ኢትዮጵያ በግድቡ ጉዳይ ከስምምነት ለመድረስ ጊዜ እያለቀባት ነው - የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ኢዜጋ ሪፖርተር
August 5, 2020 (Ezega.com) -- ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብጽና ሱዳን ጋራ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ጊዜው እያለቀባት ነው ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስጠንቀቁን ብሉምበርግ አስንብቧል። ሚኒስቴሩ ለጋዜጣው በኢሜል በላከው መልእክት እንዳሰፈረው ጊዜው አጭር ነው በግድቡ ጉዳይ እየተካሄደ ያለው ድርድር ግን በሚፈለገው ፍጥነት እየተጓዘ አይደለም ከዚህ አንጻር በሀገራቱ መካከል አንዳች ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለው እድል እየጠበበ ነው ብሏል። በሶስቱ አገራት መካከል የሚደረግን ገንቢና ፍሬያማ ንግግር እናበረታታለን የሚለው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁሉም አገራት ተመሳሳይ ቁርጠኝነት ማሳየት ከቻሉ ግን ሶስቱንም ያማከለና አገራዊ ጥቅሞቻቸውን ከግምት ያስገባ ስምምነት ላይ መድረስ የሚቻልበት እድል መኖሩን ጠቁሟል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው አመት በግብጽ ጥያቄ መሰረት ሶስቱን አገራት ለማደራደር ወስነው ድርድሩ መካሄዱን ያስታወሰው ብሉምበርግ እርሱም ሆነ በቅርቡ በአፍሪካ ህብረት ታዛቢነት የተጀመረው ድርድር ውጤት አላስገኘም ይላል። ያም ሆኖ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ጊዜ እያለቀባት ነው ከማለት ውጭ ድርድሩ ባይሳካ አሜሪካ ልትወስድ ስለምትችለው እርምጃ ያለው ነገር ስለመኖሩ የተሰጠ መረጃ የለም።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በሶስቱ አገራት መካከል እየተደረገ ባለው ድርድር ላይ የበኩሏን የግድብ ሙሌት ደንብ ማቅረቧ ተሰምቷል። በሱዳን ጥያቄ መሰረት ለቀናት ተራዝሞ የነበረው የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች የተሳተፉበት የሶስትዮሽ ድርድር በቪዲዮ ኮንፍረንስ በመታገዝ በትናንትናው እለት መካሄድ መጀመሩ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ታዲያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የውሃ ሚኒስትሮች በትናንትናው እለት በሰጡት መመሪያ መሰረት የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ የህግ እና የቴክኒክ ቡድኖች የድርድር ስብሰባቸውን በዛሬው እለት ቀጥለው ማካሄዳቸውን አስታውቋል። በድርድሩ ላይም የደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካ ታዛቢዎች እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የመደባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል ሲል መረጃው አረጋግጧል። የዛሬው የድርድር ስብሰባ ሶስቱ አገራት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደንቦችን አስመልክቶ ስምምነት ባልደረሱባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ ያለመ እንደነበረም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
በዛሬው የድርድሩ ውሎ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ቢሮ ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መሰረት እንዲሁም የሶስቱ ሀገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትናትናው እለት በደረጉት ስብሰባ ባወጡት አቅጣጫ ላይ ተመርኩዞ በጋራ ሰነድ ላይ ለመስራት ተስማምተዋል። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ የበኩሏን የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ደንብ ለአገራቱ ማቅረቧን ነው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመግለጫው ያስታወቀው። ሱዳን እና ግብፅ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ይህንኑ ሰነድ በጥልቀት ለመመልከት ጊዜ እንደሚፈልጉ ጠቅሰው ስብሰባው ለተጨማሪ ቀናት እንዲራዘም ጠይቀዋል። ይህንንም ተከትሎ ሁለቱ አገራት የውስጥ ምክክራቸውን ሲያጠናቅቁ የተጀመረውን ድርድር ለመቀጠል ከስምምነት መደረሱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። የሚቀጥለውን የድርድር ጊዜ በተመለከተም የግብፅ ልኡክ ባቀረበው ሀሳብ መሰረት ንግግሩ በመጪው ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓም እንደሚቀጥል ሚኒስቴሩ አብራርቷል። ድርድሩ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለ11 ቀናት ሲካሄድ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ባሳለፍነው ሐምሌ 6 ቀን2012 ዓ.ም ግን በሱዳን በኩል በቀረበው የይዘግይልኝ ጥያቄ መሠረት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወቃል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን