4th International Trade Show Addis Ababa Ethiopia


የትግራይ ምርጫ እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት የሌለው ነው - የፌደሬሽን ምክር ቤት

ኢዜጋ ሪፖርተር

House-Federaion-EthiopiaSeptember 7, 2020 (Ezega.com) -- የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የትግራይ ክልል ምክር ቤት፣ የምርጫ ኮሚሽኑና አስፈፃሚ አካላት ያወጡት አዋጅና የፈፀሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው ሊደረግ የታሰበው ምርጫ "በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይፀና እና ተፈፃሚነት የሌለው ነው" በማለት የመጨረሻ ያለውን ውሳኔ በሙሉ ድምጽ አስተላልፏል፡፡ ከመካሄዱ በፊት ጭምር ሲያወዛግብ የቆየውና ብዙዎች በትኩረት ሲጠብቁት የነበረው የምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ በሕገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴዎች በኩል በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ውይይት አድርጓል ተብሏል፡፡ በውይይቱ ላይ በእስካአሁኑ  ሂደት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ ክብር ያለው መሆኑን፣ "ህገወጥ አካላት በሚፈፅሙት ድርጊት ምክንያት በሕዝቡ ላይ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም" ብሎ የሚያምን መሆኑን እና በቀጣይም ችግሮችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሰኡን ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የራያ ራዩማ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ እና የወልቃይት ጠገዴ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች በመጥቀስ "የትግራይ ክልል እያካሄደ ካለው ህገወጥ ምርጫ ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብትን አለማክበር ተቀባይነት የሌለውና ሊታረም የሚገባው" መሆኑ ከማስቀመጡም ባሻገር የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ያስተላለፈውን ውሳኔ እና የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ በደብዳቤ ሕገ መንግስቱና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዲከበር የሰጡትን ማሳሰቢያ አለመቀበሉ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነው ብሏል ምክር ቤቱ፡፡ በተጨማሪም ምክር ቤቱ ያጸደቃቸውን የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔዎች ያብራራ ሲሆን በእዚህም መሰረት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012 ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 55(15) እና አንቀጽ 55(2)(መ) ጋር ይቃረናል፣ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012ን መሰረት አድርጎ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ስልጣን ይጥሳል በመሆኑም በትግራይ ክልል የሚደረገው ምርጫ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ስለሚጥል የሚሉትን ዘርዝሮ በክልሉ የሚደረገው ምርጫ እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት የሌለው ነው ሲል ውሳኔውን አሳውቋል።

የህገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ወርቁ አዳሙ እንዳሉት የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ ነው። በህገ መንግስቱ መሰረት የምርጫ ህግ ማውጣት ለፌደራል መንግስቱ ምርጫውን ማስፈጸም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑን ገልጸው ቦርዱ በሚቋቋምበት ወቅትም "ክልሎች ስልጣን ይኑራቸው" የሚል አንቀጽ አልሰፈረም ብለዋል። ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል የኢትዮጵያም የዓለም ስጋት የሆነውን የኮቪድ-19 ወረርሽን ለመከላከል ሕገ መንግስታዊ ትርጉም ተሰጥቶ ምርጫው እንዲራዘም በፌደሬሽን ምክር ቤት የቀረበውን ውሳኔ ሳይቀበል መቅረቱንም አንስተዋል። ምክር ቤቱ ክልሉ ምርጫ የሚያደርግበት ስልጣን እንደሌለው ቢያሳውቅም በሕገ መንግስቱ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ የምርጫ ህግ በማውጣትና የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም እንቅስቃሴ ማድረጉን የተናገሩት አቶ ወርቁ ከዚህም ባለፈ "ምርጫው ህጋዊ መሰረት የሌለውና መቆም እንደሚገባው የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ፣ የራያ ራዩማ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጠይቀዋል" ብለዋል። የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ ኅብር ኢትዮጵያና ኢዜማ በበኩላቸው ከውሳኔው በፊት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ለማካሄድ ከታቀደው ክልላዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በገዢው ፓርቲና በሕወሓት መካከል ያለውን ውጥረት በዘለቄታዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ውሳኔ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል ሲሉ ተደምጠዋል።

የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሔ እንደተናገሩት ህወሓት ለማካሄድ ያሰበው ምርጫ "ህገመንግስቱን የጣሰና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከስተላለፈው ውሳኔ ያፈነገጠ" ነው። በተለይም መላው ዓለም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተናወጠበትና ምርጫ ባስተላለፈበት በዚህ ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫው እንዲራዘም ያስተላለፈውን ውሳኔ የጣሰ ነው። ህወሓት ምርጫውን ለማካሄድ ሕገ መንግሥታዊ የጊዜ ገደብ ምክንያት ቢያደርግም ዋና ዓላማውም ትግራይን ከሌላው ሕዝብ ለመገንጠል ያለመ ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ "ይህ ምርጫ ላለፉት 27 ዓመታት በመላው አገሪቱ ያደረሱትን ጥፋትና ጉዳት ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚያደርጉት ሽሽት ነው" ብለዋል ያሉት ሊቀመንበሩ የህውሓት መሪዎች ምርጫውን የሚያካሂዱት ለእውነተኛ ዲሞክራሲ መስፈን ከማሰብ ሳይሆን በተገነጠለች ትግራይ ተዝናንተው ለመኖር ያቀዱት ሴራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ትግራይን ብቻ ሳይሆን መላውን የኢትዮጵያ ክፍል የሚያናጋ ሥራ መሆኑን ገልፀው «የትግራይን ሕዝብ ወንድም እህት ከሆነው ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያጋጩት ነው» ብለዋል። ጦርነት ማወጅም ሆነ የትግራይ ሕዝብን ለሞት የሚዳርግ ማንኛውም እርምጃ ፓርቲያቸው መኖር አለበት ብሎ እንደማያምን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ ይልቁንም  "ፋይናንስ ከመከልከል ጀምሮ የኮሙዩኒኬሽንና የትራንፖርት አማራጮችን በመዝጋት ህውኃትን ከጥፋት ጎዳናው መመለስ ይገባል ነው ያሉት። ከዚህም ባለፈ ሕዝቡን ለተጨማሪ የጦርነት ስጋትም ሆነ በምርጫ ሰበብ ለባከነው ገንዘብ የህውኃትን አመራሮች ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ እንደተናገሩት የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው የሕወኃት መንግሥት ምርጫን ለማካሄድ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ "ሕገ መንግሥቱንም ሆነ ፓርቲዎች የፈረሙትን የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ የሚጣረስ ነው።" የክልሉ መንግሥት እስካሁንም ድረስ ምክር ቤቱ የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች ወደ ጎን በመተው የራሱን መንገድ መምረጡን አስታውሰው አሁንም "የምክር ቤቱን ውሳኔ ይቀበለዋል" የሚል እምነት እንደሌላቸው አመልክተዋል። በመሆኑም የሕወኃትን አቋም ሊያስቀይር የሚችል ውሳኔ ማስተላለፍ ከምክር ቤቱ እንደሚጠበቅም አስገንዝበው ነበር። "በእኛ እምነት የፌዴራል መንግሥቱን በሚያስተዳድረው ብልፅግና እና በህወኃት መካከል ያለው ልዩነት ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው መፈታት ያለበት" ያሉት አቶ ናትናኤል የፌዴራል መንግሥት ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ይህንን ኃላፊነቱን በሰላማዊ መንገድ ሊወጣው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።  የኅብር ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር ግርማ በቀለም "የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤው ከትግራይ ክልል ምርጫ ጋር በተያያዘ ጠንካራ ውሳኔ ያስተላልፋል ብለን እንጠብቃለን" በማለት ገልጸው ነበር። በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ 2̌.7 ሚሊዮን ሰዎች መመዝገባቸውና ለምርጫው የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን መግለጹ ይታወቃል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :