ኢትዮጵያ ከፀሐይ ግርዶሽ የሚገኝ ከፍተኛ የቱሪስት ገቢ አጣች

ኢዜጋ ሪፖርተር

Solar-Eclipse-EthiopiaJune 19, 2020 (Ezega.com) -- በኢትዮጵያ የፊታችን እሁድ ሰኔ 14, 2012 ዓ.ም እንደሚታይ ከሚጠበቀው ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ጋር በተያያዘ ከዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ይገኝ የነበረ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ በኮቪድ 19 ወረረሽኝ ምክንያት የሚታጣ መሆኑን የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። የፀሐይ ግርዶሹ በእለቱ እንደ ሀገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 12፡50 እስከ ረፋዱ 3፡30 ቆይታ ይኖረዋል የተባለ ሲሆን ይህንኑ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ክስተት ለመመልከት ከ20 ሺህ በላይ የተለያዩ ሀገራት ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ተመዝግበው እንደነበርም የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል። ከተመዘገቡት ጎብኚዎች በተጨማሪም በርካቶች ክስተቱን ለማየት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሚጠበቅ ነበር።

በተለይም በግርዶሹ ምክንያት 90 በመቶ በጨለማ ይዋጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ ስፍራዎች መካከል አንዱ ወደ ሆነው ታሪካዊው የላልይበላ መካነ ቅርስ ለመሄድ ፍላጎት የነበራቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም በኮቪድ 19 ምክንያት ጉዞው መከልከሉን ነው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ የገለጹት። የጸሃይ ግርዶሹን ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በዓለም ዙሪያ የማስተዋወቅ ስራ ሲከናውን መቆየቱን የገለጸው የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ ኢትዮጵያ ሁነቱን ለማየት ከሚመጣ ከእያንዳንዱ ቱሪስት ልታገኝ ትችል የነበረውን ገቢ በወረርሺኙ ምክነያት ማጣቷን ገልጿል።

የአሜሪካው ናሳ ካርታ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ይህ የቀለበት ፀሃይ ግርዶሽ የሚከሰትባቸው በርካታ ቦታዎችን ሲኖሩ በተለይ ሙሉ የቀለበት የፀሃይ ግርዶሽን በንፋስ መውጫ፣ ላሊበላ እና አካባቢዎቹ ማየት እንደሚቻል አረጋግጧል። በሌላ በኩል እንደ አሶሳ፣ ባህር ዳር፣ አዲስ አበባ፣ መቀሌ እና በሌሎችም የአገሪቱ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ ከፊል የሆነውን የፀሃይ ግርዶሽ ማየት ይችላሉ ተብሏል። በተያያዘ ይህ የፀሃይ ግርዶሽ ክስተት በተመሳሳይ ቦታ በድጋሚ የሚከሰተው በአማካይ በ375 ዓመት ውስጥ አንዴ መሆኑን ባለሞያዎች ይናገራሉ። የፊታችን እሁድ ሰኔ 14 ይታያል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ክስተት ታዲያ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በኮንጎ፣ በፓኪስታን እና በህንድ የተወሰኑ ስፍራዎች እንዲሁም በቻይና ይከሰታል ተብሎም ይጠበቃል።

የናሳ መረጃ እንደሚያሳየው የአየር ሁኔታው የሚፈቅድ ከሆነ በእነዚህ አገራት ያሉ የተወሰኑ ህዝቦች በተለይም አጓጊ የሆነውን መሉ የእሳት ቀለበት የሚመስል የጸሀይ ግርዶሽ አስገራሚ የተፈጥሮ ክስተት በሰማይ ላይ ያያሉ። በርካታ አይነት የፀሃይ ግርዶሽ አይነቶች ሲኖሩ በጥቅሉ የፀሃይ ግርዶሽ የሚፈጠረው ጨረቃ በምድር እና በፀሃይ መካከል በመግባት የፀሃይ ብርሃን ወደ ምድር እንዳይደርስ በምትጋርድበት ወቅት ነው። መሬት ፀሃይን እንዲሁም ጨረቃ መሬትን እንደሚሽከረከረሩ የሚታወቅ ሲሆን የእሁዱ የእሳት ቀለበት የሚመስል የፀሃይ የቀለበት ግርዶሽ የሚከሰተው ፀሃይ ለመሬት ቀረብ ስትል በተጨማሪም ሙሉ ጨረቃ ደግሞ ከመሬት ትልቁ ርቀቷ ላይ ስትሆንና እነዚህ የፀሃይ፣ የመሬት እና የጨረቃ የመቀራረብ እና የመራራቅ ክስተቶች ደግሞ በኦርቢት የመሽከርከር ወቅት ሶስቱም በአንድ ቀጥታ መስመር ውስጥ ተሰልፈው ሲገኙ ነው ሲሉ የዘርፉ ባለሞያዎች ያስረዳሉ። በዚህ ቅጽበት ነው ታዲያ ሙሉ ጨረቃ ከምድር ስትርቅ ወይም ወደ ፀሃይ ስትቀርብ ፀሃይን ሙሉ በሙሉ መሸፈን ስለሚያቅታት በጨረቃ የክበብ ዙሪያ የቀለበት ቅርፅ የያዘ የፀሃይ ትርፍ ነጽብራቃዊ አካል የሚታየው ማለት ነው።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :