በኢትዮጵያ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ተመዘገበ
ኢዜጋ ሪፖርተር
July 22, 2020 (Ezega.com) -- አገር አቀፍ የዋጋ ግሽበት ቀደም ባሉት ወራት ከነበረበት በማሻቀብ ባሳለፍነው ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 21.6 በመቶ መድረሱን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ። የዋጋ ግሽበቱ ለተከታታይ ወራት ሲጨምር የቆየ ቢሆንም አሁን የተመዘገበው ቁጥር ግን ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመላካች ነው። የፌዴራል መንግሥት በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. በጀመረው አዲሱ የበጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ አሁን የሚታየውን የዋጋ አለመረጋጋት ወደ ነጠላ አኃዝ ወይም ወደ ዘጠኝ በመቶ ለማውረድ እንደሚስራ ከሳምንት በፊት አዲሱን የአገሪቱ በጀት በፓርላማ ባስታወቀበት ወቅት መግለጹ ይታወሳል። ይሁን እንጂ የበጀት ዓመቱ በተጀመረበት በዚህ ወር ያለውን የዋጋ ግሽበት የሚጠቁመው መረጃ እንደሚያሳየው ፈጣን የሆነ የዋጋ ግሽበት አዝማሚያ ከወዲሁ እየተስተዋለ ይገኛል።
የአገሪቱ የሰኔ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በ21.6 ከመቶ ለመጨመሩ ቀዳሚ ምክንያት የሆነው በምግብ ሸቀጦች ላይ የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የበለጠ ኣሻቅቦ ወደ 23.1በመቶ ከፍ በማለቱ ሲሆን በዚህም መሰረት አብዛኞቹ የእህል ዓይነቶችና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸውን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ አስነብቧል። በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የ19.7 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸው ለአጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ መጨመር ሌላው ምክንያት እንደሆነ መረጃው አመልክቷል፡፡ በዚህ ዘርፍ ለታየው የዋጋ ግሽበት ጉልህ ድርሻ ከያዙት መካከል የቤት ኪራይ፣ የቤት እንክብካቤና የማብሰያ ዋጋ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ ትራንስፖርትና ሕክምና ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል። የኮሮና ወረርሽኝ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አመላከቱየስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው ወርኃዊ የሸቀጦች ዋጋ መረጃ እንደሚገልጸው በሰኔ ወር መጨረሻ የተመዘገበው አገር አቀፍ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ21.6 በመቶ መጨመሩንም ገልጿል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በማነፃፀር የሚገኘው ውጤት ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን እንደሚገልጽ የሚያስረዳው መረጃው በሰኔ ወር የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከግንቦት ወር ከነበረው አጠቃላይ የዋጋ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር በ2.9 በመቶ እንደጨመረም አመልክቷል።
በተያያዘ መረጃ የኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋት በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትላቸውን ጫናዎች የተነተኑ ከፈተኛ የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚያደርሰውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች በመንተራስ በሠሩት ጥናት መሠረት በኮሮና ምክንያት ኢኮኖሚው ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ሊያስተናግድ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ አጥኚዎቹ ባወጡት የጥናት ውጤት መሠረት የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል መንግሥት የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ወይም የ114 ቢሊዮን ብር ኢኮኖሚያዊ ድጋፍና ማነቃቂያ በጀት ቢይዝም በመለስተኛና በአስከፊ ደረጃ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመመከት በቂ እንዳልሆነ አስቀምጠዋል፡፡ በመሆኑም ቅደመ ኮሮና ከነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት በመነሳት የበሽታው ሥርጭት ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ለተራዘመ ጊዜ ቢቆይ ኢኮኖሚው እስከ 314 ቢሊዮን ብር የሚገመት ኪሳራ ለማስተናገድ የሚገደድበት ዕድል እንደሚኖርና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለተያዘው በጀት የተገመተው የዘጠኝ በመቶ የኢኮኖሚው ዕድገትም ወደ 0.6 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል ምሁራኑ ግምታቸውን አስቀምጠዋል ሲል ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ ሊከሰቱ የሚችሉት ጉዳቶች እንደ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ይዘታቸው የተለያየ ይዘት እንደሚኖራቸው ያመላከቱት የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ ጥናቱ በብሔራዊ ኢኮኖሚው ላይ ማለትም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያና ከፍጆታ እንዲሁም ከኢንቨስትመንት ጉዳት አንፃር፣ ከፊስካል ማዕቀፍ ወይም ከመንግሥት ገቢና ወጪ አንጻር፣ ከዕዳና በጀት ጉድለት አንፃር፣ ከውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት አንጻር እና ከሌሎቸም መለኪያዎች አንጻር በስፋት ትንታኔ አቅርበውበታል። እ.ኤ.አ. ከ2010/11 እስከ አሁን ድረስ ያለውን ጊዜ መነሻ በማድረግ እ.ኤ.አ. እስከ 2029/30 ያለው ጊዜ ኢኮኖሚያዊ ግምታቸውን ያስቀመጡት ምሁራኑ ወርኃዊ ደመወዝ
ማግኘት ያልቻሉ አባወራዎች ሊደርስባቸው ከሚችለው የገቢ ዕጦትና ኪሳራ፣ በሥራ መቀዛቀዝ ምክንያት ሊከሰት ስለሚችለው ከሥራ የመሰናበት፣ የዓመት ዕረፍት ለመውጣት መገደድ፣ ለይቶ በመቆየት ብሎም በቤት የመቆየትና መሰል ጉዳዮች የሚያስከትሏቸውን ጫናዎችን ሁሉ በማመላከት ሊደርስ የሚችለው ኢኮኖሚያ ጉዳት እስከ ምን ድረስ እንደሚሆን አጥንተዋል፡፡ መንግሥት ጣልቃ በመግባት መሠረታዊና ወሳኝ የሚባሉ ድጋፎች አድርጎም፣ በመለስተኛና በከፍተኛ ደረጃ የሚደርሱ ጉዳቶችን ያመላከቱት ምሁራኑ፣ የሠራተኞች የምርታማነት ዕድገት በመለስተኛ ደረጃ እስከ 2.8 በመቶ ገደማ እንደሚቀንስ ሲጠበቅ፣ በከፍተኛ የጉዳት ደረጃ ከታየ ግን ከ6.4 በመቶ ያላነሰ ቅናሽ ሊያሳይ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
ካፒታል በመለስተኛ ትንበያ የ2.2 በመቶ በከፍተኛ ደረጃ ትንበያ የ2.6 በመቶ ቅናሽ ሊያሳይ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡ ከፍተኛ ቅናሽ እንደሚያሳዩ ከተገመቱትና እያሳዩ ከሚገኙት መካከል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና የውጭ ሐዋላ ገቢ ትልቅ ቦታ ይዘዋል፡፡ በመለስተኛ የጉዳት ግምት ከታየ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የ24 በመቶ ቅናሽ እንደሚያስመዘግብ ሲጠበቅ በከፍተኛ የግምት ስሌት መሠረት የ70 በመቶ ቅናሽ እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል፡፡ በቅርቡ የወጣው የመንግሥት መረጃም የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን የ1.7 ቢሊዮን ዶላር በማስመዝገብ አፈጻጸም ማሳየቱን አጥኚዎቹ አጣቅሰዋል፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም በመለስተኛ ግምት የ25 በመቶ በከፍተኛ የጉዳት ስሌት መጠን የ60 በመቶ ቅናሽ እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ እስከ 25 በመቶ ቅናሽ በመለስተኛ የጉዳት ስሌት ግምት መሠረት የተቀመጠ ሲሆን በከፍተኛ የጉዳት ስሌት መጠን ሲቀመጥ ቅናሹ እስከ 50 በመቶ ሊሰፋ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና በውጭ ገዢዎች ዘንድ እስከ 25 በመቶ የፍላጎት ቅናሽ እንደሚያስተናግድ ሲገመት በመለስተኛ የጉዳት ስሌት ዕይታ ግን ቡና ላይ የሚደርስ የገበያ መቀዛቀዝ እንደማይኖር ምሁራኑ ተንብየዋል፡፡ የገቢ ንግድ ላይም ከከፍተኛ የጉዳት ትንበያ አኳያ እስከ 25 በመቶ የሚደርስ የአገር ውስጥ የፍላጎት ቅናሽ እንደሚኖር ገምተዋል፡፡
እንዲህ ያሉ መላምቶችን ዋቢ ያደረገው የምሁራኑ የጥናት ሪፖርት እ.ኤ.አ. በ2019/20 እንዲሁም በ2020/21 በጀት ዓመት የአጭር ጊዜ የተፅዕኖ ስሌት መሠረት የኮሮና ቫይረስ ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ በሚኖረው ቆይታ የኢኮኖሚው ዕድገት ቅድመ ኮሮና እ.ኤ.አ. በ2019/2020 እንደሚኖረው ይታሰብ ከነበረው የዘጠኝ በመቶ ዕድገት ወደ 5.9 በመቶ እንዲሁም በ2020/2021 የ6.7 በመቶ ዕድገት እንደሚያሳይ ተገምቷል፡፡ ይህም በመለስተኛ የጉዳት መጠን የተቀመጠው ሲሆን ሊደርስ የሚችለው የጉዳት መጠን በገንዘብ ሲተመን ከ127 ቢሊዮን ብር እስከ 159 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ በከፍተኛ የጉዳት መጠን ሲሰላ የኢኮኖሚው ዕድገት ከሚጠበቀው የዘጠኝ በመቶ በ2020/2021 ወደ 0.6 በመቶ እንደሚያዘቀዝቅ በዚህም እስከ 314 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበርን ሐሳብ አይወክልም የተባለውንና "የኮሮና መጠነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት፣ ፖሊሲና የማገገሚያ አማራጮች" በሚል ርዕስ ይፋ የተደረገውን ጥናት የማኅበሩ ሦስት አባላት እንዳጠኑት በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ታደለ ፈረደ (ዶ/ር)፣ ማኅበሩን በቅርቡ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት መምራት የጀመሩትና የግብርና ሚኒስርቴር አማካሪው ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) ከዓለም ባንክ አማካሪዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ሞዴሊንግ ባለሙያዋ ሉሊት ምትክ ጋር የተጣመሩበት ይህው የፖሊሲ ጥናት ውጤት ለሙያዊ ግምገማ ቀርቦ እንደሚመከርበት ይጠበቃል፡፡
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን