መስፍናዊው ስንብት!

ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

Mesfin-Woldemariam-tributeOctober 5, 2020 (Ezega.com) -- በገፃችን ከስራዎቻቸው እየሰበዝን በአስረጅነት ስንጠቅስ የቀዳሚነቱን ቦታ የያዙት ጉምቱው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ናቸው፡፡ እኚህ አንጋፋ የአደባባይ ምሁርና አሰላሳይ በርካታ ወጣቶችን አስከትለዋልና ስለፖለቲካዊ ድፍረታቸው ያደንቋቸዋል፡፡ አደባባይ ለመውጣት ፍርሃት እጅና እግረ-ሙቅ የሆነባቸው የዕድሜና ዕውቀት ቀራቢዎቻቸው “ምሁራን” ደግሞ በአንድ ጎኑ ስለእርሳቸው ሲሰጉ በሌላው በኩል ደግሞ አድር ባይነትንና እበላ ባይነትን ስለሚጠየፈው ደፋር ብዕራቸው ለየኔታ መስፍን እጅ ይነሳሉ - ባርኔጣ ከፍ እያደረጉ፡፡

ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ስላመኑበት እውነት ሲሟገቱና ሲፅፉ፤ ኢትዮጵያዊነትን ከእምቢ ባይነት ጋር ሲያመዝኑና ብቻቸውን ብዙ ሆነው ሲደክሙ ኖረዋል፡፡ የያዝነውን “አዲስ ዓመት” ግባት ተከትሎ በመስከረም ጅማሮ ላይ “ተጠየቅ መስከረም!” ያሉትን ቆየት ያለ ግጥም በፌስቡክ ገፃቸው ላይ አጋርተውት ነበር፡፡ በግጥሙ መግያ ስንኞች ላይ “ምን ሰራህ?!” የሚል ሹፈታዊ ጥያቄ ለሚያቀርብላቸው ወርሃ መስከረም ምንም ባይነግሩትም ዕድሜያቸውን ጥንቅቅ አድርገው የሰሩና የኖሩበት ጋሽ መስፍን እስከመጨረሻይቱ ህቅታ ድረስ ሲፅፉና ሲናገሩ፤ ሲያነቡና ሲያስነብቡን መኖራቸው አይታበልም፡፡

“ተጠየቅ መስከረም - ዛሬስ ዋ ዛየለም!
አንተን ለመቀበል “እንቁጣጣሽ” እያልን፤
ከርስ እንሞላለን - እንሳከራለን፤ እንጨፍራለን፡፡
አልገባኝም እኔን አንተ መወደድህ፤
ስትገባ ስትወጣ ድግስ መቀበልህ፤
ዶሮው፤ በጉ፤ ሰንጋው ይታረድልሃል፤
ርጥብ ቄጠማና ደም መውደድህ ታውቋል፡፡
እንስማው ተናገር - የያዝከውን ነገር፡፡
ለኛ ያመጣኸው ስጦታህ ምንድነው?
ክፈተው ሣጥንህን - እስቲ እንመልከተው፡፡
ለምለሙን ሳር እንደሁ - ይጋጡት ከብቶቹ
ለኛለሰዎቹ - ለኛ ምን ይዘሃል
ሞት ሊጠፋ ነው ወይ ባዲስ ፍልስፍና

ከአዲስ አበባ የቀድሞ ፊውዳል ሰፈሮች አንዱ በሆነው ስድስት ኪሎ አካባቢ በ-1922 ሚያዝያ አጋማሽ የተወለዱት ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን ታሪክ፤ ሃይማኖቶችና ባህሎች፤ ሁሉአቀፍ ኩነቶችን በመተንተኑ ረገድ ቀዳሚው ሙያቸው ያደረጉት የሥነ-ዓለም (Geography) ሙያ አልገደባቸውም፡፡ ታሪክን ጠንቅቀዋል፣ ፖለቲካውን ተክነው ማህበረ-ኢኮኖሚውን በተመለከተም የሚሰነዝሯቸው ሃሳቦችና ትችቶችም ጠብ የሚሉ አይደሉም፡፡

“እንጉርጉሮ” የሰኟት የግጥሞች ስብስብ መድብል አለቻቸውና ገጣሚም ነበሩ፡፡ ፀሀፊ፣ መምህር፣ ፖለቲከኛና ከሁሉም በላይ ብርቱ የሰብዓዊ መብቶችና እኩልነት ተሟጋች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያችንን መልክ የቀየሩትን ችጋሮች “ጠኔ” ሲሉ በመሰየም ሰሚ ባያገኙም መፍትሄ ያሉትን ለአራቱም መንግሥታት ሲያቀርቡ ኖረው አልፈዋል፡፡ መተቸትና ችግሩንም መጠቆም ለመፍትሄ ማፋለጉ የሚሰራ ቀዳሚ ስራ መሆኑን ያልተረዱ “ስራቸው ሁሉ መተቸት ብቻ ነው!” ቢሏቸውም በተግባር ቦታዎቹ ድረስ በመሄድ፤ ስለጉዳዩ በማንቃትና ዕርዳታ ጭምር በማሰባሰብ በየወቅቱ ህዝባችንን ስለሚመታው ችጋር ታግለዋል፡፡

ኖሮ የመሞት ክብር!

አንጋፋው ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ በአንድ ፅሁፉ ከወሎ የጁና ከሸዋ የመጡት የፕሮፌሰር መስፍን ወላጆች መስፍንን ሲሰጡን ጋሽ መስፍንም የሁለት ሴት ልጆች አባት እንደሆኑ መፃፉን አንብቤያለሁ፡፡ በቤተ-ክህነት ትምህርት የድቁናን ማእረግ አግኝተዋል የሚለን አለምነህ ትምህርት ጠል የነበሩበትን ጊዜም ያወሳል፡፡ ሁለቱም ሴት ልጆቻቸው በህክምና ሙያ ውስጥ ያሉ ዶክተሮች ሲሆኑ አንጋፈዋ ዶ/ር መቅደስ መስፍን ከሁለት ሳምንታት በፊት የኔታ በኮሮና ተህዋሲ ሳቢያ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ገብተው በነበረበት ወቅት:- “ላሰባችሁልኝ ሁሉ እግዚአብሔር ያስብላችሁ፡፡ እኔ ደህና ነኝ!” የሚል መልዕክት ከአባቴ አምጥቻለሁ ብላ ለወዳጆቻቸው መፅናናትን ሰጥታም ነበር፡፡

ዶ/ር ሰማያት መስፍን እምብዛም በሚዲያዎች አትገኝም፡፡ እህቷ ዶ/ር መቅደስ ግን በአንድ ወቅት “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ “የእሳቸው ልጅ በመሆንሽ ምን ይሰማሻል?” ተብላ ስትጠየቅ “የእሱ ልጅ በመሆኔ በጣም በጣም ነው የምኮራው! በነገራችን ላይ እናቴም ያልተዘመረላት ጀግና እንደሚባሉት አይነት ነች….እኔም ከነሱ በመፈጠሬ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡” ብላ እንደነበርም አስታውሳለሁ፡፡ ፕሮፌሰሩ ከልጆቻቸው እናት ጋር አልነበረም የሚኖሩት፡፡ በተለይ የሚታወቁበት ሥልጣንን እና ባለ-ሥልጣናትን ያለማቋረጥ “መጎንተላቸው” ማብቂያ ያገኘውም እስከህልፈታቸው ድረስ ሂሳዊ ድጋፍ ከሰጡትና ተስፋም ካልቆረጡበት የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አገዛዝ ላይ ብቻ ነው፡፡

በዚህች ማስታወሻም “ኖሮ መሞትስ እንደ…..!” ከሚባልላቸው የአገር ሰው ሆነውና ከአገር ሰውጋ በአገር ኖረው ስላለፉት ፕሮፍ ስራዎች እያስታወስን አስትምህሯቸውን እናዘክራለን፡፡ “ክፉ ቀን ጥሩ ነው፡፡ ያለፋል እንጂ ያልፋል፤ የመጪው ጥሩ ቀን ምልክትም ነው፡፡” የሚሉትን ፕሮፍ ሞት ሰምተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ “የሃሳብ ልዕልና ምልክት፣ የሠላማዊ ትግል አርዓያ፣ ላመኑበት ነገር እስከመጨረሻው ሞጋች፣ ላመኑበት እውነት ብቻ የሚቆሙት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በማረፋቸው ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶኛል፡፡” ሲሉ ርዕሰ ብሔራችን ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴም ለቤተሰቦችና ወዳጆቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደርም ይህንኑ ፈለግ መከተላቸው መልካም ጅምር ሆኗል፡፡ ከሙዚቀኛው ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጀምሮ ሌሎች በርካቶች ሐዘናቸውን ገልፀዋል፡፡

የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀፍሬ ስብሀት “‘እገሌ’ኮ አረፈ!’ ስንባል ይሰማን የነበረ ድንጋጤና ሩህሩህ የአዛኝነት ስሜት ወዴት ጥሎን ሄደ? እንዴትስ አንድን አረጋዊ መምህር በሀገር ወግ አልቅሰን ለመቅበር ተሳነን? ሙት ወቃሽነትን ከማን ተማርነው?!” ብሎ በአግራሞት እስኪጠየይቅ ድረስ “አማራ የሚባል ብሔር የለም!” ማለታቸውን ከሚያወግዙት ጀምሮ ኦሮሞ-ጠል ናቸው እስከሚሉት ድረስ ከባህላችንም ሆነ ከሰብዓዊ እሴት በተፃራሪ ሲረባረቡ መስተዋላቸው እንግዳ የሆነባቸው በርካታ ነበሩ፡፡

እርጅና ለፕሮፌሰሩ ልዩ ሁኔታ (Exception) ሆኖ አበርትቷቸዋልና በአንድ ተራ የፌዴራል ፖሊስ አባል በጥፊ እየተመቱ ሳይቀር ተጋፍጧቸውን አላቆሙም፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ኦበናንግ ሜቶ “Today Ethiopia lost one of its greatest saint sons and a true patriot, Prof. Mesfin Woldemariam.” ያለላቸው ፕሮፍ በአጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ ሆነውም ለወጣቱ እንዲደርስ እፈልጋለሁ ያሉትን “ዛሬም እንደትናንት?” የሚለውን የመጨረሻ መፅሃፋቸውን በወራት ውስጥ አድርሰዋል፡፡

ፕሮፍ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን አሁናዊ አጠራሩ እንጦጦ፣ ሁለተኛ ደረጃን በኋላ ላይ በመምህርነትም ባገለገሉበት እቴጌ መነን ተምረዋል፡፡ ከለንደን ጀምሮ በህንድ ፑንጃብና በአሜሪካ ክላርክ የድረ-ምረቃቸውን በመከታተል ዶክትሬታቸውን ወስደዋል፡፡ ለረጅም ጊዜ ባስተማሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል በመምህርነትና ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ ለእርሳቸው ኢትዮጵያዊነትን “ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?” ሲሉ ባሳተሟት የቆየች መፅሃፍ ከገለፁትም በላይ “ችግርን መካፈል” ነውና የህዝባቸውን ጩኸት ሲጮሁ፣ ችግሩን ሲካፈሉና ድምፅ ሲሆኑለት ኖረው አልፈዋል፡፡ በውጪ አገር አስተምረውና ተመራምረው ዶላራዊ ኑሮ መኖርም ትርጉም ያጣባቸው በዚሁ ባህሪያቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

መስፍን፤ ሰብዓዊ መብቶችና ፖለቲካ….

ፕሮፌሰር መስፍን እንደየትኛውም ፊደል ቀመስ ለፖለቲካ ቅርበት የነበራቸውና ተሟጋች ተማሪዎችንም ይደግፉ የነበረው ከዘውዳዊው አገዛዝ ጀምሮ ቢሆንም አገዛዙ በሹመት ሊያከሽፋቸው ለትንሽ ጊዜም ቢሆን የሰሩበትን “የጊምቢ ገዢነት” በመተው በመደበኛው ፖለቲካን የጀመሩት ከአካዳሚያዊ ነፃነትጋ በተያያዘ በተካሄደው ጉባዔ ሳቢያ ግርግር ሲከተልና ከወዳጃቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ቦንግር ጋር ለአጭር ጊዜ ሲታሰሩ ነው፡፡

ይልቁንም ከታሪካዊው ምርጫ-97 በፊት ፕሮፌሰሩ የሚታወቁት በምሁርነት፣ በሰብዓዊ መብቶች ተነሟጋችነትና ተቺነታቸው ነበር፡፡ ዓብይን የችግሩ አካል ባለማድረጋቸውና በተለይም አምባገነን እንዲሆን ፈቃድ ያሳየ በሚመስሉ የቅርብ ጊዜ ፅሁፎቻቸው ብዙኃንን ያስከፉት ፕሮፍ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲን በአባልነትም በተወዳዳሪነትም ባይሳተፉበትም ከወዳጆቻቸውጋ አዋልደውት ታስረውለታል፡፡ ከዚያ በፊት ባቋቋሙት “ቀስተ ደመና ለማህበራዊ ፍትህና እኩልነት” የፖለቲካ ማህበር በኩልም ታግለዋል፡፡

በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በአማርኛና እንግሊዝኛ በርካታ መፃህፍትን ያስቀሩልን ፕሮፍ ከፖለቲከኛነቱ ይልቅ “ህገ-አራዊት ነው!” የሚሉትን ጭንቅላት አቀጫጭ የጉልበት አገዛዝ ለማጋለጥ ከህግ ባለሙያ ጓዶቻቸው ጋር በመሆን ያቋቋሙትና ተገድዶ ስያሜውን ከመቀየሩ በፊት በያኔው አጠራሩ “የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ” ሰኝተው ያቋቋሙት ቀዳሚ የሰብኣዊ መብቶች አንቂና ተቆርቋሪ ድርጅት ይዘክራቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

ይህ በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ላይ ሲሰራ የቆየው አንጋፋ ተቋም ከኢህአዴግ መንግሥት ሽግግር ምስረታ ሰሞን በመስከረም 29/1984 የተመሰረተ ሲሆን በሳምንት አንድ ቀን ለአስር ደቂቃ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ግንዛቤን ለመፍጠር ጠይቆ የአየር ሰዓት መከልከሉም የታሪካችን ክፉ አካል ነው፡፡ ከነጉድለቶቹና ፕሮፍ ሊያዩት በሚፈልጉት የበቃ ቁመና ላይ ከነአለመድረሱ በተለያዩ የኢትዮጵያችን አካባቢዎች የሚፈፀሙ መንግሥታዊ ጥሰቶችን የሚያጋልጥ ነው፡፡ በእርግጥ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስተማርም ሆነ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶችን ተርጉሞ ለማሰራጨት የመጀመሪያው ባይሆንም ዋነኛው ነው፡፡

ፕሮፌሰሩ የመጀመሪያዎቹን ዓመታት በስራ አስፈፃሚ ኃላፊነት የመሩትና ዋጋም የከፈሉበት ይህ ተቋም በርካታ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችን አፍርቷል፡፡ ማክሰኞ ለዕረቡ አጥቢያ መስከረም 19/20 ቀን 2013 በመንፈቅ-ሌት አርፈዋል መባሉ ከተሰማ በኋላ የሰብዓዊ መብቶችና የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪና አንቂ (Human Rights & Environmental Activist) ለሆኑት የቀድሞ መሪው ከወራት በፊት ምስጋናና ዕውቅና የሰጠው ተቋም ወዲያው ነበር ማዘኑን የገለፀውና ለህግ ልዕልና ወሰብዓዊ መብቶች ክብረት የጤናና የዕድሜ ሁኔታቸው እንደፈቀደላቸው ስለሰሩ ምስጋናውን ያደሰው፡፡

የቀለም ቀንዱ ፕሮፌሰር “የዶ/ር ዓብይ ራዕይ” እንዲሳካ ሲሽቱ ብልፅግና ኢዜማ የገለፀውን ቆሻሻ “አብዮታዊ እርምጃ!” ባሉት መንገድ እንዲያፀዳ ከመንገርም አልቦዘኑም፡፡ የቀደመ የጤና ችግራቸው በተለይም ከመተንፈሻ አካል ጋር የተያያዘው የአጋዥ መሳሪያ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሲታገዙ የሰነበቱት ሊቅ ህልፈት የሃሳብ ገበያውን በብዙ እንደሚጎዳ እሙን ነው፡፡

የአሰላሳዩን መስፍን የተበታተኑ ስራዎች በቅርብ ጊዜ ሰብስበ አድርጎ ማንነቱን ያላወቅኩት ሰው ቀዳሚውን ቅፅ “አድማጭ ያጣ ጪኸት” ሲል ለንባብ ማብቃቱ መልካም ጅምር ሲሆን ፕሮፍ የደርግ ሥርዓት ወድቆ የተመሰረተው መንግሥት የሰጠውን ተስፋ ለመርዳት ሁለት ዓላማዎችን ይዞ ስለቆመው ሰመጉ ሲፅፉ “ኢሰመጉ ከየት ወዴት?” በማለት ለትውልድ የሚተላለፍና ስምን ሲያስጠራ የሚኖር እንደሆነ ጠቅሰው ሀብቶቼ የሚሏቸውን መፃህፍት ለአዋሳው ቅርንጫፍ ሲያወርሱት ከአዋሳ ለአብያተ-መፃህፍት የሚሆን ቦታ የነፈገውን መንግሥታዊ ሥርዓትና ቤተ-መፃህፍቱን በስሙ ለማስጠራት የሚፈልግ ፈቃደኛ ግለሰብ እንኳ ያለመኖሩን በማስታወስ ሥርዓተ-ማህበራችንን ግን እንዲህ ታዝበውት አልፈዋል፡-

“በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ሰዎች ለኢሰመጉ ሀብት ማውረስን ቢለምዱ የኢሰመጉ ዓላማዎችን ለማስፋፋትና ማህበረሰባችንን ወደተሻለ አቅጣጫ ለመግፋት የተሻለ ኃይል ይኖር ነበር….የኢሰመጉ መክሳት የማህበረሰቡን መክሳት የሚያመለከት ነው፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ማህበረሰቡ ኢሰመጉን በሚገባ ባለመደገፉና እንዲከሳ በማድረሰጉ ራሱንም አከሳ፡፡ ራሱን ጎዳ፡፡ እስከዛሬ አንድም ባለሃብት ለኢሰመጉ ቋሚ ሀብት ያወረሰ አለመኖሩ አስተሳሰባችን ከግለሰብ ወደማህበረሰብና ወደ ትውልድ አለመሸጋገሩን ያመለክታል፡፡ ዛሬም ቢሆን ማህበረሰቡ የኢሰመጉን መንፈሳዊ ተልዕኮ በትክክል ተገንዝቦ ኢሰመጉን በመርዳት ራሱን ለመርዳት የሚያስችለው ደረጃ ላ ገና አልደረሰም፡፡” ብለው ነበር፡፡

ይሄ አገላለፅ ብርቱ ህመምን የያዘና ለአንባብያኑም የሚሰጥ ነው፡፡ አንዳንዶች “ምሁራዊ ትምክህት” የሚሉትን ባህሪ ፕሮፍ ፊት-ለፊት ይናገሩታልና የዚህን ቃል ተፈጻሚነት ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ፕሮፍ የከኖሩባቸው ዘጠናን ተሻጋሪ ዓመትና ወራት የባከነ እምብዛም ይመስለኛል፡፡ ቁጡና ተቃራኒ ሃሳብን የማይታገሱ ቢሏቸውም ለስልጡን ውይይት ምቹ ነበሩ፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት ሙሉ ጉዳዩን በእርሳቸው ዙሪያ አድርጎ ለተዘጋጀው “አሻራ” መፅሄት ይህንን ነግረው ነበር፡- “አንድ መፅሃፍ በቅርቡ ለንባብ አበቃለሁ፡፡ ርዕሱን ‘አዳፍኔ’ ብዬዋለሁ፡፡ ‘መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ’ የተሰኘው መፅሃፍ ተከታይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ መክሸፍ የሚለው ቃል አልገባ ያላቸው አዳፍኔ ይገባቸው እንደሁ ብዬ ነው፡፡ ዘቱም ሁሉንም አዳፍኖ የሚጓዘውን የአምባገነንት አካሄድን አመላካች ነው፡፡ ጭቆናን፣ ኋለ-ቀርነትን፣ የንዋይና የሥልጣን ፍቅርን፣ ክህደትን የሚያሳይ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ እያነበበ የማያነብ፣ እየጠየቀ መረዳትን የማይፈልግ ሰው አይወዱም ነበርና በእነዚህ መፃህፍቶቻቸው ከብዙዎች ጋር በብዕር ተቆራቁሰዋል፡፡ ከንግግራቸው ይልቅም ብዕራቸው የሰላ ነበር፡፡

የመርማሪ ኮሚሲዮኑ ነገር….

ሰብዓዊ ክብርን ወድደው መጠቃትንና ግፍን የሚጠሉት መስፍን በአንድ ወቅት እንዴት መታወስ ይፈልጉ እንደሆን ተጠየቀው ያ ብዙም ግድ እንደማይሰጣቸው ተናግረው ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖ የእርሳቸው ስም ሲነሳ አብረው ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ ጨፍጫፊው የደርግ ስርዓት ያለህግና ፍርድ በአብዮታዊ እርምጃ ያስወገዳቸውና በድግግም “ስልሳዎቹ” እየተባሉ የሚጠሩት የዘውዱ ባለሥልጣናት ጉዳይ አብሮ ይነሳል፡፡ ደርግ ሥልጣን እንደያዘ ባቋቋመው መርማሪ ኮሚሲዮን ውስጥ የሰጡት ምክረ ሃሳብን በተመለከተ በተደጋጋሚ መልስ የሰጡበት ቢሆንም የኢህአዴግ አመራሮች በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሳይቀር ይህንኑ እያነሱ ያሳቅሏቸው እንደነበር አይረሳም፡፡ እንዲያውም ፕሮፌሰሩ አንድ የኢህአዴግ ሰው “ዘአማን በላይ” በሚል የብዕር ስም “ፕሮፌሰሩ ከፍርድ ውሳኔ በፊት የሰጡት ብይን!” ሲል የፃፈውን በራሳቸው ገፅ https://mesfinwoldemariam.wordpress.com በኩል በማጋራት እንዲነበብ እስከመተባበር ደፍረዋል፡፡

እርግጥ ነው ስህተት ከሰራ የማይወቀስ ማንም አይኖርም፡፡ ጭቆናን ሳይሆን ጨቋኙንና የጨቋኙን ብሔር በሚጠላ ሥርዓተ ማህበር ውስጥ ግን ሙትን መውቀስም ተገትቶ ከንቱ ውዳሴ ይዘንባልና ይህንን ማሰልጠን እስካልተቻለ ጉዳዮቻችን ሁሉ ከአሉባልታ ያለማለፍ ዕድላቸው የጠበበ ይሆናል፡፡ እምቢ ባይነትን አብዝተው የሚወዱትና ለጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያምም ያልገበሩት የኔታን መልካምን ለማድነቅን ክፉን ለመተቸትና ቢያንስ በመተባበር ላላመደገፍ በሚኖራቸው አቋም አላማቸውም፡፡ ጀርባቸውን ለህዝብ ከሰጡና በእንግሊዝኛ ብቻ አልያም ቅድሚያ በእንግሊዝኛ ከሚያሳትሙ ምሁራን የሚለያቸው ህዝቡን ማወቃቸው፤ መስለውት መኖራቸውና ፊት-ለፊት እየተጋፈጡ ማንቃታቸው ይመስለኛል፡፡

በመጋቢት 2011 ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ ማህሌት አብዱል ጋር ስማቸውን ሲያጠለሽ በኖረው “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ ቆይታ ነበራቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ ጋዜጣዋን ያነብቡ እንደሆነና ስለመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች ተጠይቀው እንደሌሎች እዚህ ስማቸውን የማልጠቅሳቸውና በዚያው የለውጥ ሰሞን ቃላቸውን ለጋዜጣዋ ከሰጡ ምሁራን በተለየ ይህንን ነበር ያሉት፡- “ኢህአዴግ ከገባ ጥቂት ጊዜያት ወዲህ አላነብም….ደግሞ ምን ለማድረግ ነው የማነበው? ምን አዲስ ነገር ለማግኘት? ደግሞ ከእናንተ ይልቅ የግሉ ፕሬስ ደፋር ፅሁፎችን ይዞ ስለሚቀርብ አነባለሁ፡፡ የግሉ ሚዲያ ወኔ አለው፡፡ እናንተ ጋር ያለው የእንጀራ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ድሮም ሆነ ዛሬም ያው ነው፡፡ ዛሬ ተለወጠ ተብሎ ነገ እዚያው መስመር ውስጥ ነው ያላችሁት፡፡ ለእውነት ብላችሁ ሳይሆን የምትሰሩት ለእንጀራ ብላችሁ ነው….እናንተም ደመወዝ መንግሥት ስለሚከፍላችሁ ብቻ የእሱ-አፍ ለመሆን ፈቃደኛ ሆናችሁ ነው የምትገቡት፡፡ አብዛኛው ባለሙያ እበላ ባይ ነው፡፡ ሁላችሁም ወፍራም እንጀራ ለማግኘት ነው ጥረታችሁ፡፡ በበላችሁት መጠንም ይበልጥ ታመሰግናላችሁ፡፡ ካላመሰገናችሁ እንጀራው ይቀጥናል፡፡ ይህ ነው እውነታው”

እንዲህ ያሉት እውነተኛ የኔታ መስፍን ስለሞት ብዙ ፅፈዋል፡፡ በተለያየ ጊዜም አነጋጋሪ ኑዛዜዎችን አድርገዋል፡፡ “ፃዕረ ሞትና መስፍን ወልደማርያም” ባሉት ሀቲታቸው ላይም አንድ ሁለት….እያሉ አምስት ድረስ የቆጠሯቸው ከሞት ጋር መፋጠጦችን ነግረውናል፡፡ በእንጉርጉሯቸውም “ሞት ማለት…” ይምትል ግጥም አለቻቸው፡፡ ስድስተኛው ጣዕር ለሞት እጅ አሰጥቷቸው እነሆ ይህ ፅሁፍ በሚነበብበት ዕለት ሥርዓተ ቀብራቸው እየተፈፀመ ነው፡፡ በፀጋዬ ገ/መድህን “የብዕር ሞት” እጅ ነስተንና ባርኔጣችንን አውርደን በክብር እንሰናበታቸው፡፡

“የቃለ ልሣን ቅመሙ - የባለቅኔ ቀለሙ
ነጠበ እንጂ ፈሰሰ አንበል - ቢዘነበል እንኳ ደሙ
ሰከነ እንጂ ከሰለ አንበል - ቢከሰከስ እንኳን ዐፅሙ፡፡
የቃል እሳት ነበልባሉ - አልባከነምና ውሉ
የዘር ንድፉ የፊደሉ - ቢሞት እንኳን ሞተ አትበሉ፡፡”

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :