ኢትዮጵያ የብር ኖት ለውጥ አደረገች

ኢዜጋ ሪፖርተር

New-Bank-Notes-EthiopiaSeptember 14, 2020 (Ezega.com) -- በኢትዮጵያ የወረቀት ብር ኖቶች ለውጥ ሊደረግ ነው የሚለው ወሬ መናፈስ ከጀመረ ከሁለት  ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ቅያሬው እውን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።ከ 5 ብር ኖት በስተቀር ሁሉም ብሮች ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀየሩ የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ የተደረገው የብር ለውጥ አገሪቱ እያካሄደችው ያለችው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ አንዱ አካል እንደሆነ አስረድተዋል። በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የ200 ብር ኖት መዘጋጀቱም ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የብር ለውጡ ለሕገ ወጥ ተግባራት የሚውለውን ገንዘብ ለማስቀረት፣ ሙስናንና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ይረዳል ሲሉም ተደምጠዋል። ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና የሐሰተኛ የብር ኖት በገበያው ውስጥ በተደጋጋሚ መከሰታቸው አገሪቱን ለማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት እንዳጋለጣት የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች ይናገራሉ። ያጋጠመውን የዋጋ ንረት የመቆጣጠሩ ተግባርም በሚፈለገው መጠን ውጤት ማምጣት እንዳልቻለ የሚናገሩት የዘርፉ ባለሞያዎች ለዚህ ደግሞ ከባንክ ውጪ የሚንቀሳቀስ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መኖሩ አንዱ ችግር መሆኑን ያስረዳሉ።

በብር ቅያሪው ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እንዳሉት 2.9 ቢሊዮን አዳዲስ የብር ኖቶች ታትመው በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በበቂ ሁኔታ ለማድረስ ዘግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን እነዚህን የብር ኖቶች ለማሳተም መንግስት ከ3.7 ቢሊዮን ብር በለይ ውጭ አድርጓል። ቅያሬው በ3 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ያሉት ገዢው አዲሶቹ የብር ኖቶች ቀደም ሲል ከነበሩት በተሻለ ለአጠቃቀም ምቹና ረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ ተደርገው መሰራታቸውን ገለጸዋል። ከቀለም አንጻር አዲሱ ባለ 200 ብር ኖት ሐምራዊ፣ ባለ100 ብር ኖት ውሃ ሰማያዊ፣ ባለ50 ብር ኖት ቀይ ብርቱካናማ፣ ባለ10 ብር ኖት ደግሞ አረንጓዴ ቀለም አላቸው። በአዳዲሶቹ የብር ኖቶች ላይ ቀደም ሲል በነበሩት ላይ ያልነበሩ የአገሪቱን ገጽታ የሚያሳዩ ምስሎች የተካተቱበት ሲሆን በዚህም በባለ አስር ብር ኖት ላይ ግመል፣ በባለ መቶ ብር ኖት ላይ ደግሞ የሶፍ ኡመር ዋሻና የሐረር ግንብ እንዲካተቱባቸው ተደርጓል። የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር እንዳመለከቱት "ከኢትዮጵያ ውጪ በጎረቤት አገራት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የኢትዮጵያ ብር ተከማችቶ ይገኛል" በመሆኑም ከብር ለውጡ ጋር ተያይዞ በውጪ አገራት ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብር ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።ከእዚህ ሌላ የብር ቅያሬው በውክልና የማይከናወን በመሆኑ መታወቂያ በመያዝ ባለቤቱ ብቻ መቀየር እንዳለበት ሃላፊው ጨምረው አስረድተዋል።

ላለፉት 23 ዓመታት በዝውውር ላይ የነበሩትን የብር ኖቶች ከገበያ በማስወጣት በአዲሶቹ የመተካቱ ሂደት በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጧል። ነገር ግን አሮጌዎቹን የብር ኖቶች በአዲስ በመተካቱ ሂደት ውስጥ 100 ሺህ እና ከዚያ በላይ ብር ያላቸው ሰዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መቀየር እንዳለባቸው ተገልጿል። በዚህ ሂደት ውስጥ እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ ለሚደረግ የብር ለውጥ ቀጥታ ገንዘቡን በመስጠት የሚከናወን ሲሆን ከአስር ሺህ ብር በላይ የሚቀየር ከሆነ ደግሞ ብሩን ለመለወጥ ባመጣው ግለሰብ ስም የባንክ ደብተር ተከፍቶ እንዲቀመጥ ይደረጋል ተብሏል። ይፋ የተደረጉት አዳዲሶቹ የብር ኖቶች አስመስለው የሚሰሩ ሐሰተኛ የብር ኖቶችን ለመከላከልና ለመለየት በሚያስችል ሁኔታ የተለያዩ የደኅንነት መጠበቂያ ገጽታዎች እንዲኖሯቸው ተደርጓል። በተጨማሪም ለዓይነ ስውራን አጠቃቀም እንዲያመች የመለያ ምልክት ያለው ሲሆን፤ በዚህም ዓይነ ስውራን የብሩን ዋጋ በእጅ ዳሰሳ ማወቅ የሚችሉበት ምልክትና የደኅንነት መጠበቂያ ገጽታ አላቸው።

ከዚህ ባሻገርም የብር ኖቱ ወደ ላይ ወይም ወደታች በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ደማቅ የቀለም ፍንጣቂ የደኅንነት መጠበቂያ ገጽታ ያለው ሲሆን የብር ኖቶቱ በእጅ ሲዳሰሱ የመጎርበጥ ስሜት እንዲሁም የብሩ ዋጋ ይታያል። አዲሶቹ ኖቶች ተጨማሪ ባለቀለም ኮከብ የደኅንነት ገጽታን ከማካተታቸው ባሻገር አብረቅራቂ የደኅንነት መጠበቂያ ክር፤ በክሩ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስያሜ በምህጻረ ቃላት በአማርኛና በእንግሊዝኛ እንዲሁም የብሩ መጠን ሰፍሮ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ አዲሶቹ የብር ኖቶችን ወደ ብርሃን አቅጣጫ በማዞር ሲታዩ ከፊት ከሚታየው ምስል ትይዩ ተመሳሳይ ደብዛዛ መልክ የያዘ ምልክት ይታያል። እንዲሁም የብር ኖቶቹ በብርሃን አቅጣጫ ሲታዮ ኳስ የሚመስሉ ምልክቶች ከኖቶቹ በስተጀርባ ካለው ተመሳሳይ ምልክት ጋር በፍፁም ትይዩ ሆነው በአንድ ቦታ ላይ ያርፋሉ።

በተመሳሳይ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ "አንዳንድ ባንኮች" ህገወጥ የብር ኖቶችን እያሰራጩ ይገኛሉ የተባለ ሲሆን ጠቅላይ ሚንስትሩ በዛሬው መግለጫቸው እንዳሉት በጥብቅ ክትትል እየተደረገባቸው ያሉት ባንኮቹ በድርጊቱ ተሳትፈው ከተገኙ "ከሚቀጥለው ቀን ጀምሮ ባንክ አይደሉም" ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በድርጊቱ ተሳትፏል የተባለው ባንክ ወጋገን ነው ያሉት የተለያዩ ምንጮች ባንኩ በተለይ በATM ማሽኖቹ አማካይነት ህገወጥ ገንዘቡን ሲያሰራጭ  ስለመቆየቱ በእርግጠኝነት መናገር እንደሚቻልም ይናገራሉ። በሁሉም የወጋገን ባንክ ኤትኤሞች የሚወጡት ገንዘቦች በሙሉ አዲስና ቁጥራቸው ተከታታይ ነው መባሉ የባንክ ባለሞያዎች ዘንድ በህገወጥ መንገድ የታተመ የገንዘብ ኖቶችን በATM በኩል እያሰራጩ እንደሆነ ተጨባጭ ማስረጃ እንደሆነ ተነግሯል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :