ኢትዮጵያውያን ጦርነትን እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ ግብጾች ያውቁታል - ጀነራል ብርሃኑ ጁላ

ኢዜጋ ሪፖርተር

GERDJune 12, 2020 (Ezega.com) -- የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገሩ ህልውና እና ክብር ከመጡበት ሞት የማይፈራ ጀግና ህዝብ መሆኑን አይደለም ግብጽ የአለም ህዝብ ያውቀዋል ሲሉ የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ። ጀነራሉ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋራ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዳሉት የተሳሳተው የመሪዎቿ አስተሳሰብ ግብጽን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳት ይገኛል። የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቭዥን ጣብያ 'ቃል በቃል' ባቀረበው ዘገባ ጀነራሉ ግብጾች ጦርነት ከመጣ ኢትዮጵያውያን እንዴት ጦርነትን መስራት እንደሚችሉ በሚገባ ያውቁታል ማለታቸውን አስታውቋል። ጀነራሉ የጦር መሳሪያ በገፍ መሰብሰብ ብቻ በጦርነት ውስጥ ለድል አያበቃም ያሉ ሲሆን በጦርነት ውስጥ ለድል የሚያበቁ ሳይንሳዊ የሆኑ የጦርነት መሰረታዊያን የሚባሉ ህጎች አሉ እነዚህ የጦርነት መሰረታዊያን ቁልፎች በሙሉ ደግሞ በኢትዮጵያውያን እጅ ናቸው ብለዋል።

ግብጾች ለ30 እና 40 አመታት የሰበሰቧቸው የጦር መሳሪያዎች አሏቸው በእዚህ አስፈራርተውም የጋራ የሆነውን ውሃ እንዳትነኩ ማለትን ይሞክራሉ ያሉት ጀነራል ብርሃኑ ጁላ መሪዎቿ በእዚህ መልኩ ማሰብ አልነበረባቸውም ከማለታቸውም በላይ ግብጻውያን ከኢትዮጵያ ጋር መጣላት ሳይሆን ሀገሪቱን ተንከባክበው መያዝ እና ውሃውን እንዴት አድርገን በጋራ እንጠቀም ማለት ነበረባቸው ብለዋል። ከዚህ ባለፈ ከላይ ያለው እንጂ ከታች ያለው ሀገር ውሃውን መጠቀም አይችልም የሚለው እሳቤ አያስኬድም አለም አቀፍ ህግም አይደግፈውም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ግብጽ አሁን የያዘችው መንገድ ለሀገሪቱ ብዙ ጠላት የሚያፈራባት እና ጠላትነት በጨመረ ቁጥር ደግሞ ውሃውን ሙሉ በሙሉ የእኔ ነው ወደሚል እልህ ውስጥ ይከታል ብለዋል።

ጀነራሉ በንግግራቸው መቼም ቢሆን የግብጽ ሰራዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ እና ምሽግ ሰርቶ የአባይን ገባር ወንዞች አይጠብቅም፣ የኢትዮጵያን ምድርም አይረግጥም ያሉ ሲሆን እነዚህ ወንዞቻችን ከጦርነትም በላይ ታላቅ አቅም እና ጉልበት አላቸው ሲሉ ማስፈራሪያ አዘል ማብራሪያቸውን አሰምተዋል። የግብጽ ፖለቲከኞች፣ ሚዲያዎች፣ ምሁራኑ እና ሌሎች የግብጽ ህዝብ እንዲደነግጥ፣ እንዲፈራ እና ውሃ የሚያጣ እንዲመስለው አድርገው ውሃ የምትለቅለትን ኢትዮጵያን ዘላለም በጠላትነት እንዲመለከት የረጅም ዘመን ሰርተዋል ያሉት ጀነራል ብርሃኑ ዛሬ ችግር ያመጣባቸውም ይሄ ይመስለኛል ብለዋል።

ጨምረውም የፖለቲካ አመራር ማለት የግብጽን ህዝብ ዘላቂ ጥቅም አይቶ ከሌሎች ህዝቦች ጋራ በፍቅር፣ በወንድማማችነት እና በመከባበር አስተሳስሮ ያለ ጦርነት እና ያለ ጠላትነት በጋራ እንዲጠቀም ማድረግ የሚችል ነው ያሉ ሲሆን ብልህ፣ አርቆ አሳቢ እና ለህዝቡ የሚጨነቅ የፖለቲካ መሪ ማድረግ የሚጠበቅበትም ይህንኑ ነው ማለታቸው ተዘግቧል። ከዚህም በተጨማሪ ጠላትን መቀነስ እና ወዳጅን ማብዛት የሚባል ስሌትን ከመከተል ይልቅ መፎከር፣ ሁሉም አማራጭ ጠረጴዛ ላይ ነው ማለት፣ የሀሰት ሪፖርት ጽፎ መበተን እና ግዙፍ የሚዲያ ዘመቻ ከፍቶ ኢትዮጵያን ማጥላላት እና በጠላትነት መፈረጅ ትርጉም የለሽ ነገር ነው ብለዋል የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ።

በሌላ በኩል የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በታላቁ የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል የሚካሔደው ድርድር መቀጠሉን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል። በዚህም ድርድሩ እስከ ሰኔ 04 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ለሦስተኛ ቀን የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት የሚመለከቱ መመሪያዎች እና ሕጎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ታዛቢዎች በተገኙበት በቪዲዮ ውይይት አማካኝነት መካሔዱን ገልጿል። ሐሙስ ዕለት በኢትዮጵያ ሊቀመንበርነት በተካሔደው ውይይት ሀገራቱ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና አተገባበር ላይ ያላቸውን ስጋት አንሥተዋል ያለው መግለጫው በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ውኃውን ስለምትጠቀምበት ሁኔታ ሱዳን ባቀረበችው ምክረ ሐሳብ ላይ መምከራቸውን አስታውቋል። ኢትዮጵያ በሦስቱ ሀገራት መካከል የሚካሔደው የውይይት ሒደት በመልካም አቀራረብ እና ሁሉንም በሚያስማማ መልኩ እንዲከናወን ያላትን ጽኑ አቋም ማስታወቋም ተገልጿል። ሐሙስ ዕለት የተካሔደው ውይይት የታዛቢዎች ሚና ምን መሆን እንዳለበት ውሳኔ የተላለፈበት ነው ያለው መግለጫው በእዚህ ጉዳይ ተላለፈ የተባለውን ዝርዝር ውሳኔ ከመግለጽ ተቆጥቧል። በዕለቱ በሀገራቱ መካከል የተዘጋጁ ዶክመንቶች ልውውጥ መደረጉን ያስታወቀው መግለጫው በሦስቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው ውይይት ሰኔ 06 ቀን 2012 ዓ.ም በሱዳን ሊቀመንበርበት እንደሚቀጥልም ጠቁሟል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :