የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት ተጠናቀቀ

ኢዜጋ ሪፖርተር

GERD-first-fillingJuly 22, 2020 (Ezega.com) -- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደ ታሪካዊ ምእራፍ በመሸጋገር ለመጀመሪያ ዙር የታቀደለትን 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ሙሉ ለሙሉ መያዙ ተነገረ። ምንም እንኳን በአጠቃላይ ግድቡ ከሚያስፈልገው ከ74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ አንጻር ሲታይ ሙሌቱ እጅግ ብዙ የሚቀረው ቢሆንም ለመጪዎቹ የውሃ ሙሌት ተግባራት ወሳኝ ኩነት መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል። የጠቅላይ ሚንሰትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ እንደተገለጸው በዚህ ክረምት ባለው መልካም የዝናብ ሁኔታ ታግዞ በመጀመሪያው ዓመት ለመያዝ የታቀደው የውሃ መጠን ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ ተጠናቆ ውሃው በግድቡ አናት ላይ መፍሰስ ጀምሯል። ይህንኑ የሚያሳየው የተንቀሳቃሽ ምስል በተለያዩ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች መታየቱን ተከትሎም በርካቶች ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴና ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራልና የመንግስት ባለስልጣናትም የደስታ መግለጫ መልእክቶችን ሲያስተላልፉ ውለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በ‘እንኳን ደስ አላችሁ’ መልዕክታቸው "ስኬቱ ኢትዮጵያውያን ዳግም ሀገር ተኮር ስራ ሰርቶ እንዴት ማሳካት እንደሚቻል ያረጋገጡበት መሆኑን ገልጸው "ይበልጥ የሚያስደስተው ማንም ባልተማመነብን ወቅት በራሳችን ዐቅም ላይ ዕምነት ኖሮን ማሳካት መቻላችን ነው ሕዳሴ ግድባችን የዚህ ትውልድ መለያ ማኅተምና ሰርቶ የማሳካት ትእምርት ነው" ብለዋል። የግድቡ ሙሌት "አንገታችንን ሊያስደፉ ሲከጅሉ ለነበሩት ሁሉ የጫኑብንን የድህነትና የኋላቀርነት ሸክም ወዲያ ልናሽቀነጥር መቁረጣችንን ጮክ ብለን የምንናገርበት ድምጻችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት ቢጠናቀቅም ቀሪ የቤት ስራዎች መኖራቸውንና የዲፕሎማሲ ስራዎችና ኃይል የማመንጨት ተግባር እንደሚቀር አመልክተዋል። ከዚህም ሌላ ግድቡ በደለል ምክንያት ሙሉ ጥቅም ከመስጠት እንዳይስተጓጎል የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ በስኬት ማጠናቀቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይህንን ኩነት በማስመልከት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ደግሞ ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ አስፈላጊ ነው ላለችው ዓላማ ልትጠቀምበት እንደምትችል አመልክተዋል። "አባይ ወንዝ ነበር ተገርቶ ወንዝም ሐይቅም ሆነ" ያሉት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ "ከእንግዲህ በወንዝነቱ ይፈሳል፣ በሐይቅነቱ ኢትዮጵያ ለፈለገችው ልማት ሁሉ ለመዋል እጅ ሰጥቷል እውነትም አባይ የእኛ ሆነ!!" ሲሉ ጽፈዋል። የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚ/ሩ ስለሺ በቀለም የእንኳን ደስ ያለን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። እርሳቸው እንዳሉት ትናንት ምሽት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለአመቱ "የሚያስፈልገውን 4.9 ቢ.ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ ከግድቡ አናት ላይ ፈሷል ይህም የተሳካው ወደታችኛው ተፋሰስ ሀጋራት የሚሄደው ውሃ ሳይቋረጥ ነው።" ዶ/ር ስለሺ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ "ይህ ውጤት ዋነኛ ምዕራፍ ነው፣ ይህ በግድቡ የተያዘው ውሃ በመጪው ዓመት በሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ያስችለናል፤ ግንባታችንም ይቀጥላል" ብለዋል። ከመልዕክታቸው በተጨማሪ በትዊተር ገጻቸው ላይ ግድቡ ከመሞላቱ በፊት እና ከተሞላ በኋላ ያለውን ሁኔታ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ያጋሩት ሚኒስትር ስለሺ ትናንት ምሽት የተደረገው የመሪዎች ውይይትም "የሰከነና ጥሩ መግባባት የታየበት ነበር" ብለዋል። ስምምነት ባልተደረሰባቸው የቴክኒክና የሕግ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ በቀጣይ ጉዳዮች አካሄድ ስምምነት ተደርጓል ያሉት ኢ/ር ስለሺ በዚህም መሰረት "የሁሉም ደረጃ ውሃ ሙሌት በአጭር ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ስምምነት ላይ እንዲደረስ፣ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የሆነ ስምምነት የውሃ አጠቃቀምን ጨምሮ በወደፊት ድርድሮች እንዲቋጩ መሪዎቹ ወስነዋል" ብለዋል።

ከትናንቱ ውይይት ጋር በተያያዘ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳም የተካሄደው ውይይት ውጤታማ እንደነበረ ያረጋገጡ ሲሆን የሦስቱ አገራት ውይይት ይቀጥላል ብለዋል። የአፍሪካዊያንን ችግር በአፍሪካ መፍትሄ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት በስበሰባው የተሳተፉትን አካላት ሁሉ ፕሬዝዳንት በመልእክታቸው አመስግነዋል። በተመሳሳይ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንሰትር አብደላ ሃምዱክም የተደረገው ውይይት ስኬታማ እንደነበረ ገልጸው ግድቡ የሚሞላበትን እና የሥራውን ሂደት በተመለከተ ድርድሮች እንዲቀጥሉ ተግባብተናል ብለዋል። የግብጹ አሃረም ኦላይን በበኩሉ የፕሬዝደንት አል-ሲሲን ቢሮ ጠቅሶ እንደዘገበው ግብጽ ከኢትዮጵያ እና ከሱዳን ጋር ግድቡ የሚሞላበት እና የግድቡን አሰራር በተመለከተ ከስምምነት ለመድረስ ተስማምታለች ብሏል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :