በኢሬቻ በአል ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም በህወሓት የተደራጀ ቡድን መያዙን ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አስታወቀ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Irreecha-Celebration-TPLFOctober 1, 2020 (Ezega.com) -- በቢሾፍቱና በአዲስ አበባ ከተማ ከሚከበረው የኢሬቻ በዓል ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃቶች ለመፈጸም፣ አመጽ ለማቀጣጠልና ግጭትና ትርምስ ለመፍጠር ከትግራይ ክልል የጸጥታ ቢሮ ሃላፊና ከህወሓት የጥፋት ቡድኖች ተልዕኮ ተቀብሎ በህቡዕ ሲያስተባብርና ሲመራ የነበረ የኦነግ ሸኔ ቡድን ከእነ ግብረአበሮቹ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ማድረጉን የበሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ማምሻውን ለመገናኛ ብዙሃን ባሰራጨው መግለጫ ላይ እንደገለጸው ከኢሬቻ በዓል ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ፣ በቢሾፍቱና በሌሎቹም የአገሪቱ አካባቢዎች በጦር መሳሪያ የተደገፈ የሽብር ጥቃት፣ አመጽ ፣ ግጭትና ትርምስ ለመፍጠር ተልዕኮ ለተሰጠው በህቡዕ የተደራጀ አንድ ታጣቂ ቡድን የሚውል 10 ክላሺንኮቭ የጦር መሳሪያ ከ 280 ጥይቶች ጋር ከመቀሌ ወደ ባቲ ሲጓዝ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም ቀን በደቡብ ወሎ ዞን ሃይቅ ከተማ ከእነ ተሽከርካሪው በቁጥጥር ሥር ውሏል። በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ህዝባዊ አመጽ እንዲነሳ በማድረግ ይህን እንቅስቃሴ ለማሳካት ከተመለመሉት መካከል አንዱ የሆነው እንድሪስ እያሱ መሃመድ የተባለ የኦነግ ሸኔ አባል ከትግራይ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊና ከሌሎች ጥቂት የህወሓት የጥፋት ቡድኖች ጋር በህቡዕ ተልዕኮውን ሲያቀናጁ እንደነበርም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አመልክቷል።

እነዚህ "የጥፋት ቡድኖች በመጪው ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልሎች የሚከበሩትን የኢሬቻ በዓላት ተገን በማድረግ በኦሮሚያ ክልል አመፅ እንዲቀጣጠልና ወደ ሌሎች ክአካባቢዎችም እንዲዛመት በጦር መሳሪያ ጭምር የታገዘ ትርምስ ለመፍጠር ከመቀሌ ወደ መሃል አገር የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ሲልኩ እንደነበር" ማረጋገጡንም ተቋሙ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ለዚህ "እኩይ ተግባራቸውም ግለሰቦችን መልምለው ወደ መቀሌ በመውሰድ አሰልጥነው ወደተለያዩ አካባቢዎች ይልኩ እንደነበር" የገለጸው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለዚህ ተልዕኮ እንዲረዳቸው ካደራጇቸው የህቡዕ ቡድኖች መካካል አንዱ እንድሪስ እያሱ መሃመድ በተባለ የኦነግ ሸኔ አባል የሚመራና ላለፉት ወራት ከከሚሴ፣ መቀሌ አዲስ አበባ በመመላለስ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀስ ቆይቷል ብሏል። በተጨማሪም የጥፋት ቡድኑ መሪ "መቀሌ ከሚገኘው የትግራይ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ተኪኡ ምትኩና ሌሎች ጥቂት የህወሓት የጥፋት ቡድኖች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠርና ወደ መቀሌ በመመላለስ የጦር መሳሪያ፣ ገንዘብና ተልዕኮ ተቀብሎ ከሸኔ ታጣቂ ቡድን ጋር በማስተሳሰር በኦሮሚያ የአመጽ ቡድን ሲያደራጅ ቆይቷል" ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ እንድሪስ እያሱ መሃመድ እና ግብረአበሮቹ ከመቀሌ በተሰጣቸው ተልዕኮ መሠረት በባቲ የህቡዕ ቡድን አበላትን በማደራጀት በአካባቢው የብሄር ግጭቶችን የማስፋፋት እንዲሁም በሌሎችም ስፍራዎች ግጭት የመቀስቀስ ተልዕኮ ተቀብለው ሲያስፈጽሙ ቆይተዋል ያለው መግለጫው አማርኛ፣ ኦሮሞኛ፣ ሱማሊኛ፣ አፋርኛና አረብኛ በድምሩ አምስት ቋንቋዎችን የሚናገረው የሽብር ቡድኑ መሪና አስተባባሪ እንድሪስ እያሱ መሃመድና ግብረ አበሮቹን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገው እንቅስቃሴ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በጥብቅ ሙያዊ ዲስፕሊን የመከታተልና መረጃ የመስጠት ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና የኢፌዴሪ መካላከያ ሰራዊት በጋራ መስራታቸውንም በመግለጫው አመልክቷል፡፡ "መቀሌ ተሸርቦ ደቡብ ወሎ ዞን ሀይቅ ከተማ ላይ የከሸፈው የሽበር ጥቃት መሳሪያዎችን በከረዩና በባቲ በኩል ወደ ቢሾፍቱና አዲስ አበባ በማስገባት ከፍተኛ ሁከትና ግርግር በመፍጠር አገርን ለማተራመስ እቅድ እንደነበረው" የጠቆመው መግለጫው ሴራውን በማክሸፍ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጉንም ያትታል፡፡

በተያያዘ መረጃ መስከረም 23 እና 24 የሚከበረውን የኢሬቻ በአል ለመረበሽ የተዘጋጁ 503 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል ፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ኮማንደር አራርሳ መርዳሳ ቀድም ብለው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት የኢሬቻ በዓል ላይ የሚሳተፉ የበዓሉ ታዳሚዎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ኮሚሽኑ በጥብቅ እየሰራ ይገኛል። የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት በተለያየ አቅጣጫ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሀይሎች እንዳሉና ኮሚሽኑም እንደደረሰባቸው የገለፁት ኮማንደሩ እስካሁን ድረስ 503 ሰዎች፣ 14 ክላሽ ፣ 26 ቦምብ እና 103 ሽጉጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ የኢሬቻ በዓል በኮረና ምክንያት እንደ ከዚህ ቀደሙ በርከት ባለ ሰው የማይከበር ስለሆነ በገዳ አባቶች የተላለፈውን ውሳኔ ህብረተሰቡ ስራ ላይ ማዋል እንዳለበትም ጄኔራል ኮማንደር አራርሳ አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመሆን "ከህወሓት እና ከሸኔ የተሰጣቸውን ግዳጅ በመውሰድና ኦሮሚያን የጦርነት አውድማ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሀይሎችን በማጋለጥ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ" ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ "የስልጣን ጥም ያለባቸው አካላት 'ከመስከረም 25 በኋላ መንግስት የለም' እያሉ ህብረተሰቡን ለማወክ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በምንም ሁኔታ እንደማይሳካላቸውም ኮማንደር አራርሳ ተናግረዋል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :