ሱዳን የግድቡ ግንባታ የደኅንነት ሥጋት ስላለበት የውኃ ሙሌቱ መጀመር እንደሌለበት አስታወቀች

ኢዜጋ ሪፖርተር

GERD-fillingMay 19, 2020 (Ezega.com) -- ሱዳን በኢትዮጵያ የህዳሴ ግንባታ ላይ የደኅንነት ሥጋት እንዳላትና ይህ ጉዳይ መፍትሔ ሳያገኝ ኢትዮጵያ የግድቡን የውኃ ሙሌት መጀመር እንደሌለባት አስታውቃለች። ይሄኛው አስገራሚ የሱዳን አዲስ አቋም ፖለቲካዊ አጀንዳ ያነገበ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ተናግረዋል። ሪፖርተር እንደዘገበው ኢትዮጵያ በመጪው ሐምሌ ይጀመራል ያለችውን የግድቡን የውኃ ሙሌት ዕቅድ የያዘ ሰነድ ለታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት (ለሱዳን እና ግብጽ)  ለመላክ ከሰሞኑ ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን ሁለቱ ሀገራት ግን ሰነዱ እንዲላክላቸው እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ ከጠየቁ ታማኝ ምንጭ ተገኘ ብሎ ሪፖርተር እንደዘገበው በኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት የተሰናዳው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል ዕቅድና ሥነ ሥርዓትን ያካተተ ሰነድ ላይ ድርድር ለማድረግ እንዲረዳ በማሰብ ነበር ኢትዮጵያ ለግብፅና ለሱዳን መንግሥታት ሰነዱን ለመላክ ጥያቄ ያቀረበችው። ይሁን እንጂ ሁለቱም ሀገራት ሰነዱ እንዲላክላቸው እንደማይፈልጉ ምላሽ መስጠታቸው ተሰምቷል።

በሱዳን በኩል የቀረበው ምክንያት የግድቡን የውኃ ሙሌት አስመልክቶ የሚደረገው ድርድር እንደ አዲስ መጀመር ሳይሆን ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ሲካሄድ ቆይቶ የተቋረጠው ሂደት ሊቀጥል ይገባል የሚል እንደሆነ የገለጹት ምንጩ የሱዳን መንግሥት ይህንኑ አቋሙን ሰሞኑን በይፋ ማስታወቁን አረጋግጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሱዳን በኢትዮጵያ የህዳሴ ግንባታ ላይ የደኅንነት ሥጋት እንዳላትና ይህም ጉዳይ መፍትሔ ሳያገኝ ኢትዮጵያ የግድቡን የውኃ ሙሌት መጀመር እንደሌለባት ጨምራ አስታውቃለች ተብሏል። በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው እኚሁ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ግን ሱዳን ያነሳቸው ይህ ጥያቄ የግድቡ ግንባታ በተጀመረበት የመጀመርያው ዓመት ላይ የዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን በአንድ ዓመት ጥናቱ የለያቸው የማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች ላይ ተመሥርቶ የተፈጠረ እንደነበር አስረድተዋል። ዓለም አቀፍ ባለሙያዎቹ ከግድቡ የግንባታ ጥራት ደረጃና በሱዳን ላይ ከሚፈጥረው ሥጋት ጋር አያይዘው በወቅቱ የሰጡት መሠረታዊ ምክረ ሐሳብ የኮረቻ ግድቡን የሚመለከት እንደነበርም ግለሰቡ  ገልጸዋል። በወቅቱ የተሰጠው ምክረ ሐሳብ የኮሮቻ ግድቡ የአለት ግንባታ በመሆኑ ግድቡ ውኃ በሚይዝበት ወቅት ውኃ ሊያሰርግ እንደሚችል እና ይህም በሒደት የኮርቻ ግድቡን ሊጎዳ ስለሚችል ከወዲሁ መልስ እንዲሰጠው የሚጠይቅ ነበር ።

በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያ ማስተካከያዎችን ማድረጓ የተበራራ ሲሆን ከተወሰዱት የማስተካከያ ዕርምጃዎች መካከል ለውኃው የሚጋለጠው የኮርቻ ግድቡ ክፍል ውኃ በማያሰርግ የግንባታ ቁስ እንዲሸፈንና ከዚያ በላይ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በኮንክሪት እንዲለበጥ ተደርጎ መልስ ማግኘቱን ገልጸዋል። በመሆኑም በዚህ ያለቀ ጉዳይ ላይ እንደ አዲስ ነገር ከሱዳን የተሰማው ድምፅ ፖለቲካዊ መሆኑ ገልጽ ነው ያሉ ሲሆን ለዚህ ማስረጃው ደግሞ ሱዳን በወቅቱ በተወሰደው መፍትሔ ምክኒያት ሥጋቱ ሙሉ ለሙሉ መቀረፉን ተረድታ ላለፉት ዓመታት አንስታው የማታውቀው ሃሳብ መሆኑ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ግንቦት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰበሰቡት የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት የግድቡን የግንባታ ደረጃና ከዚሁ ጋር የተያያዙ አጠቃላይ ፖለታካዊ ጉዳዮች አስመልክቶ ሰፊ ውይይት መድረጉ ይታወሳል። በዚህ ውይይት መደምደሚያም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀን በተመለከተ በአሜሪካ ‹‹አሸማጋይነት›› ሲካሄድ ቆይቶ ያለ ስምምነት ወደ ተቋረጠው መድረክ እንደማትመለስ ስምምነት ተደርሶ አቋሟ ይፋ ተደርጓል። የዚህን ውይይት አስመልክቶ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ በወቅቱ በሰጡት አስተያየት በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት በግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ሲደረግ የቆየው ድርድር ወደ ስምምነት የማያደርስ በመሆኑ እንደተቋረጠ ገልጸዋል።

በቀጣይ ሊኖር የሚችለው ድርድር በሚመለከታቸው ሦስቱ ሀገራት መካከል ብቻ እንደሚሆን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ከዚህ በተጨማሪ ሦስቱም ሀገራት ተስማምተው የሚቀበሉት አሸማጋይ ካለ በአደራዳሪነት ሊሳተፍ የሚችልበት እድል መኖሩንም ጠቁመዋል። አሸማጋይ የማስገባት ጉዳይ አስፈላጊ ከሆነ ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ወደ አሜሪካ የመሄድ ፍላጎትን እንደማትቀበል ያስታወቁት ሚንስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት ወደ አፍሪካ መመለስ እንደሆነ እና የተሻለ አሸማጋይ ከአፍሪካ ሊመረጥ እንደሚችል አመላክተዋል። በኢትዮጵያ በኩል ለድርድር የተያዘው ቀዳሚ አማራጭ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚካሄደውን የመጀመርያ ዙር የውኃ ሙሌት ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ መወያየት ነው ያሉት ሚንስትሩ ለዚህም የሚረዳ ሰነድ በኢትዮጵያ በኩል ተሰናድቷል ብለው ነበር። ይህንኑ ሰነድ ነው  ሱዳን እና ግብጽ እንዲላክላቸው እንደማይፈልጉ ያስታወቁት ተብሏል። በተለይ የሱዳን አቋም መቀየር በሂደቱ ላይ ስጋት መደቀኑን የሚናገሩት ባለሞያዎች በኢትዮጵያ በኩል ሰነዱን ለሌሎችም የተፋሰሱ ሀገራት በመላክ ጫና ለማሳደር መሞከር እንዳለበት ይመክራሉ።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :