሮቻቸውን ከድንበር አካባቢ ለማስወጣትና ወሰን የማካለል ስራ ለመስራት የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴም ጀምረዋል። ሱዳን በኢትዮጵያ ሰራዊት በሃይል ተይዞብኛል የምትለውና አል-ፋሻቅ በሚል የሰየመችው ለም የእርሻ መሬት በአማራ ክልል በተለይም ጎንደር አካባቢ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል።
ጋዜጣው እንደሚለው ኢትዮጵያ መሬቱ የሱዳን ሉአላዊ ግዛት ለመሆኑ እውቅና እንደምትሰጥ ከዚህ ቀደምም ተቀብላ ቆይታለች። ያም ሆኖ ስፍራውን ለማካለል ፈቃደኛ ሳትሆን በመቅረቷ የአካባቢው ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች መሬቱን ለእርሻ ስራ ሲገለገሉበት ቆይተዋል። ከዚህም አልፎ የሀገሪቱ መከላከያ ሃይል ለአርሶ አደሮቹ ጥበቃና ከለላ እያደረገ ይገኛል። ጋዜጣው ይህንን ይበል እንጂ ስፍራው ከቀድሞም ጀምሮ የኢትዮጵያ ግዛት የነበረ ስለመሆኑ በርካታ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ስፍራው እጅግ ለምና ለተለያዩ የእርሻ ምርቶች ተስማሚ መሆኑን ተከትሎ በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩ ሱዳናውያን በተደጋጋሚ አይናቸውን ሲጥሉበትና አልፎ አልፎም ድንበሩን አልፈው በመግባት በሃይል ለመያዝ ሲሞክሩ ቆይተዋል ተብሏል። አሁን ተደረሰ የተባለውን ስምምነት ተከትሎ የሱዳን የሽግግር መንግስት ይህንኑ ስፍራ ለመቆጣጠር ሰራዊቱን ወደ ስፍራው ማሰማራቱን ጋዜጣው አረጋግጧል።
ከስፍራው እየወጡ ባሉ ያልተረጋገጡ መረጃዎች መሰረት ከሆነ የሱዳን ወታደሮች የተባለው የወሰን ማካለል ከመተግበሩም በፊት ድንበሩን ጥሰው በመግባት መሬቱን እየተቆጣጠሩ ይገኛሉ። ሁኔታው የአካባቢውን አርሶአደሮች ከማፈናቀሉም በላይ በርካታ መኖሪያ ቤቶች እንዲፈርሱ አድርጓል ተብሏል። መረጃው ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ በአማራ ክልል ህዝብ ዘንድ መነጋገሪያ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ቁጣን መቀስቅሱ አልቀረም። በርካቶች መንግስት ህዝቡ በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክኒያት ትኩረቱ መወስዱንና በዚሁ የተነሳ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማክበር እንቅስቃሴው መታገዱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ያስተላለፈው ውሳኔ ነው የሚል አቋም በማንጸባረቅ ላይ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ከሰሞኑ "ፋኖ በሚል ሽፋን በመንቀሳቀስ የህዝቡን ሰላም በማወክ ላይ ነው" ያለው አካል ላይ በተለይ በጎንደርና አካባቢው ከከፈተው ዘመቻ በስተጀርባ የተደረገ ሴራ ነው በሚልም ተቃውሞው አይሏል።
በተጨማሪም መንግስት የተጠቀሰውን ግዙፍና ለም የእርሻ መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የወሰነው ሀገሪቱ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ለያዘችው ኢትዮጵያን የሚደግፍ አቋም እንዲሁም ይህንኑ አቋሟን አጠናክራ በመቀጠል ከኢትዮጵያ ጎን እንድትሰለፍ በማሰብ "በእጅ መንሻነት" ያቀረበው ገጸ-በረከት መሆኑንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት መናገራቸው ተስምቷል። ኢትዮጵያና ሱዳን ከ 1,600 ኪ.ሜ በላይ ርዝመት ያለው ወሰን የሚጋሩ ሀገራት ሲሆኑ በአብዛኞቹ ስፍራዎች ሁለቱን የሚያስማማ የወሰን ማካለል እስካሁን አልተደረገም።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን