መንግስት እስረኞቹ ያሉበትን ቦታና ሁኔታ እንዲያሳውቅ አምነስቲ ጠየቀ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Amnesty-International-EthiopiaJuly 19, 2020 (Ezega.com) -- በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ሰዎች ያሉበትን ትክክለኛ ስፍራና ሁኔታ መንግስት በግልጽ ሊያሳውቅ አንደሚገባ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ። በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ቢያንስ 5 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቀሰው የአምነስቲ የዛሬው ሪፖርት ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የት እንዳሉ በማይታወቁበት ሁኔታ ተለይተው መታሰራቸውን አመልክቷል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ጃዋር መሐመድን ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፣ እሰክንድር ነጋን ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፖለቲከኞችን እና የኦ ኤም ኤን ጋዜጠኞችን በስም የዘርዘረው ሪፖርቱ ባለስልጣናት ታሳሪዎቹ ያሉበትን ቦታ ለቤተሰቦቻቸው "በአስቸኳይ በማሳወቅ ክስ እንዲመሰርቱባቸው ካልሆነም በአስቸኳይ እንዲለቀቁ" የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ኃላፊ ዲፕሮስ ሙቼና ጠይቀዋል።

በተለይም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ዋነኛ ባለስልጣናት የት እንዳሉ ለማወቅ እንዳልቻሉ ጠበቆቻቸው እንደተናገሩ የጠቀሰው ሪፖርቱ ሁሉም ማለትም የፌደራል፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች ተጠይቀው ግለሰቦቹ በእነሱ ቁጥጥር ስር እንዳልሆኑ እንደገለጹላቸው አመልክተዋል። "ግለሰቦችን በእስር ለማቆየት የሚቻለው ፖሊስ በታሳሪዎቹ ላይ ጠንካራ ማስረጃ ካለው ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ሰዎች የነጻነት መብታቸው ተገፎ ከታሰሩ በኋላ ፖሊስ ማስረጃ የሚያፈላልግበት አሰራር ተገቢ አይደለም" ብለዋል ዲፕሮስ ሙቼና። አምነስቲ በሪፖርቱ ላይ  "የኢትዮጵያ መንግስት ወደተለመደው የጭቆና መንገድ መመለስ የለበትም ከማለቱም በላይ የሰዎችን የመቃወምና የተለየ የፖለቲካ ሃሳብ የማራመድ መብት ማክበር ይጠበቅበታል" ሲሉ በድርጅቱ የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ኃላፊ አማካኝነት ማሳሰቡን ገልጿል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተከሰተው አለመረጋጋት በአንዳንድ ቦታዎች የብሄርና የሃይማኖት ጥቃት በተሸጋገሩ ተቃውሞዎችና በጸጥታ ኃይሎች ቢያንስ 177 ሰዎች መገደላቸውንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መቁሰላቸውንም በሪፖርቱ አመልክቷል።

በተያያዘ ዜና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦኤምኤን) ጋዜጠኛ ጉዮ ዋሪዮ ዛሬ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የቤተሰቡ አባላት ለቢቢሲ ተናግረዋል። አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከመገደሉ ከአንድ ሳምንት በፊት በኦኤምኤን በተላለፈው ቃለ መጠይቅ ላይ ድምጻዊውን ቃለመጠይቅ ያደረገው ይህ ጋዜጠኛ መሆኑ ይታወሳል። ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር መዋሉን የተናገሩት አንድ የቤተሰቡ አባል እንዳሉት ከሆነ በወቅቱ የጸጥታ አባላቱ ጉዮን ወደ የት ይዘውት እንደሚሄዱ ለመናገር ፍቃደኛ አልነበሩም እኚህ የቤተሰቡ አባል እንደሚሉት "የጸጥታ ኃይሎቹ በመሳሪያ ስላስፈራሯቸው" ተከትለውት መሄድም እንዳልቻሉ ገልፀዋል። ከፀጥታ አባላቱ መካከል አምስቱ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ የደንብ ልብስን የለበሱ ሲሆን አንዱ ደግሞ መደበኛ ልብስ መልበሳቸውን የቤተሰቡ አባል ተናግረዋል። አክለውም ከሃጫሉ ግድያ እና የኦኤም ኤን ቢሮ መዘጋት በኋላ ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው ራቅ ያለ ስፍራ ተሸሽገው እንደነበር ተናግረው ፖሊሶቹ ያሉበትን ፈልገው እንዳገኟቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በሰጠው መግለጫ ድምጻዊው ከኦኤም ኤን ጋር ያደረገው ቃለመጠይቅ የ1 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ርዝመት ቢኖረውም "ሆነ ተብሎ ብሎ አንዳንድ ክፍሎቹን ቆርጦ አውጥቷል" ሲል ተናግሮ ነበር። በኦኤምኤን ላይ ተላለፈው የድምጻዊ ሃጫሉ ቃለ መጠይቅ ጠቅላላ ርዝመት 47 ደቂቃ ብቻ ሲሆን እንደ አቃቤ ሕግ መግለጫ ከሆነ ተቆርጦ የወጣው ቃለመጠይቅ "ድምጻዊው ከኦነግ ሸኔ የሚደርስበትን ዛቻ" የሚገልፀው ክፍል ነበር። በአቃቤ ሕግ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክተሮች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍቃዱ ፀጋ በመግለጫው ወቅት ጠያቂው "ሆነ ብሎ አርቲሰቱን ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር የሚያጋጨውን ነገር እንዲናገር ለማድረግ ግፊት ሲያደርግ ነበር "ማለታቸው የሚታወስ ነው። የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳም ሃጫሉ ሁንዴሳን "ኦኤም ኤን አሳልፎ ሰጠው" ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :