ዕድል ከሌለህ…..ድሃ ትሆናለህ!!! የገንዘብ ኖቶች ወግ - ስላቀ ህይወት

ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

October 5, 2020
 
Ethiopian-New-Bank-Notes-“ከሀብታም ቤት ጥብስ፤ ከድሃ ቤት ጥቅስ አይጠፋም!”
(የታክሲው ጠቃሽ፤ ብሩክ)

“ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ!”
(አገራዊ ብሂል)

“Poverty is like punishment for a crime you didn’t commit.”
(Eli Khamarov, Author)

እንደምን ሰንብተሃል ዕድለ ቢሱ ወዳጄ?….በዓሉንስ እንዴት አሳለፍከው ይሆን?! ያ ጉድ የማያልቅበት ተስፋዬ ካሳ ድሆች ፆም ሲፈታ “ሌላ ፆም ከመያዝ በቀር” በዓልን እንደማይዙ ሲቀልድ ሰምተሃልና ይቅር…..መቅድሙን በተከተለው ስላቅ መሰንበቻችንን “በደሳሳ ጎጆ እምኖር የሞራል ባለፀጋ ነኝ!” ሲል ነገሩን በገደለው ገጣሚ ነበር የተሰናበትኩህ፡፡ ያው ድሃ ብሆንም ከነሞራሌ ነኝና ያለሁት “አለሁ አልሞትኩም!” አይነት ብስጭት ስላበዛህብኝ ነበር ያንን መጋበዜ….በእርግጥ የእኛን መደብ በቅርቡ የተቀላቀለውና የመደባችሁን “ቁስሎች” በመነካካት እንዴት በአንድ ጊዜ ውዴታንም ገንዘብንም አጣምሮ መስራት እንደሚቻል የተካነው ከያኒ ቴዎድሮስ ካሳሁን ዘ-አፍሮ ባንድ “ባዶ” የሚል የሶሎሞን ሞገስ (ፋሲል) ግጥምን ያዜመ ሙዚቃ አለው፡፡

ብላቴናው በዚህ ሙዚቃው በአንድ በኩል አሁን የሚኖረውን አኗኗር ያኔ ላይ ሆኖ ሲመኘው፣ በሌላ በኩል ግን ለገንዘብና ለዚህ አይነቱ የድሎት ወምቾት ኑሮ ስል ደግሞ ሰላሜን የማጣ መሆንን አልፈልግም፤ ታምኖ መኖርን እንጂ መዋሸትን አልችልም፤ የዓለማችን ሙላት “ሰው” ነው እንጂ ገንዘብ አይደለምና ይልሃል….ይህም ብቻ አልበቃውም ከሰላሳ ዲናሩ ሽያጭ በስተጓዳኝ “የዓመል ነው እንጂ ድሃ የገንዘብ የለም!” ሲል አንተን መሰል ወዳጆቼ ላይ የሚሳለቅም ይመስላል….በእርግጥ ባያውቅህ ነውና አትፍረድበት ወዳጄ! እንጂማ ያንተን ሸጋ አመል ብናካፍለው ለበርካቶች ተራፊ ነው፡፡ ችግሩ ያለው….ይህንን ፀባየ-ሰናይነትህንና ዓመለ ሸጋነትህንም የደበቀው የገንዘብ ድህነትህ ነው፡፡ እስኪ የሙዚቃ ግጥሙን አንጓዎች ቆዝምባቸውማ:-

“ዋሽቶ ለመኖር አፌ - አይችልም ከቶ
ታምኖ ይኖራል እንጂ - ያለውን በልቶ
ደልቶኝ የሞላ ኑሮ - መኖር ባልጠላም
ገንዘብ ለማግኘት ብዬ አላጣም ሰላም
እኔ አላጣም ሰላም (2)
ይህ ዓለም ንዋይ ጭኖ - ወርቁን በሙዳይ
ማርኮት ከረታት ነብሴን - ከሰጣት ጉዳይ
ህሊና ሲያጣ ሰላም - ወርቅ አልማዝ ሞልቶ
ሳይተኙ ማደር ሊሆን - ከራስ ተጣልቶ
ከዚህ ሁሉ ቅጣት - ይሻላል ማጣት
አስኮንኛት ነብሴን - አልሞላም ኪሴን፡፡
ነብሴ እጅ እንዳትሰጪው ለኪሴ - ታጣይኛለሽ ከራሴ
ሰላሜ እረፍት ያለብሽ መኝታ - ታምናሽ አኑሪን ከጌታ፤
አንገት ከሚሰበር - ባይበላስ ቢቀር
ያሉት ከሚጠፋ - የወለዱት ይጥፋ
ይሉኝታ ከማጣ - ዛሬ ገንዘብ ልጣ
አስገምቼው ራሴን - አልሞላውም ኪሴን…..”

ብላቴናው “ሰው” የዓለም ጌጥና ታላቅ ፍጡር መሆኑን ሲነግርህ ሀብታም ካልሆነ በቀር ታናሽነቱን ይሸሽግብሃል፤ ሰው “የሰው መድኃኒት” መሆኑን ሲጠቁምህ መድኃኒትነቱ ለሽረትህ ብቻ ሳይሆን ለሞትህም ጥርጊያውን ሊያመቻች እንደሚችል ይሰትረብሃል፡፡ በእርግጥ እርሱ ጎራችንን የተቀላቀለ ብልጥ ነውና መንቃት ያለብህ ዕድለ ቢሱ ድሃ ወዳጄ አንተው ነህ….በተደጋጋሚ በአንጋፋው ሙዚቀኛችን ስንኞች በኩል እንዳስታወስኩህ ገንዘብ ከሌለህ ወዳጅም ሰውም አይኖርህም….”እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም!” የምንግዜውም ምርጥ መርህህ ሊሆን ይገባል፡፡

ምናልባት ይህንን ፅሁፍ በምታነብበት ሰዓት ይህንን መርህ ከተጠራጠርክ እነሆ ከሴቶቹ ሰፈር “የትዝታዋ ንግሥት!” ልትባል የምትችል ሴት ናትና በዛወርቅ አስፋውን ተጋበዛት….ያው ውበት ከሆድና ከምትመገበው ምግብና ከምትኖረው አኗኗርም ይመጣልና ዛሬ ላይ ብታያት ያኔ እኔና አንተ እንደምናውቃት ላትለያት ትችላለህ ወዳጄ….ምን ለማለት ፈልጌ ነው?! “ገንዘብ የማይቀይረው ምንም ነገር የለም!” ለማለት ፈልጌ ነው….እናማ በአንድ ሙዚቃዋ “በድህነቴ ላይ ማህተቤን እወዳለሁ!” ምናምን ካለችና ድሆች የሚወዱትን “ባዶ ህሊና” ካዛከረች በኋላ “ሳለ በእጄ ሁሉ ከደጄ!” በሚለው አገራዊ ብሂል መሰረትነት መሪውን ታዞረዋለች፡-

“ገንዘብ ሰርገኛ ነው - ሰው ሲያቀርብ ሰበስቦ
ድህነት ግን ሲያርቅ - ይመስላል ተስቦ፡፡”

ያው ለድህነት ሌላ ስም ስትሰጠው አቻ ያደረገችለት “ተስቦ”ን ነው፡፡ የተስቦን ምንነትና አስፈሪነት ላብራራልህ ብል ካንተ ከባለቤቱ የተሸለ አልገልፀውምና….እንደፈረደብህ አንተው ተጠበብበት….አሃ! የምሬን ነው’ኮ የእናንተ ችግር ነዋ! ካሻህ ደግሞ ኮሮና ተህዋሲ የፈጠረውን ፍርሃት አስበው፣ ይባሰኝ ካልክ የ-HIV AIDS-ህምም ይሰጠው የነበረውን አስፈሪ ምስል አስታውስና ስለአመልህ ብልሹነት ሳይሆን ስለኪስህ ባዶነት በእነዚህ አስፈሪ ተስቦዎች ልክ ሲርቁህ ሳለው….አዎ ተግባብተናል፡፡

መልክዓ ድህነት….

ዕድል ከሌለህ ድሃ ትሆናለህ….ድሃ ስትሆን ደግሞ ግብሩን ወስዳችሁ ስያሜውን ሰጣችሁን እንጂ ህሊና ይሉት ነገር አይኖርህም…..ወዳጄ! የእኔ መደቦች አይደሉምኮ ገድለው የሚፈትሹህ፣ ጤፍን ከጄሶ አዋህደው “እንጀራ” የሚሸጡልህ፣ በሰላም ወጥተህ ምግባትና መኖርንም የሚከለክሉህ…..ያንተው ጉዶች ናቸው! በስላቃችን መግቢያ ክፍል ላይ ያስተዋወቅኩህ አለማየሁ ገላጋይ የተባለ ጠበቃችሁ ስለድህነት ምንጭ የከተበውን አንብበህም አልነበር? እስኪ ደግሞ ከዘነበ ወላ “ማስታወሻ” ላይ ጋሽ ስብሃት ለአብ ገ/እግዚአብሄር የድህነትን አስቀያሚ መልክ ከራሱ የህይወት ልምድ ሲገልፀው ላስነብብህማ፡-

“….ቤተሰቡ ሁሉ ቢትርና ቢግርም በጣም ድሆች ነበርን፡፡ በጠቅላላ የምንችለውን ያህል ሁሉ ሰርተን የድህነት ሰንሰለትን መበጠስ አልቻልንም….ድህነት ስልህ የከፋውንም በዚያው በህፃንነት ዕድሜዬ ውስጥ አይቻለሁ፡፡ አሁን ሰውዬውን ረስቻቸዋለሁ፡፡ የልጁን እናት ነው የማስታውሳቸው፡፡ አንዲት ላም ብቻ ነበረች ያለቻቸው፡፡ ትታለባለች፡፡ ልጅ ራበውና ከእርጎዋ ላይ ሰረቀቆ ተጎነጨላት፡፡ እናት ከውሏቸው መጥተው እርጎዋን ሲያዩ ተሰርቆላታል፡፡ ልጃቸውን ጠርተው ጠጥቶ እንደሆነ ጠየቁት፡፡ ልጅ ካደ፡፡ ‘በል ቶሎ ላባ አምጣልኝ!’ ብለውት እንዳመጣላቸው አፉን አስከፈቱት፡፡ ዶሮ ላባዋን አፉ ውስጥ ከትተው ጉሮሮውን ኮረኮሩት፡፡ ልጁ አስመለሰው፡፡ እርጎዋም ወጣች፡፡ “ይቻት ወተቴ!” አሉ እናት….ድህነት እዚህ ድረስ አስጨንቆ ልጃቸውን ‘ብላልኝ፣ ጠጣልኝ!’ ከማለት ይልቅ የልጅህንም ሆድ ያስፈትሽሃል፡፡”

አየህልኝ አይደል ወዳጄ….የድህነት ክፋትና መልኩ ይህንን ያህል ያስቀይማል፡፡ ከፈጠሪ ሲለጥቅ “ሩህሩህና አዛኝ” የምትባለውን እናትን እንኳ ይፈትናል…..አትፍረድ! ወደነጥባችን ስንመለስ ደህንነታችንን እና ሀብታችንን ለማስጠበቅ ከአስርቱ የዓለማችን እጅግ ድሃ አገራት አንዷ በሆነችው አገራችን ጦቢያ በሀብታም ስም የሚኮፈስ ቢሆንም መንግሥትን እንደግፈዋለን፡፡ በእርሱ በኩል ከምናስቀጥራቸው ድሃ የፖሊስ አባላት በተጨማሪ በእጅ-አዙር የምንረዳቸው ባለሥልጣናት “ኤጀንሲዎችም” አሉልን…..እነዚህ ኤጀንሲዎችም እኛ ከምንከፍላቸው ሩቡን ብቻ እየሰጡ የሚያመጡልን ድሃ ዘበኞችና የፅዳት ሰራተኞች አሏቸው፡፡

እናልህ ወዳጄ….ፖሊሱም፣ ዘበኛውም ሆነ ፅዳቷ….እኛንና ንብረቶቻችንን እየጠበቁ “ድሃ” ሆነው አኗኑረው መሞታቸው ሳያንስ መበዝበዛቸው ያንገበግባል….አንዳንድ ባለ-ህሊና የመንግሥት ባለሥልጣናትና መገናኛ ብዙኃኑ ሊዘምቱባቸውና እነዚህን ጭቁን ድሃዎች ቢያንስ ለስራቸው የሚመጥን ክፍያ እንዲያገኙ ሊሞክሩላቸው ቢነሳሱም “በረጅሙ እጅ” ጉዳዩ ዝም እንዲልና ያ ሁሉ ጨዋታ እንዲበርድ ሆኗል አዎ! ዕድል ከሌለህ ድሃ ትሆናለህ….የሚሊዮን ብሮችን ሀብት እየጠበቅክም ሆነ የባለሚሊዮኖችን ነብስ እያጀብክ ታኗኑራለህ፡፡ ስራ ልልቀቅ ብትል ሊተኩህ ያሰፈሰፉ ሚሊዮኖች ናቸውና የሚያስቀርህ አይኖርም፡፡

እጀ-መንገዴን….ሰሞኑን አንድ የመንግሥት ሰው ያሉትን ሰምተህ ይሆን? ለነገሩ ለዕለት ጉርስህ ስትሮጥና ስታንጋጥጥ እየዋልክ በምን ጊዜህና ልቦናህ ትሰማቸዋለህ….ለማንኛውም ሹምዬው በስጋትነት ፈርጀውሃል! አዎን! ባል-ሥልጣኑ እንዳብራሩት ከሆነ “ድሃ ወጣቶች” የሚበዙባቸው አካባቢዎች ጉዳያቸውን በገንዘብ ማስፈፀም ለሚፈልጉ ኃሎች ምቹ ቀጠናዎች ናቸው ብለውሃል….የዚህ ቱርክኛው ደግሞ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የግብፅና ሱዳን ተላላኪ ልትሆን የምትችለው ድሃ ስትሆን እንደሆነ ታምኗል….ሽብርተኛ ድርጅቶችም ሊመለምሉህ የሚሰናዱት በዚሁ መስፈርትነት ነው ብለውሃል፡፡ ያንተን ነፃ-ፈቃድና አለን የምትለውን “ሞራል” አልጠቀሱም ሹምዬው….አይዟችን ወዳጄ!

ድሃ እና ድህነት….

በእርግጥ….”የኑሮ መጠንሽን ከኔ ጋር አትለኪ!” የሚለውን የትዝታውን ንጉስ ጋሽ ማህሙድ አህመድ ሙዚቃ እያደመጥሽ ተከተይኝ እንጂ ይሄ ጉዳይ አንቺን ጠብሻሟን ሴቲትም የምለከታል፡፡ ለጥቂት የገንዘብ ኖቶች ስትይ ያለፍላጎትሽ የምትገቢባቸው አጓጉል ህይወቶች በርካታ ናቸውና….ደግሞስ በወጣትነት ዘመን ያልመጣ ብር እምብዛም ደስታን አያመጣም፡፡ “ብልጥግናው” ውግንናውን ከእኛ ሰፈር አድርጓልና ሙሽሮቻችን ፎቶ ስለሚነሱበት ቦታ ማማር እንጂ እናንተ ስራ ሰርታችሁ “ሰው” መሆን ባትችሉ እንኳ በልታችሁ እንድታድሩ ስለሚያስችሏችሁ የስራ ቦታዎች ጉዳዩም አይደለም….ስለመዝናኛ ከተሞች ግንባታና ስለብልጨታቸው እንጂ ስለኢንዱስትሪ መንደሮች መስፋፋትም ብዙም አይገደው!

በቅዱሳን መፃህፍቱ “ጥረህ ግረህ ብላ!” ተብሏል፡፡ ወዳጄ ሆይ! ድህነት ተፈጥሯዊ ነው ወይስ ኔልሰን ማንዴላ እንደነገረን ሰው ሰራሽ? ማለቴ “ሃብታም ሰራሽ” ነው? የሚለው አሁን ድረስ እያሟገተ ቢኖርም አንተ ወዳጄ ድሃ የሆንከው እኔ ሃብታም ስለሆንኩ ነው ብለህ ታምናለህ? ወይስ ድህነትን በስላቅ የሚገልፀው በዕውቀቱ ስዩም በአንድ የኀሰሳ ስጋ ግጥሙ እንደሚናገረው ያንተንና የሌሎችንም እልፍ ከሲታሞች “ድርሻ” በስግብግብነት ስለወሰድኩ ይሆን? ....እስኪ እንደርስበት ይሆናል፡፡ የሆነው ሆነናስ…..ቁር እየቀጋህ ኖረህ፣ ያንን ጉንጭ አልባ ፊትህን ህ.…ዘባተሎህን ለብሰህ.…አንዱ ግልገል-ሊበራል ፖለቲከኛ ይነሳና “ድህነት ምርጫ ነው!” የሚል ኢንተርቪው ሲሰጥ ትደርሳለህ፡፡ አንተ ወዳጄ ይህንን ድህነትህን በቨምርጫህ የምትኖረው የሚመስለው ስንት ከንቱ አለ መሰለህ! አላጋጮችም አንጀትህን ቢያደብኑት አትፍረድ.…ባይሆን ሄደህ ስለድህነትህ አረቄ ቤት ተጣድ -  እናቱን ድህነት!

ድሃ ስትሆን…..ዓለምን እንኳንስና በአካል በቴሌቪዥን እንዳታውቃት ትሆናለህ….አሁን አንተ ይሄን ፅሁፍ በምታነበብት ቅፅበት ዓለም እየተነጋገረበትና በጉጉት እየጠበቀ ያለው አኗኗርን ማቅለያ (Technologies) ምን እንደሆነ እንኳ አታውቅም….ምርጫና አማራጮች የሉህምና አገርህን እንኳን ለማወቅ ኪስህ አይፈቅድልህም….እዚያው ከተወለድክበት መንድር ኖረህ ትደፋለህ! በቃ ታሪክህም በዚህ መልኩ ይደመደማል፡፡ በአንፃራዊነት የእናንተ የድሆች ጠበቃ የነበረው አቶ መለስ ዜናዊ እንኳን እንዲያ ሲያመሳቅልህ ላቀረብከው የ“እትብቴ የተቀበረበት ሰፈር ነው!” ንጭንጭህ የሰጠውን መልስ ታስታውሳለህ አይደል….አዎ! “የልማት ተነሺ” ማለት በሌላ ስሙ “የድሃ-ድሃ” ማለት ነው፡፡ የማይችል፤ አቅም የሌለው፤ ከከተማ ወጥቶ በከተማ ዳርቻዎች የሚሰፍር ማለት ነውና….ለእኛ ለአልሚዎቹ ለምንችለው ትለቃለህ - አበቃ!

ሥነ-ልቦናዊ ንቅለትህ ይቆየንና ህግጋቱም እንኳ ጠንካራው ደካማውን ቢያጠቃው አይከላከሉለትም፡፡ እስኪ ከመሞት መሰንበት፣ ማምሻም ዕድሜ ነው፣ ኑሮ ካሉት መቃብርም ፍሪጅም ይሞቃሉ….እያልክ ኑር ማለቴ አኗ-ኑር፡፡ በእርግጥ ገንዘብ ከድህነት እንጂ ከሞት አያስጥልም….ቢሆንም ግን ኖሮ መሞትና አኗኑሮ መሞት ይለያያሉ…ሲኖርህ ላጥ ታደርጋለህ! ከሌለህ ለጥ ነው የምትለው፡፡ አይዞህ ወይ አምሮህ አምሮህ ይተውሃል ወይም ደግሞ አምሮትህ በማየት ይወጣልሃል፡፡ አንድ የታክሲ ረዳት፡-

“ይበላል በገንዘብ
ይጠጣል በገንዘብ፤
ትርፍ ካልተጫነ
ኬት ይመጣል ገንዘብ?
እንዳትጨቃጨቅ ይህንን ተገንዘብ!” ብሏል አሉ፡፡ የውሸት ኑሮ ግን የእውነት ሞት ያሳዝናል! አዎ….ድሃ እጅግ አድርጎ መውድ ያለበት ነገር ቢኖር ሞትን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉንም ሰው በፍትሃዊነት “እኩል” የሚያደርግ ያው እርሱ ነውና……ከአቅም በላይና ከማን አንሼ መንጠራራት ግን ትርፉ ድሃ እንደጋጠው አጥንት መጋጋጥ ነው ክፉኛ! እንቁራሪት በሬን አክላለው ብላ እንደፈነዳችወ፣ አይጥም ለሆዷ ዝሆንም ለሆዱ ወንዝ እንደወረዱትና ድልድዩን ፣አንቀጠቀጥነው፣ እንዳለችው……አቅምህን አውቀህ ማህሙድ እንደዘፈነልህ ካልኖርክ ሞትህም እንደ አኗኗሪነትህ ሁሉ መልከ-ጥፉ ሊሆን ይችላል፡፡

ደግሞስ ምናባቱ! ለአንድ እንጀራ….እንዳትል አደራህን ወዳጄ! አንድ እንጀራ ብንበላም ልዩነቱ ወጡ ላይ ነው….ሲፈርድብህ ከአንቀልባ እስከ ሞትህ፤ ከገንፎ እስከ ንፍሮህ (ስትገባ አልቅሰህ ስትወጣ የሚያለቅስልህ አጥተህ!) ድሃሃሃ ሆነህ ኖረህ ነጭ ድሃ ሆነህ ትሞታለህ….ዕድልህ ነው ወዳጄ! የተፃፈ የአርባ ምናምን ቀን እጣ ፈንታህ….በሚቀጥለው ወግ እስካገኝህ የሀብት መንገድን ቢያንስ በሃሳብ ውሳኔህ ጀምረውና ድህነትህን ግን - ቻለው ግድየለም!

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :