ኢትዮጵያ ከግብፅ የተሰነዘሩ ከባድ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፏን አስታወቀች

ኢዜጋ ሪፖርተር

Egypt-Ethiopia-CyberattackJune 24, 2020 (Ezega.com) -- በተለያዩ መቀመጫቸዉን ግብፅ ባደረጉ የሳይበር ወንጀለኞች በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ መጠነ ሰፊ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታውቋል። ጥቃቱ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በማስተጓጎል ከፍተኛ ጫና ለመፍጠር ታስቦ ሰኔ 10፣ 12 ፣ 13 እና 14/2012 ዓ.ም በተከታታይ እንደተሰነዘረ ኤጀንሲው አብራርቷል። የሳይበር ጥቃት ሙከራው በተለይ በተጠቀሱት ቀናት በተቀናጀ መልኩ የተቃጣው ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ፣ አኑቢስ ዶት ሃከር እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ በተባሉ የግብጽ የሳይበር አጥቂዎች ቡድን አማካይነት መሆኑን ኤጀንሲው ጨምሮ ገልጿል። ወንጀለኞቹ በጉዳዩ ዙሪያ ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጁ የቆዩ እና ኤጀንሲው ሲከታተላችው የነበሩ መሆኑን የሚያስረዳው መረጃው ተቋማቱ በይበልጥ አርብ ሰኔ 12/2012 እና ቅዳሜ ሰኔ 13/2012 ዓ.ም ከፍተኛ የሚባል የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ማድረጋቸውን በመጥቀስ ይከስሳል።

የሳይበር ጥቃት ሙከራው በሀገሪቱ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የደህንነት መስሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች ድረ-ገጾች ላይ ያነጣጠረ ነበር ያለው ኤጀንሲው ወንጀለኞቹ በተለይ በእነዚህ 2 ቀናት ጊዜ ዉስጥ የ13 የኢትዮጵያ መንግስት ተቋማት እና የ4 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የድረ-ገጽን እንቅስቃሴ በመከታተል ከፍተኛ የማስተጓጎል ሙከራ ማድረጋቸውን ጠቅሷል። በተጨማሪም የሳይበር ጥቃቱ ከተሰነዘረባቸው ተቋማት መካከል አብዛኛዎቹ በድረ-ገጽ ግንባታ ሂደት ደህንነታችውን ታሳቢ ያላደረጉ ድርጅቶች እንዲሁም በቀጣይነት የደህንነት ፍተሻ ያላደረጉ እና ከፍተኛ የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት የነበረባቸው መሆኑንም ኤጀንሲው አረጋግጧል። እንደመረጃው ከሆነ ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ፣ አኑቢስ ዶት ሃከር እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ የተባሉት የሳይበር ጥቃት ፈጻሚ የግብጽ ቡድኖች ለድርጊቱ ሃላፊነቱን የወሰዱ ሲሆን ዋና አላማቸዉም በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በተለይም በቅርቡ ይጀመራል በተባለው የግድቡ የውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ ሁሉን አቀፍ ተጽእኖ በሀገሪቱ ላይ መፍጠር እንደነበር በይፋ መግለጻቸው ተሰምቷል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የወንጀለኞቹን እንቅስቃሴ አስቀድሞ በመከታተል ቅድመ ዝግጅት ባያደርግ እና ይህንን መጠነ ሰፊ የሳይበር ጥቃት በጊዜ መከላከል ባይችል ኖሮ ጥቃቱ በሀገሪቱ ላይ ጉልህ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖሊቲካዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበርም ገልጿል። በመሆኑም ሁኔታውን ቀድሞ በመከላከሉ ሊደርሱ የሚችሉ ከፍተኛ አደጋዎችን ማስወገድ መቻሉን ከግምት በማስገባት ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ ለወደፊቱም

አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ማሳወቁን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በተያያዘ በቀጣይም መሰል ጥቃቶች በስፋት፣ በረቀቀ መንገድ እና ከተለያዩ ስፍራዎች ሊሰነዘሩ እንደሚችሉ አስቀድሞ በመገንዘብ መንግስታዊ ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ሆኑ .የ{et domain}ን ከመጠቀማቸው በፊት የድረ-ገጻቸውን ደህንነት በሚገባ እንዲያረጋግጡ እና ራሳቸውን ከሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት ለመከላከል አስፈላጊውን ተጨማሪ የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲወስዱ ኤጀንሲው በጥብቅ አሳስቧል።

ከዚህ ሌላ ሁሉም ተቋማት ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር ያለባቸውን የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸውን ክፍተቶች በሚገባ መድፈን እንዳለባችው እና የተለያዩ የሳይበር ደህንነት ጥቃት ሙከራ ሲያጋጥማቸውም ሆነ ሙያዊ ድጋፍ ሲያሻቸው ለኤጀንሲው በማሳወቅ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ ተነግሯል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በተለይ ባለፉት ሁለት ቀናት የተቃጡትን የሳይበር ጥቃቶች ለማክሸፍ በተከናወኑ ተግባራት ወቅት ከፍተኛ ትብብር አድርገዋል ያላቸውን ኢትዮ ቴሌኮም፣ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን እና ሌሎች ተቋማትን ለድርጊታቸው ምሰጋናውን አቅርቧል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :