4th International Trade Show Addis Ababa Ethiopia


ህውሓትና ብልፅግና፤ የመጨረሻው መባቻ?

ሠላም ዓለሙ

PP-TPLFSeptember 7, 2020 (Ezega.com) -- ኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ መጥቶ ወሽመጧን ቆረተው እንጂ፤ 6ተኛዋን ብሄራዊ ምርጫ በ2012 ዓ.ም. ለማድረግ ቀን ቆርጣ ነበር፡፡ ይህን ምርጫ እንዲያሰናዳ ኃላፊነት የተጣለበትና ስልጣን የወሰደው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ዝግጅቱን ራሱን ከማሻሻል ጀምሮ የተለያዩ ህጎችን ሲያሻሽልና አዳዲስ ህግጋትንና ደንቦችንም ሲያረቅ ከርሟል። ምንም እንኳ ከፖርቲዎች ዛሬም ውግዘት ባይለየውም፡፡

ነሀሴ 23 ለማካሄድ ውጥን ተይዞለት የነበረው ምርጫ 2012 በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ምክንያት ቦርዱ በያዘው የጊዜ ሠሌዳ ማካሄድ እንደሚቸገር ለእንደራሴዎች ም/ቤት አቤት ብሎ፤ እንዲራዘም ውሳኔ ተደርሷል፡፡ ይህ ውሳኔ ታዲያ ለሁሉም የተዋጠ አልነበረም፡፡ ህገ መንግስቱ መከበር አለበት ሲል ወገቡን የያዘው ትግራይ ክልል፤ የምርጫ 2012 መራዘምን አልቀበልም ብሏል፡፡ አቋሙም በአፍ ብቻ ሳይበቃ እነሆ ትግራይ ክልል ምርጫ 2012ን ኮሮናን አሻፈረኝ ብላ ልታካሄድ የቀናት እድሜ ብቻ ቀርቷል።

የፌደራል መንግስቱና የትግራይ ግብግብ

ከ2010 ዓ.ም. ማግስት ጅምሮ ማዕከላዊ መንግስቱና የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መቃቃር የአደባባይ ሚስጥር ነው። የትግራይ ባለስልጣናት ጓዛቸውን ጥቅልለው ከአዲስ ኦበባ ወደ መቀሌ መክተም የግብግቡ መጀመሪያ ይሁን እንጂ መቋጫ ኦይደለም። ክልሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ኦህመድ ኦስተዳደር ስልጣን ከጨበጠ ወዲህ ልቡ ወደ ወደ አዲሱ መንግስት ኦልወደቀም። በዚህ ላይ በየጊዜው የተለጠፉለት አስንዋሪ ታርጋዎች ቂም እንዲቋጥር አድርጓል። በተለይም ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የአገረ ሀብት ምዝበራ ወደ አንድ ክልል ብቻ ማንጣጥር መቆራረጫ ሆኖ ተመዝግቧል።

ህገ መንግስቱ መከበር አለበት በሚል እልህ የተጀመረው ምርጫ ግን ፍጥጫው በኪነ ጥበብ ስሙ ክላይማክስ መድረሱ ሁነኛ ማሳያ ነው። ይህን የሁለቱን ቡድኖች አንገት ለአንገት መያያዝ ለአገር ህልውና ያሰጋል ያሉ ሁሉ ሊያሸማግሉ ቢሞክሩም፤ ጠብ ያለ ፍሬ ነገር አልተገኝም። የቅርብ ጊዜ ትውስታ የሆነውን የአገር ሽማግሌዎችን የከሸፈ ሙከራ ማየት በቂ ነው።

ሌላው የሁለቱ አካላትን መቃቃር ለመጥቀስ ያህል፤ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሲባል የወጣው የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ መጣስ ነው። በአዋጁ መሰረት የመረጃ ፍሰትን ለመቆጣጠርና በኃላፊነት ለማሕበረሰቡ ለማድረስ ሲባል፤ ወረርሽኙን በተመለከተ መረጃን የሚሰጠው ጤና ሚኒስቴር ብቻ እንዲሆነ ይደነግጋል። ይሁን እንጂ ትግራይ ክልል በዚህ ህግ አልገዛም ሲል በራሱ መንገድ ስል ቫይረሱ መግለጫ መስጠቱን ተያያዘው። ማንም ግን የህግ ያለህ አላለውም።

ፌደሬሸን ም/ቤትና የትግራይ ም/ቤት እሰጣ ገባ

በሀምሌ ወር መጨረሻ ኬሪያ ኢብራሂም የህገ መንግስት ጥስት እየተፈጽመ ነው በሚል የለቀቁት ተቋም ትግራይን ምርጫ አታካሂድ ብሎ ደብዳቤ ጸፎ ነበር። የትግራይ ም/ቤት አፈ ጉባኤም ለዚህ ደብዳቤ ምላሽ ሲሰጡ የደረሰውን ደብዳቤ ‘‘ህገ መንግስታዊ መሰረት የሌለው፤ የህገ መንግስት መርሆዎችንም የሚጥስ፤ የብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት የሚጻረር ነው’’ ሲሉ ተቃውመውታል።

ለነሀሴ 30 አስቸኳይ ስብስባ የጠራው የፌደሬሽን ም/ቤት፤ አጀንዳ አስቀድሞ አልተላከልንም በሚል የም/ቤቱ የትግራይ ተወላጆች አልተሳተፉም ነበር። ከዚህ ስብሰባ አንድ ቀን አስቀድሞ የትግራይ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባው ምን እንደሚወስን የተነበየ እስኪመስል ድረስ ቆራጥ ውሳኔ አስልፏል።

‘‘ሊካሄድ የታሰበውን ምርጫ ለማስቆም በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚተላለፍ ማንኛውም ውሳኔ እንደ ጦርነት አዋጅ አየዋለሁ አለ’’። ፌደሬሽን ም/ቤትም ያበጠው ይፈንዳ ብሎ ነሀሴ 30 2012 ዓ.ም. በዝግ ባካሄደው ስብሰባው በመጪው ረቡዕ (ጳጉሜ አራት) በክልሉ ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ ከአገሪቱ ህገ መንግሥት ጋር የሚቃረን በመሆኑ "እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈጻሚነት የሌለው ነው" ሲል በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

በም/ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ መሰረት በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ የሚደረገው እንቅስቃሴ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 9 (1) መሰረት እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት የሌለው ነው በማለት፣ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ ለመገናኛ ብዙኸኝ ይፋ ባደረገው መግለጫው አስታውቋል። ም/ቤቱ በስብሰባ ላይ "ህገ ወጥ አካላት በሚፈፅሙት ድርጊት ምክንያት በሕዝቡ ላይ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም ብሎ እንደሚያምንም አስምሮበታል።

ለፌዴሬሽን ም/ቤት ምላሽ የሰጡት የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ውሳኔውን ‘‘ራሱ ከሳሽና ፈራጅ የሆንብት’’ የሆነበት ከም/ቤቱ የቀደመ አሰራርና ከህገ መንግስቱ ያፈነገጠ ነው ብለውታል። ኃላፊው የም/ቤቱን ሁኔታ ሲገልጹም ‘‘እኔ ያልምረቁት መንግስት እድሜው የሚያጥር ይሁን የሚል እርግማን ነው የተሰጠው ይላሉ’’።

ረቡዕ ጳጉሜ አራት ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ክልላዊው የትግራይ ምርጫ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ። ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን መራጮችም ለመምረጥ ተመዝግብዋል።

የወደፊት እጣፋንታ

ፌዴራል መንግስት እና ትግራይ ክልላዊ መንግስት፤ ብልፅግና እና ህውሓትና ሆሊውድ ላይ ያሉ የፊልም ገጸ ባህሪያት እስኪመስሉ ድርስ ግብግቡን በጉጉት እየመሩት ነው። በእልህ የተጀመረ ግን ጣሪያ የደረሰ ፍጭት፤ ፍሬው ምን ይሆን የሚለው የሚሊዮን ብር ጥያቄ ሳይሆን አይቀርም።

ትግራይ ምርጫውን ከማካሄዱ ካልተግታና መስከረም መጀመሪያ አካባቢ ይፋ የሚያደርገው የምርጫ ውጤትም ተቀባይንትም ተፈጻሚነትም ከሌለው የክልሉ እጣፈንታም ሆን የአገሪቱ ህልውናስ ምን ሊሆን ይችላል? ከሌሎች ክልሎች ጋር ያለው ግንኙንትስ እንዴት ነው የሚሆነው? የበጀት ክፍፍልን ጨምሮ ሌሎች የጋርዮሸ ስራዎች ምን ይውጣቸው ይሆን? በዝሆኖች ግጭት ሳሩ ምን ዋጋ ይከፍል ይሆን? የዚህ ሁሉ መልስ በጊዜ እጅ ላይ ወድቋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :