ኢትዮጵያ የኬንያን አውሮፕላን በስህተት መትታ መጣሏን አመነች

ኢዜጋ ሪፖርተር

Kenya-Aircraft-downMay 9, 2020 (Ezega.com) -- የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሶማሊያ ውስጥ የኬንያን የጭነት አውሮፕላን መትቶ መጣሉን በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል አሚሶም አረጋገጠ። የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል አባል እንዳልሆነ የተነገረው የኢትዮጵያ ሠራዊት አንድ ክፍል ሶማሊያ ውስጥ አውሮፕላኑን መትቶ የጣለው ከአጥፍቶ ጠፊ ተልዕኮ ጋር ተመሳስሎበት መሆኑን አስታውቋል። በድምሩ አምስት ሰዎችን ጭኖ ሲበር የነበረው የጭነት አውሮፕላን በሶማሊያ ደቡብ ምዕራብ ግዛት ውስጥ ተመቶ የወደቀው ባሳለፍነው ሰኞ ሚያዚያ 26/2012 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ነበር። አውሮፕላኑ ለዩ ስሟ ባርዳሌ በምትባል ከተማ በሚገኝ አየር ማረፊያ አቅራቢያ የተመታ ሲሆን በክስተቱም የሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል። አውሮፕላኑ ተመቶ የወደቀበት ቦታን ተቆጣጥሮ የሚገኘው የአሚሶም ሴክተር ሦስት ኃይል አዛዥ የሆኑት ብርጋዴየር ጀነራል አለሙ አየነ ለቢቢሲ እንዳሉት በአካባቢው ያለው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባላት ስለ በረራው የሚያውቁት ነገር ያልነበረ ከመሆኑም በላይ እና አውሮፕላኑ ለማረፍ የሄደበት አቅጣጫም አጠራጣሪ ነበር።

ኮማንደሩ በአካባቢው በሚገኘው አየር ማረፊያ አንድ አውሮፕላን ለማረፍ የሚሄድበት አቅጣጫ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ መሆኑን ጥቅሰው ይህ በኢትዮጵያ ጦር ተመትቶ የወደቀው አውሮፕላን ግን ለማረፍ ሲሞክር የነበረበት አቅጣጫ በተቃራኒ አቅጣጫ ማለትም ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ስለነበረ ስህተቱ ሊፈጸም ችሏል። ብርጋዴየር ጀነራል አለሙ አየነ በባርዳሌ የጦር ካምፕ ጥበቃ ላይ ያለው ጦራቸው የኬንያውን የጭነት አውሮፕላን መትቶ የጣለበትን ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች በዝርዝር አስረድተዋል። በዚህም መሰረት አንደኛ አውሮፕላኑ ወደ ባርዳሌ ከተማ እንደሚበር መረጃ እንዳልነበራቸው ሁለተኛ አውሮፕላኑ ከተለመደው ውጪ ወደ ምድር ቀርቦ እየበረረ እንደነበር ሶስተኛ ደግሞ በካምፑ የሚገኘው ጦር አውሮፕላኑ ከተለመደው ውጪ ዝቅ ብሎ የሚበረው የአጥፍቶ መጥፋት ዒላማ እየፈለገ እንደሆነ በመጠርጠራቸው የተነሳ መትተው መጣላቸውን አስታውቀዋል።

የሶማሊያ ደቡብ ምዕራብ ምክትል የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሐሳን ሁሴን ለቢቢሲ እንደገለጹት ከአምስቱ ሟቾቹ መካከል ሁለቱ ሶማሊያውያን ሲሆኑ ሦስቱ ደግሞ የኬንያ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ናቸው። ንብረትነቱ የኬንያው አፍሪካን ኤክስፕረስ ኤርዌይስ የሆነው አነስተኛ የጭነት አውሮፕላን አደጋ እንዳጋጠመው በተነገረበት ወቅት በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያው ላይ አደጋው የደረሰው አውሮፕላኑ በኢትዮጵያ ጦር ተመትቶ መውደቁን በመግለጽ ሲቀባበሉት የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል፣ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ አልያም በሶማሊያ መንግስት በኩል ሳይረጋገጥ ቆይቷል። በመጨረሻ ሁሉም ሀገራት የአደጋውን ትክክለኛ ምክኒያት በጋራ ለማጣራት መስማማታቸው የተነገረ ሲሆን በውጤቱም አውሮፕላኑ ለማረፍ ሙከራ ሲያደርግ በኢትዮጵያ መመታቱና መውደቁ ተጠቁሟል። የጭነት አውሮፕላኑ በወቅቱ የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶች የሆኑ መድሃኒቶችንና የወባ መከላከያ አጎበር ጭኖ እንደነበርም ተገልጿል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :