ግብጽ በቀጠናው የጦር ሰፈር እንዳታቋቁም ኢትዮጵያ አስጠነቀቀች

ኢዜጋ ሪፖርተር

Egypt-militaryJuly 29, 2020 (Ezega.com) -- ግብጽ በምስራቅ አፍሪካ የጦር ሰፈር በማቋቋም የቀጠናውን ሰላም ለማደፍረስ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንድታቆም ኢትዮጵያ እንዳስጠነቀቀች ዴይሊ ኔሽን ዘግቧል፡፡ ከ4 ቀናት በፊት ከፍተኛ ባለስልጣናትን የያዘ የግብጽ የልዑካን ቡድን ከሶማሌላንድ ግዛት አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ ጋራ በሀርጌሳ ተገናኝቶ መወያያቱ ይታወሳል፡፡ ዋናው የውይይቱ ማጠንጠኛም ግብጽ በራስ ገዟ አስተዳደር ክልል ውስጥ የጦር ሰፈር ለማቋቋም በምትችልበት ሁኔታ ዙሪያ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን የግብጽን እቅድ ተከትሎ ነው ማስጠንቀቂያውን ያወጣችው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኔሽን እንደተናገሩት ምንም እንኳን ግብጽ እንደ አንድ ሉዐላዊ አገር ከየትኛውም የቀጠናው አገር ጋር ግንኙነት የመመስረት መብት ቢኖራትም ይሄንን ስታደርግ ግን ሌሎች አገራትን በሚጎዳ መልኩ መሆን የለበትም ያ ሳይሆን ቀርቶ የግብጽ ድርጊት ሌላ 3ኛ አገር ላይ ስጋት ከፈጠረ ተቀባይነት የለውም፡፡  

ሶማሌላንድ የግብጽን ጥያቄ መቀበል አለመቀበሏን በተመለከተ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም ያም ሆኖ ተወያዮቹ በካይሮና ሃርጌሳ አገናኝ ቢሮዎችን ለመክፈት ተስማምተዋል የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት የሰጡት አምባሳደር ዲና ታዲያ በውይይቱ ስለተደረሰባቸው ስምምነቶች ጠንካራ መረጃዎች አለማግኘታቸውን ጠቅሰው ግንኙነቱ ኢትዮጵያንና ሌሎች ጎረቤት አገራትን የሚገዳ እንደማይሆን ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሶማሌላንድን ጨምሮ ከአብዛኛዎቹ ጎረቤቶቿ ጋር መልካም ግንኙነት አላት ያሉት ቃል አቀባዩ በሁለቱ አካላት የተደረሰው ስምምነት ሌሎችን የሚጎዳ ከሆነ ግን ህገወጥና ዓለም አቀፍ የሰላምና ደሀንነት መመሪያዎችን የጣሰ እንደሚሆንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡ የግብጽ ባለስልጣናት በሀርጌሳ ያደረጉትን ቆይታ ተከተሎ በገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሺዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክም በሶማሌላንድ ተመሳሳይ ጉበኝት አድርገዋል፡፡

ነገር ግን ጉብኝቱ ከግብጽ ድርጊት ጋር የሚገናኝ እንዳልሆነ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡ ይህ የተለመደና ታቅዶ የሚከናወን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከሪያ ጉብኝት ነው ያሉት አምባሳደር ዲና በእዚህ ዙሪያ የሚናፈሱት ወሬዎች መሰረተ ቢስ ናቸው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁን ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ዕውን ማድረጓን ተከትሎ ግብጽ በቀጠናው የጦር ሰፈር ለማቋቋም የምታደርገውን እንቅስቃሴ ማጠናከሯን ታዛቢዎች መናገራቸውን ኔሽን ዘግቧል፡፡ ባሳለፍነው ወር ግብጽ ተመሳሳይ የጦር ሰፈር በደቡብ ሱዳን ለመገንባት ተስማምታለች የሚል መረጃ በስፋት ወጥቶ በደቡብ ሱዳን  ውድቅ መደረጉን ጋዜጣው አስታውቋል፡፡

በሌላ ዜና የግብጽ ጦር የገዛቸውን 5 ሩሲያ ሰራሽ ዘመናዊ የጦር ጄቶችን መረከቡን ሚድል ኢስት ሞኒተር አስነብቧል፡፡ Su-35 የተሰኙት 5 ጄቶች ከ 9210-9214 የሚል ኮድ ለጥፈው ከሩሲያ ወደ ግብጽ ሲበሩ የሚያሳዩ ፎቶዎች መውጣታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡ ባሳለፍነው አመት ግብጽ እነዚህን ሩሲያ ሰራሽ የጦር ጄቶች ለመግዛት ባቀደችበት ወቅት አሜሪካ ተቃውሞዋን ያሰማች ሲሆን ግብጽ እቅዱን ካልሰረዘች ጠንከር ያለ ማዕቀብ እንደሚጣልባትም አስጠንቅቃ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግብጽ ይህንን የአሜሪካን ማስፈራሪያ ወደ ጎን በመተው በ2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ከሩሲያ ለመግዛት ካዘዘቻቸው ከ20 በላይ Su-35 የጦር ጄቶች 5ቱን መቀበሏን ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :