በአዲስ መልክ የተጀመረው የግድቡ ድርድር በታዛቢዎች ሚና ላይ ውዝግብ ተነሳበት

ኢዜጋ ሪፖርተር

GERD-TalksJune 10, 2020 (Ezega.com) -- ለወራት ተቋርጦ የነበረው እና በአለም ዙሪያ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል ዳግም መካሄድ ጀምሯል። በአዲስ መልክ የተጀመረው የህዳሴው ግድብ ድርድር ደቡብ አፍሪካን፣ የአውሮፓ ሕብረትን እና አሜሪካን በታዛቢነት ማሳተፉ ታውቋል። ይሁን እንጂ በድርድሩ በታዛቢነት የሚሳተፉት አካላት ሚና ምን መሆን ይገባዋል በሚለው ሃሳብ ላይ በተደራዳሪ ሀገራቱ መካከል መግባባት ላይ መድረስ አለመቻሉ ተነግሯል። የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለውና ከሱዳንና ከግብጽ ጋር የተራዘመ ድርድርና ውይይት ሲደረግበት የቆየው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የተመለከተው ድርድር ማክሰኞ ሰኔ 2/2012 ዓ.ም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት በድጋሚ መጀመሩን አረጋግጦ በታዛቢዎቹ ሚና ዙሪያ በተነሳው አለመግባባት ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ እንዳለው "የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ልዩነቶችን በድርድር ለመፍታት ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ዝግጁ ናት" ብሏል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አክሎም ይህ በሦስቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቅ ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሚሆን አመልክቷል ሚኒስቴሩ ይህን ይበል እንጂ ሁለቱ ማለትም ግብጽ እና ሱዳን በጉዳዩ ዙሪያ የየራሳቸውን የተለየ ሃሳብ ማቅረባቸው ተሰምቷል። በሀገራቱ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ የተጀመረው ድርድሩ ቀደም ሲል በ "ታዛቢነት" ከነበረችው አሜሪካ ጋራ አብሮ የነበረውን የአለም ባንክን ያላካተተ ሲሆን በምትኩ ደቡብ አፍሪካን እና የአውሮፓ ሕብረትን በአዳዲስ ተሳታፊነት መዝግቦ ተካሂዷል። በዚህ ከወራት በኋላ በተካሄደው የመጀመሪያ ስብሰባ ተሳታፊ ሀገራቱ ስለ ድርድሩ የአካሄድ ሥነ ሥርዓት፣ ስለ ታዛቢዎች ሚና፣ ስለ ድርድሩ አካሄድ እና ሌሎች ዋና ዋና ያልተቋጩ ጉዳዮች  ላይ  ሰፋ ባለ መልኩ መወያየታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም ተደራዳሪ ሀገራቱ ቁልፍ የድርድር ጉዳዮች ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች በዝርዝር አቅርበው በቀጣይ ቀናት ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ ከስምምነት ደርሰዋል ተብሏል። ያም ሆኑ ግብጽ ድርድሩ በአሜሪካ አሸማጋይነት ከተደረሰው "ስምምነት" ተነስቶ ይቀጥል የሚል ሃሳብ አንጸባርቃለች ኢትዮጵያ በበኩሏ በራሷ በኩል የተዘጋጀ መደራደሪያ ሃሳብ መኖሩን በማስታወስ ድርድሩ ይህንኑ መሰረት አድርጎ መካሄድ አለበት የሚል አቋም መያዟ ተሰምቷል። ሶስተኛዋ ተደራዳሪ ሱዳን ሁለቱን ሀገራት የሚያስታርቅ አዲስ መደራደሪያ እንደምታቀርብ ማስታወቋ ተነግሯል። ከአርብ እና እሁድ ውጪ በሌሎቹ ቀናት ሁሉ ድርድሩ እንዲካሄድ የተስማሙት ሶስቱ ሀገራት በተለይ ስምምነት ባልተደረሰበት እና የድርድሩ ታዛቢዎች ሚናን በሚመለከት በተነሳው አለመግባባት ዙሪያ ላለው ልዩነት ላይ መፍትሄ ለማግኘትና በሌሎች ጉዳዮች ላይም ለመነጋገር ስብሰባው የሚቀጥል ይሆናል ሲሉ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ ስምምነት ላይ በደረሱበት የድርድሩ ሁለተኛ ቀን ውሎ ሀገራቱ በተለይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የወሃ ሙሌት እና ዓመታዊ የውሃ አለቃቅን በተመለከተ ውይይት መካሄዱ ነው የተሰማው። የሶስቱ ሀገራት ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት እና ዓመታዊ አለቃቅ ላይ ብቻ የተወሰነ መሆን አለበት የሚል ጠንካራ አቋም የያዘው የኢትዮጵያው ልኡክ በዚህ ረገድ የሚደረሰው ስምምነት ሀገሪቱ በሚቀጥለው ወር ለማካሄድ ቀን የቆረጠችለትን የግድቡን የውሃ ሙሌት በምንም መልኩ የሚያስተጓጉል እንዲሆን እንደማይፈቅድ አስታውቋል ።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :