በኦሮሚያ የተፈጸመው ድርጊት የዘር ማጽዳት ገጽታ ያለው ነው - አለም አቀፍ ሪፖርት
ኢዜጋ ሪፖርተር
July 23, 2020 (Ezega.com) -- አለም አቀፉ የአናሳ ህዝቦች መብት ቡድን በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተፈጸመውን ግድያ፣ የአካል ማጉደልና የንብረት ማውደም ድርጊት በማውገዝ መግለጫ አውጥቷል። ድርጊቱ "በክልሉ በሚኖሩ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ህዝቦች በተለይም በአማራና ጉራጌ ብሄር ተወላጆች ላይ የተፈጸመ የዘር ማጽዳት ወንጀል ነው" ያለው ተቋሙ ሁኔታው የኦሮሞ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ምክኒያት አድርጎ መቀስቀሱን አስታውቋል። ከአርቲስቱ ሞት በኋላ በብዙ ቁጥር የተደራጁ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ወጣቶች በክልሉ የሚኖሩ አናሳ ቁጥር ያላቸውን የሌላ ብሄር ሰዎች ገድለዋል፣ በእነዚሁ ግለሰቦች ባለቤትነት የተቋቋሙ ሆቴሎችን፣ ት/ቤቶችን፣ የንግድ ተቋማትንና መኖሪያ ቤቶችን አቃጥለዋል ያለው ሪፖርቱ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ ኦሮሞዎች ያፈሯቸው ንብረቶች የተጎዱበት ሁኔታም አለ ብሏል። ተቋሙ የተፈጸመው ድርጊት የዘር ማጽዳት ገጽታ እንዳለው ያስረዳሉ ያላቸውን ነጥቦችም ዘርዝሯል በእዚህም መሰረት፦
1ኛ ጥቃቶቹ ቀድሞ የታቀዱ ናቸው
"ድርጊቱን የፈጸሙት ሰዎች ኢላማ ውስጥ የገቡ ሰዎችን ስም ዝርዝር በመያዝና በየቤቱ እየዞሩ መታወቂያ በማየት በተለይም የአማራና ጉራጌ ህዝቦችን አጥቅተዋል። ከዚህም ሌላ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በአብዛኛው የአካባቢው ነዋሪዎች ያልሆኑ ሲሆን ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበት ትራንስፖርት ጭምር ተመቻችቶላቸዋል።"
2ኛ የክልሉና የፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት ድርጊቱን እንዳላየ አልፈውታል
"በአብዛኛዎቹ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የፌደራሉም ሆነ የክልሉ መንግስት የስራ ሃላፊዎች የጸጥታ ሃይሎችን ለማሰማራትና ተጠቂዎቹን ከጥቃት ለማዳን ፈቃደኞች አልነበሩም። ይባስ ብሎ ተጎጂዎች ሲጣሩ ጣልቃ የመግባት ስልጣን የለንም የሚሉት እነዚህ አካላት ተጠቂዎቹ ራሳቸውን ለመከላከል ሲሞክሩ ግን በክልሉ ልዩ ሃይል እርምጃ እንዲወሰድባቸው አድርገዋል።"
3ኛ መገናኛ ብዙሃን የጥላቻ ንግግርና ግጭት ቀስቃሽ መልእክቶችን አስተላልፈዋል
"በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙሃን ጥቃቶቹን ሲያባብሱና ወንጀሎኞቹን በመረጃ ሲደግፉ ታይቷል። በተለይም ከአሜሪካዋ ሚኒሶታ የሚሰራጨው ኦ ኤም ኤን የተባለው የቴሌቭዥን ጣቢያ የተደራጁት አጥፊዎች የአማራ ብሄር ተወላጅ ንብረቶችን እንዲያቃጥሉ ተከታታይ ቅስቀሳ ሲያደርግ ቆይቷል።"
4ኛ ግድያና ረብሻው በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ነው
"ገዳዮቹ የሟች አማራና ጉራጌ አስከሬኖችን በየጎዳናዎች ላይ በማውጣት ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።"
አለም አቀፉ የአናሳ ህዝቦች መብት ቡድን በኢትዮጵያ መልሶ የተከፈተውን የኢንተርኔት አገልግሎት በመጠቀም በድርጊቱ ዙሪያ ተጨማሪ ክትትልና ጥናት የሚያደርግ መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን እስካሁን ባገኛቸው ሪፖርቶች መሰረት ግን የሚመለከታቸው አካላት የሚከተሉትን ተግባራት እንዲፈጽሙ አሳስቧል፦
1ኛ የኢትዮጵያ መንግስት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአሁኑ ወቅት በኮቪድ 19 ቫይረስ እየተጋለጡ ላሉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች አፋጣኝ የደህንነት ከለላና ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርግ፣ ገለልተኛና ነጻ ቡድን አቋቁሞ የተፈጸመውን ወንጀል በማጣራት አጥፊዎችን ለህግ እንዲያቀርብ በተጨማሪም ህጋዊና ተቋማዊ ሪፎርሞችን በመቅረጽ በሀገሪቱ ያሉ አናሳ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች ደህንነት እንዲያረጋግጥ
2ኛ የአሜሪካ ባለስልጣናት በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው በኦ ኤም ኤን የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችንና በጉራጌ፣ በአማራና በሌሎች በኦሮሚያ ክልል ነዋሪ የሆኑ አናሳ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የሚቀሰቅሱ መልእክቶችን እንዲያስቆሙ
3ኛ ፌስቡክ፣ ትዊተርና ሌሎችም የማህበራዊ ትስስር ገጾች በኢትዮጵያ ያሉ አናሳ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የሚተላለፉ መልእክቶችን በንቃት በመከታተል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ
4ኛ የተባበሩት መንግስታት በሁከቱ ዙሪያ መጠነ ሰፊ ምርመራ በማድረግና የነገሩን መነሻ በማጣራት ምክረ ሃሳብ የታከለበት ሪፖርት እንዲያቀርብ
5ኛ የሀገሪቱን የጸጥታ ተቋም የሰው ሃይል የሚያሰለጥኑ ሀገራትም የስልጠና መንገዶችንና ይዘት በመከለስ የጸጥታ ሃይሉ ተመሳሳይ የዘር ማጽዳት ወንጀሎችን መከላከል እንዲችል እንዲያደርጉ ጠይቋል።
ለሳምንታት ተዘግቶ የቆየው የኢንተርኔት አገልግሎት በዛሬው እለት መከፈቱን ተከትሎ ይህንን በአለም አቀፉ የአናሳ ህዝቦች መብት ቡድን የቀረበውን ዝርዝር መረጃ ብዙዎቹ እየተጋሩትና እየተነጋገሩበት ሲሆን በመንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን