ግብጽ የኢትዮጵያን የድርድር ጥሪ ተቀበለች
ኢዜጋ ሪፖርተር
May 23, 2020 (Ezega.com) -- ግብጽ እየከረረ የመጣውን የህዳሴ ግድብ አለመግባባት ለማርገብ 'ወሳኝ' የተባለለትን ውሳኔ ማሳለፏን አልጀዚራን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳለው "ግብጽ ግድቡን በተመለከተ ፍትሀዊ፣ ሚዛናዊና የሶስቱንም ሀገራት ጥቅም የሚያስከብር ድርድር ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ ናት።" በተጨማሪም በሶስቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው ድርድር የሁሉንም በውሀው የመጠቀም ፍላጎትና መብት ከግምት ማስገባት እንደሚኖርበት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ጠይቋል። ይህ የግብጽ አዲስ አቋም የተሰማው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ከሱዳኑ አቻቸው አብደላ ሀምዶክ ጋራ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ካደረጉት ውይይት በኋላ መሆኑም ተሰምቷል።
ባሳለፍነው ወር ኢትዮጰያ የግድቡን የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት ማለትም 18.4 ሜትር ኪውብ ውሃ ከመጪው ሃምሌ ጀምሮ ማከናወን እንደምትጀምር ማስታወቋን ተከትሎ ግብጽና ሱዳን ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ግብጽ የግድቡ ድርድር ሲካሄድ በነበረባቸው አመታት ሁሉ ግንባታውን በተመለከተ የተለያዩ ተለዋዋጭ ሀሳቦችን በማምጣት ስትቃወም ከመቆየቷ አንጻር የውሃ ሙሌት እቅዱን አምርራ መቃወሟ የሚጠበቅ ነበር። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አቋሟን እየቀያየረች ያለችው ሱዳን የኢትዮጵያን እቅድ በይፋ መቃወሟ ብዙዎችን አስገርሟል። ሁኔታው በሀገራቱ መካከል ያለውን ውጥረት ከመቼውም ግዜ በላይ ከማክረርም አልፎ በተለይ በግብጽና ኢትዮጵያ መካከል ወደ ጦርነት የመግባት ምልክቶች ሲታዩ ሰንብተዋል። ያም ሆኖ ያልተጠበቀው የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መግለጫ ውጥረቱን ረገብ አድርጎታል።
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በግብጽና ኢትዮጵያ መካከል የተፈጠርው ንትርክ በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ድረስ መድረሱ ይታወቃል። የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሹክሪ ከ20 ቀናት ገደማ በፊት ለተቋሙ በጻፉት ደብዳቤ የግድቡ ውሃ ሙሌትና ወደ ስራ መግባት "ከ100 ሚሊዮን የሚሆኑ በአባይ ወንዝ ላይ ጥገኛ የሆኑ ግብጻውያንን የውሃና የምግብ ዋስትና የሚያሳጣና ህልውናቸውንም አደጋ ላይ የሚጥል ነው" ሲሉ መክሰሳቸው ይታወሳል። ከዚህ ባለፈ በጠንካራ ቃላት የተሞላው የሚንስትሩ የክስ ደብዳቤ ችግሩ የማይፈታ ከሆነ ሀገራቱን ወደ ጦርነት ሊያስገባቸው ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያን ማካተቱን አልጀዚራ አረጋግጧል። ለዚህ የግብጽ ወቀሳ ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው "ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት በተመለከተ የግብጽን ይሁንታ ለመጠየቅ የሚያስገድዳት የህግ አግባብ የለም" ብለዋል።
የግብጽ ፍላጎት ኢትዮጵያ ከወራት በፊት በአሜሪካና የአለም ባንክ አደራዳሪነት የተዘጋጀውን ሰነድ እንድትፈርም ሲሆን ኢትዮጵያ በበኩሏ በድርድሩ ፍትሃዊነት ላይ ጥያቄ በማንሳት ከውይይቱ ራሷን መግለሏ ይታወቃል። ሌላኛዋ ተደራዳሪ ሀገር ሱዳን በአብዛኛው የኢትዮጵያን አቋም በመደግፍ ብትዘልቅም ከዩናይትድ ስቴትሱ ድርድር በኋላ ግን የግድቡን የግንባታ ሂደት በተመለከተ አዳዲስ የተቃውሞ ሃሳቦችን ስታቀርብ ተስተውሏል። ለአብነትም ሱዳን የግድቡን የውኃ ሙሌት አስመልክቶ የሚደረገው ድርድር እንደ አዲስ መጀመር ሳይሆን ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ሲካሄድ ቆይቶ የተቋረጠው ሂደት ሊቀጥል ይገባል የሚል የሚል ሃሳብ ስታንጸባርቅ ከመቆየቷም በላይ ሀገሪቱ በኢትዮጵያ የህዳሴ ግንባታ ላይ የደኅንነት ሥጋት እንዳላትና ይህም ጉዳይ መፍትሔ ሳያገኝ ኢትዮጵያ የግድቡን የውኃ ሙሌት መጀመር እንደሌለባት ማሳሰቧ አስገራሚ ሆኖ ቆይቷል።
ያም ሆኖ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ጋራ ውጤታማ የተባለ ውይይት ማድረጋቸው የተዘገበ ሲሆን አብደላ ሀምዶክ ከቀናት በፊት ከግብጽ ባለስልጣናት ጋራ ተመሳሳይ ውይይት ማድረጋቸው ሲታሰብ ለግብጽ ወደ ድርድሩ መመለስ ወሳኙን ሚና መጫወታቸውን መናገር ይቻላል። ያም ሆኖ በሶስቱ ሀገራት መካከል እንደገና ይቀጥላል የተባለው ድርድር ታዛቢና አደራዳሪዎችን ስለማሳተፉ የተባለ ነገር የለም።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን