ዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የነበረውን 500 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገደ

ኢዜጋ ሪፖርተር

World-Bank-Ethiopia-AidJune 29, 2020 (Ezega.com) -- የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ለመስጠት አቅዶ የነበረውን የ500 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ ወደ ባንኩ ቦርድ ቀርቦ እንዳይጸድቅ ማገዱ ተሰምቷል። 'ኢትዮጵያ ኢንሳይደር' ከተቋሙ ታማኝ ምንጮች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት የእገዳ ውሳኔውን ያስተላለፉት የዓለም ባንክ ከፍተኛ የስራ አስፈጻሚ አባላት ናቸው። በኢትዮጵያ መንግስት ጠያቂነት ለስምምነት ተዘጋጅቶ የነበረው ይህ የገንዘብ ድጋፍ ለባንኩ የስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀርብ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ለመጪው ሐሙስ ሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ/ም የነበረ መሆኑን እና ባንኩ የገንዘብ ድጋፉን ያገደው በሁለት ምክንያቶች መነሻነት እንደሆነ የተቋሙ ምንጮች ተናግረዋል። የመጀመሪያ ነው ተብሎ በመረጃ ሰጪዎቹ የተጠቀሰው ምክንያት "ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመኗን ለማስተካከል እየሄደችበት ያለው አካሄድ አዝጋሚ ነው" የሚል ነው። ሆኖም ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማስተካከያ እንድታደርግ ተደጋጋሚ ጉትጎታዎችን እና ግፊቶችን ሲያደርግ የቆየው የዓለም አቀፉ የገንዝብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ሆኖ እያለ የዓለም ባንክ ይህን ጉዳይ በምክንያትነት ማንሳቱ "እንግዳ ነገር ከመሆኑም ባሻገር ከተልዕኮው ጋር የማይሄድ" መሆኑን ምንጮቹ አብራርተዋል።

በዓለም ባንክ በሁለተኛ ምክንያትነት የተቀመጠው ደግሞ "በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ ላይ እየተካሄደ ያለው ማሻሻያ በእቅዱ መሰረት እየተከናወነ አይደለም" የሚል ይዘት ያለው እንደሆነ ተገልጿል። በመረጃ አቀባዮቹ እንደተብራራው ባንኩ ባለፈው ህዳር ወር ውስጥ ባወጣው ሰነድ ላይ ይህንን ማሻሻያ የሚደግፈው በዘርፉ ጾታ ተኮር ለውጦች እንዲካተቱ፣ ከዋናው የኃይል መስመር ውጭ ያሉ የኃይል አቅርቦቶች ገበያ እንዲጠናከሩ እና ሀገሪቱ ባላት ሰፊ የታዳሽ ኃይል ሀብት ላይ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ስትሰራ እንደሆነ ገልጾ ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት እየተገበረ ላለው የኢነርጂ ዘርፍ ማሻሻያ የዓለም ባንክ 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ከስምንት ወር በፊት ለንባብ በበቃው ሰነድ ላይ ይፋ ተደርጓል። ጉዳዩን በቅርበት የተከተታሉ የተቋሙ ምንጭ እንደሚሉት "ማሻሻያው ተግባር ላይ ውሎ ሳለ ባንኩ ጉዳዩን የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፉን ለማገድ በምክንያትነት ማስቀመጡ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው" እኚሁ ምንጭ ለሚዲያው በሰጡት ቃልም የአሁኑ የባንኩ እርምጃ "ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ በያዘችው አቋም ላይ ግፊት ለማሳደር ያለመ ሳይሆን አይቀርም" የሚል እምነት አድሮባቸዋል።

የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ባለፈው ሰኔ 11 ቀን2012 ዓ/ም ካካሄዱት ውይይት በኋላ በግል የትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት መልዕክት መሰል ጥርጣሬዎችን አጠናክሯል። ማልፓስ በዚሁ መልዕክታቸው "ኢትዮጵያ እና ጎረቤቶቿ በውሃ ክፍፍል ላይ የሚያደርጉትን ገንቢ ውይይት እና ትብብር ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባቸው" አሳስበዋል።

አሜሪካ በዓለም ባንክ ውስጥ ያላትን ከፍ ያለ ተሰሚነትን ከግምት ውስጥ የሚያስገቡት የተቋሙ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ምንጮች የባንኩ የገንዝብ ድጋፍ እገዳ ውሳኔ ከአሜሪካ አቋም ጋር የሚገናኝ ስለመሆኑ ያብራራሉ። ባንኩ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ከፍተኛ የገንዝብ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ሆኖ ሳላ የአሁኑ የገንዘብ ድጋፍ እገዳ ከዚህ ጋር የሚቃረን መሆኑ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል ተብሏል። ለዚህም በማሳያነት የተጠቀሰው ከማልፓስ የትዊተር መልዕክት አንድ ቀን አስቀድሞ እንኳ ባንኩ "ኢትዮጵያ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የሚደርስባትን የኢኮኖሚ ተጽዕኖ መቋቋም ያስችላት ዘንድ" በሚል የ250 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ማጽደቁ ነው። ከአጠቃላይ ድጋፉ ውስጥ 125 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ በብድር የተሰጠ ቀሪው ደግሞ በእርዳታ የተለገሰ ሲሆን ይህንኑ የብድር ስምምነት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ/ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ማጽደቁ የሚታወስ ነው።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :