ከለውጡ በኋላ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከመመሪያ ውጭ ባክኗል ተባለ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Ethiopia-Foreign-CurrencySeptember 18, 2020 (Ezega.com) -- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ስልጣን በያዙ ማግስት የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ካዝና ክፉኛ ተመዝብሮ ባዶ እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል። ያም ሆኖ እሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከብሔራዊ ባንክ ደንብ እና መመሪያ ውጭ ሲባክን እንደ ነበር ሸገር ሬዲዮ ዘግቧል። ጣቢያው አገኘሁት ባለው ሰነድ መሰረት ከለውጡ ወዲህ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካኝነት ከብሔራዊ ባንክ መመሪያ ውጭ የውጭ ምንዛሪ ለማይፈቀድላቸው አካላት ሲሰጥ ቆይቷል። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአቶ በቃሉ ዘለቀ ይመራ በነበረበት በ2010 አመት ከግንቦት እስከ ነሀሴ ከባንኩ በትንሹ ከ69 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ "ከመመሪያ ውጪ ለተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች" መሰጠቱ ተነግሯል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ድልድልን አስመልክቶ ከ3 ዓመታት በፊት ያወጣውን መመሪያ ንግድ ባንኩ በከፍተኛ ደረጃ ሲጥስ እንደነበርም የተገኘው ሰነድ ያመለክታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጪ ሀገር ገንዘብ ወይም የውጪ ምንዛሪ ድልድልን አስመልክቶ ያወጣው መመሪያ ቁጥር FXD/51/2017 ለኮንስትራክሽን ድርጅቶች የግንባታ ማሽኖች መለዋወጫ ለማስገባት ለአንድ የግዢ ማቅረቢያ ከ50,000 የማይበልጥ የአሜሪካ ዶላር እንዲመደብ ይፈቅዳል።

ያም ሆኖ መመሪያው ከወጣ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት መመሪያው ተጥሶ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ባክኗል ተብሏል። ለአብነትም በ1ኛው ወቅት በቁጥር 36 ለሚሆኑ በሌላ ጊዜ ደግሞ 46 ለሚደርሱ የውጭ ምንዛሪ ጠያቂዎች ለእያንዳንዳቸው ከመመሪያው ውጪ ከ50,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ ተመድቦላቸው ወይም ተሰጥቷቸው እንደነበር መረጃው ያሳያል። ከራሱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወጣው እና የባንኩ የቀድሞ ፕሬዘዳንት አቶ ባጫ ጊና  ፊርማ እንዳለበት የተነገረው ሰነድ እንደሚያስረዳው ከሆነ በመጀመሪያው ወቅት36 ለሚሆኑ የውጪ ምንዛሪ ጠያቂዎች ለእያንዳንዳቸው ከመመሪያ ውጪ ከ50,000 ዶላር በላይ በድምሩ 19 ሚሊዮን 886 ሺ 137 የአሜሪካ ዶላር ፣ በሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ ለ 46 የውጪ ምንዛሪ ጠያቂዎች በድምሩ 27 ሚሊዮን 648 ሺ 788 የአሜሪካ ዶላር እንደተሰጣቸው ያሳያል። በ2010 አመተ ምህረት ከመመሪያው ውጪ የውጪ ምንዛሪ እንዲያገኙ ከተፈቀደላቸው ድርጅቶች መካከልም መለስ ፋውንዴሽን 100 ሺ ዶላር፣ የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ 66 ሺህ 750 ዶላር፣ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ሴንተር 500 ሺ የአሜሪካ ዶላር፣ ኢዮሃ ፕሪንተር 27 ሺህ ዶላር እና ብርሃኔ ወልዱ 140 ሺ 800 ዶላር እንደሚገኙበት ሸገር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ባንኩ በተመሳሳይ ጊዜ ማለትም በግንቦት 2010 በቁጥር 10 ለሚሆኑ መኪና አቅራቢዎች ከብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ድልድል መመሪያው ውጪ ለመለዋወጫ ማስመጫ10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሰጠም በዚሁ ሰነድ ላይ መጠቀሱ ተሰምቷል። በአቶ በቃሉ ዘለቀ እግር አቶ ባጫ ጊና ከተተኩ በኋላ የተፈፀመው አሰራር እና የውጭ ምንዛሪ ብክነት ተጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በየካቲት ወር 2011 ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ማሳወቃቸውን የተገኘው ሰነድ አመልክቷል ተብሏል። ሸገር የተፈፀመውን ህገ ወጥ የውጪ ምንዛሪ ብክነት አስመልክቶ ጉዳዩ የሚመለከተው ህግ አስፈፃሚ አካል አስፈላጊውን ምርመራ እንዲያካሂድ ባንኩ ደብዳቤ የፃፈው በየካቲት ወር 2011 ማለትም ከዛሬ 1 ዓመት ከ6 ወር በፊት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምን እርምጃ ወስዶ ይሆን ሲል የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግን መጠየቁን ገልጿል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ም/ል አቃቤ ህግ አቶ ፍቃዱ ፀጋ ጉዳዩን አስመልክቶ  በሰጡት ምላሽ እሳቸው በምክትል አቃቤ ህግ ማዕረግ የተሾሙት በቅርቡ መሆኑን ተናግረው ጉዳዩ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አጣራለሁ ብለዋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :