የሕዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌት ተጀመረ
ኢዜጋ ሪፖርተር
July 14, 2020 (Ezega.com) -- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሀ መያዝ መጀመሩን ከተለያዩ ምንጮች እንዳረጋገጠ ዋዜማ ራዲዮ ዘግቧል። ቢቢሲ በበኩሉ የከረረ የዲፕሎማሲና የፀጥታ ውዝግብ መንስዔ የሆነው የግድቡ የውሀ ሙሌት በይፋ ስለመጀመሩ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተሰጠ ማረጋገጫ ባይኖርም ከአካባቢው የተገኙ የሳተላይት ምስሎች በግድቡ ውስጥ ያለው የውሃ መጠን መጨመሩን አሳይተዋል ሲል አትቷል። ባለፉት ቀናት ግድቡ ውሀ መያዝ መጀመሩንና ወደ ግድቡ እየገባ ያለው የውሀ መጠንም 4, 400 ሜትር ኪዩብ በሰከንድ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከስር ያለው የመፋሰሻ ቱቦ (Culvert box) ደግሞ 1,700 ሜትር ኪዩብ በሰከንድ ማስተላልፍ ጀምሯል ተብሏል። የውሀ ፍሰቱ በየዕለቱ የተለያየ መጠን እንደሚኖረውና በነሐሴ ወር ከአሁኑ የበለጠ የውሀ መጠን ወደ ግድቡ እንደሚገባም የሜቶዎሮሎጂ ትንበያ ያመለክታል። በእዚህ ሂደት ከቀጠለም ግድቡ በመጀመሪያው ዓመት ሙሌት የታቀደውን 4.9 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ ውሀ መያዝ ይችላል ተብሎ ታምኖበታል።
ከግድቡ አቅራቢያ የተሰበሰቡት አዳዲስ የሳተላይት ምስሎች የተወሰዱት ሰኔ 20/2012 እና ሐምሌ 5/2012 ሲሆን ግድቡ ሁሉም ምስሎች ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን በተከታታይ እየጨመረ መምጣቱን አሳይተዋል። በሌላ በኩል ግድቡ በሚገኝበት በምዕራብ ኢትዮጵያ ጉባ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የክረምት ዝናብ በመጣል ላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምናልባት ግድቡ ከፍተኛ ውሃ መያዝ የጀመረው በእዚህ ምከንያት ይሆናል የሚል ግምት እንዳለው የሳተላይት ምስሎቹን የተከታተለው የክራይስስ ግሩብ ተንታኝ ዊሊያም ዳቪሰን ገልጿል ሲል የግብጹ አል አህራም ጋዜጣ በአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ የተነሱ ሳተላይት ምስሎችን መሰረት አድርጎ ዘግቧል። ግድቡ ውሃ መያዝ የጀመረ መሆኑን ያረጋገጠው ጋዜጣው ይህ ግን በአካባቢው በሚጥለው ከባድ ዝናድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በዝርዝር አስነብቧል። የግድቡ ውሀ መያዝ የሚያስችለው ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ560 ሜትር ላይ መድረሱን በቅርቡ በመንግስት በይፋ የተገለፀ ሲሆን የብረታብረትና መስል ስራዎች ግንባታም ተጠናቋል ተብሏል። በእዚህም የተነሳ ግድቡ አሁን ላይ ውሀ ሳይሞላ መቆየት የማይችልበት ተፈጥሯዊ አስገዳጅ ምክንያቶች መኖራቸውንም ባለሙያዎች ያብራራሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሐምሌ ወር ግድቡን በውሃ መሙላት እንደሚጀምር በተደጋጋሚ የገለፀ ሲሆን በሁለት ተርባይኖች አማካኝነትም የመጀመሪያ የሀይል ማመንጨት ስራው በቀጣዩ ዓመት መገባደጃ ላይ ይጀምራል ሲል ማስታወቁ የሚታወቅ ነው። ግብጽ በበኩሏ ድርጊቱ የውሃ ድርሻዬን ይቀንሳል በሚል ምክኒያት ድርድሩ ሳይጠናቀቅ ሙሌቱ እንዳይካሄድ ስትወተውት ቆይታለች ያም ሆኖ የዘንድሮው የዝናብ ሁኔታ ለግድቡ ሙሌት የሚያስፈልገውን የውሀ መጠን ለማሟላት የተመቸ መሆኑንና ወደታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የሚደርሰው ውሀ ላይ ይህ ነው የሚባል መስተጓጎል ሳይፈጠር ለማከናወን እንደሚቻል ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ። በተያያዘ ዜና በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያ በሱዳንና በግብፅ መካከል ሲደረግ የነበረው የምስለ-ድምፅ የርቀት ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ተሰምቷል። በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት ሲካሄድ የነበረው ይህ የሦስትዮሽ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ አረጋግጠዋል።
እስካሁን በተካሄደው ድርድር መሻሻሎች ቢኖሩም በአጠቃላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ የገለፁት ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለትም አገራቱ የደረሱባቸውን ጉዳዮች ለመሪዎቹ እንዲሁም ሲያሸማግል ለነበረው አፍሪካ ሕብረት በሪፖርት መልክ ያቀርባሉ ብለዋል። ሦስቱ አገራት ሲያደርጉት የነበረው ለዓመታት የዘለቀው ድርድር ያለምንም ውጤት ሲንከባለል መጥቶ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሙሌትን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እጀምራለሁ ማለቷን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ ግብጽ መጠየቋ የሚታወስ ነው። ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት ሸምጋይነት መካሄዱ ለኢትዮጵያ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው የተባለ ሲሆን የግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቅ፣ የድርቅ የውሃ ስሌት፣ የግድቡ አስተዳደርና ቁጥጥር፣ የግድቡ ደኅንነት ጉዳዮችን በተመለከተም የአገራቱ ቴክኒክና ሕግ ባለሙያዎች ለ10 ቀናት እየተወያዩ ነበር ተብሏል። ያም ሆኖ ድርድር ያለ ውጤት ማብቃቱን የግብፁ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰማ ሽኩሪም ማምሻውን ለሀገራቸው ቴሌቭዥን ተናግረዋል።
ዋዜማ ከኢትዮጵያ ወገን አገኘሁት ባለው መረጃ ግብፅ በድርድሩ ለማሳከት ያሰበቻቸውና ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ሌላ ተጨማሪ ግንባታ እንዳታካሂድ የህግ ግዴታ የሚጥል ምክረ ሀሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። የሕዳሴ ግድብ አስተዳደርና ቁጥጥር ላይ የተደረገው ድርድርም የታሰበውን ውጤት አላስገኘም። ግብጽ ድርድሩ ከተሰተጓጎለ ጉዳዩን ወደ መንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት መልሳ ለመውሰድ ፍላጎት ቢኖራትም ከቅርብ አጋሮቿ ጭምር ጉዳዩ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት እንዳይሄድ ተመክራለች ተብሏል። በፀጥታው ምክር ቤት ተደርጎ በነበረው የመጀመሪያ ክርክር ምክር ቤቱ የመሰረተ ልማት ጉዳዮችን ውዝግብ ማየት ከጀመረ ማለቂያ የሌላቸው ጉዳዮች ወደ ድርጅቱ እንደሚመጡና ይህም ከተቋቋመበት ዓላማ ያፈነገጠ መሆኑን ኢትዮጵያ በአምባሳደሯ ታዬ ዐፅቀሥላሤ ያስረዳች ሲሆን የመንግስታቱ ድርጅትም ጉዳዩ በአፍሪቃ ህብረት ሸምጋይነት መታየቱን ደግፎ ከኢትዮጵያ አቋም ጋር ተስማምቷል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን