4th International Trade Show Addis Ababa Ethiopia


አወዛጋቢው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ ተካሄደ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Tigray-Region-electionsSeptember 9, 2020 (Ezega.com) -- ለወራት መንግስትንና ህወሃትን በከረረ መንገድ ሲያወዛግብ የከረመው 6ኛው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ተጠናቀቀ። መራጮች ከለሊት 7 ሰአት አንስቶ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ተራ ሲጠብቁ አድረው ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ ድምፃቸውን ሲሰጡ መዋላቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የትግራይ ክልል  ምርጫ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም እንደገለፁት  ለመምረጥ ከተመዘገበው 2.7 ሚሊዮን የክልሉ ነዋሪ መካከል 97 በመቶ በላይ የሚሆነው ድምጹን ሰጥቷል። በምርጫ ወቅት ይህ ነው የሚባል ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን የገለፁት ኮሚሽነር ሙሉ ቀን ከተቃዋሚም ፓርቲዎችም ቢሆን የደረሳቸው ቅሬታ አለመኖሩን ገልፀዋል። በሰላም ተጠናቋል በተባለለት ክልላዊ ምርጫው ክልሉን የሚያስተዳድረውን ህወሓትን ጨምሮ አምስት ፓርቲዎች የተወዳደሩ ሲሆን ለምርጫ የተመዘገቡ ነዋሪዎችም ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምረው በመውጣት መምረጣቸውንና ከእኩለ ቀን በኋላ አብዛኛው የመራጭ ጣብያዎች ባዶ እንደነበሩ ተገልጿል።  የድምጽ ቆጠራው በጣብያ ደረጃ እስከ ጠዋት ድረስ ያልቃል ያሉት ኮሚሽነሩ የምርጫው ውጤት መስከረም 2 ይገለፃል ተብሎ መታቀዱን ገልፀዋል። መራጩ ህዝብ አካላዊ ርቀቱን ጠብቆ፣ ሙቀቱ እየተለካና ፀረ-ተህዋሲያን እየተጠቀመ ለኮሮና ቫይረስ በማያጋልጥ አግባብ እንዲመርጥ መደረጉንም የትግራይ ክልል  ምርጫ ኮሚሽን ተናግሯል።

በ6ኛው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ በፌደራል መንግሥቱና በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ጉልህ ሚና የነበራቸው ዋና ዋና የህወሓት አባላት በተለያዩ ጣቢያዎች ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ለውድድር የቀረቡ ሲሆን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንትና የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በአድዋ ከተማ ፓርቲያቸውን ወክለው ተወዳድረዋል። እዚያው አድዋ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ደግሞ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርና የቀድሞዋ የንግድ ሚኒስትር ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ) እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ መወዳደራቸው ተሰምቷል። በመቀሌ የምርጫ አካባቢ ህወሓትን ወክለው ከሚወዳደሩት መካከል ከጥቂት ወራት በፊት ኃላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁት የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም፣ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ክንደያ ገብረሕይወት (ፕሮፌሰር) እንደርታና የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር የአቶ ጌታቸው አሰፋ ወንድም አቶ ዳንኤል አሰፋ እንደሚገኙበት ታውቋል። የአዲግራት ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክትር ዛይድ ነጋሽ በአዲግራት ህወሓትን ወክለው የተወዳደሩ ሲሆን የቀድሞው የኮሙኑኬሽን ሚኒስትርና በተለያዩ የማዕከላዊው መንግሥት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሰሩት አቶ ጌታቸው ረዳም አላማጣ ውስጥ ተወዳድረዋል።

በሌላ በኩል ድርጅቶቻቸውን በመወከል የተፎካከሩት የሳልሳይ ወያነ፣ ባይቶና እና ውናት (ውድብ ነፃነት ትግራይ) የተቃዋሚ አመራሮች በመቐለ ከተማ ድምፅ ሰጥተዋል። 'ትግራይ ነፃ አገር ሆና ልትመሰረት ይገባል' በማለት የሚያቀነቅነው የውናት ፓርቲ ሊቀመንበር መሓሪ ዮሃንስ ምርጫው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድር ፉክክር በላይ ትርጉም ያለው እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግራል። "ይህች ቀን የትግራይ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ በተግባር ያረጋገጠበት ሰለሆነች የተለየች ናት" ያለው ሊቀመንበሩ "እንደ ውናት ይህንን ምርጫ እንደ ሪፈረንደም ነው የምናየው" እንደ ሕዝብ ትልቅ ዋጋ የተከፈለበት መብት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር በማለት ተናግሯል። ሌላኛው በከተማዋ ድምፁን የሰጠው የባይቶና ሊቀመንበር ኪዳነ አመነም በምርጫው ሂደት ደስተኛ እንደሆነ ተናግሯል::

በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ትናንት ምሽት ከብሔራዊው ቴሌቪዥን (ኢቢሲ) ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ላይ ምርጫው ሕጋዊ አይደለም ሲሉ በድጋሚ ተደምጠዋል ሂደቱን "የጨረቃ ምርጫ" በሚል የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ "ሕጋዊ አይደለም ምክንያቱም በኢትዮጵያ ምርጫ ማከናወን የሚችለው የምርጫ ቦርድ ብቻ ነው" ብለዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲረዱት የምፈልገው ነገር ህውሓት ክልሉን ለዓመታት አስተዳድሯል ክልሉን የማስተዳደር ስልጣኑም እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ እንዲራዘም ተደርጓል ብለዋል። "አሁን በዚህ ሰዓት የሚደረጉ የእቁብ ስብስቦች ወይም ጉባኤዎች የእኛ ትልቅ እራስ ምታት መሆን የለባቸውም" ያሉ ሲሆን በትግራይ የጦርነት አማራጭ እንደማይኖርም አረጋግጠዋል። "በእኔ በኩል ለኢትዮጵያ ውጊያ ያስልጋል ብዬ አላምንም። እኔ በፍጹም ውጊያ ከሚደግፉ ሰዎች ጎን መመደብ አልፈልግም እኔ የምፈልገው ለትግራይ አንድ ጥይት መላክ ሳይሆን አንድ የኮሮና አፈ መሸፈኛ መላክ ነው" ሲሉም አክለዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከቀናት በፊት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የትግራይ ክልል ምክር ቤት፣ የምርጫ ኮሚሽኑና አስፈፃሚ አካላት ያወጡት አዋጅና የፈፀሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው ምርጫው "በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይፀና እና ተፈፃሚነት የሌለው ነው" በማለት የመጨረሻ ያለውን ውሳኔ በሙሉ ድምጽ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :