የቤንሻንጉሉን ተደጋጋሚ ግድያ በመምራት የተጠረጠሩ 504 ሰዎች ተያዙ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Benishangul-GumuzOctober 16, 2020 (Ezega.com) -- በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን በርካታ ንፁኃን ዜጎች እንዲገደሉ በማስተባበርና በመምራት የተጠረጠሩ 504 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ገለጹ፡፡ የአማራና የቤንሻንጉል ክልሎች ርእሳነ መሥተዳድሮች አቶ ተመስገን ጥሩነህና አቶ አሻድሊ ሐሰን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በተገኙበት በክስተቱ ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም በተደጋጋሚ በክልሉ መተከል ዞን በንፁኃን ላይ በሚፈፀመው ጥቃት ውስጥ የህወሃት እጅ እንዳለበት ደርሰንበታል ብለዋል። "ለውጡን ተከትሎ ያኮረፉት እነዚህ አካላት ከሚፈጥሩት የፀረ ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ" በተጨማሪ ከመሬት ይዞታ ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውንም አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡ በተለይ አቶ አሻድሊ ሃሰን ህወሃት ይህን ድርጊት ለማስፈፀም ወጣቶችን በመመልመልና አንዳንድ በኢንቨስትመንት የገቡ ባለሀብቶችን በመጠቀም ችግሮቹ እንዲባባስ ሲሠራ ከርሟል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ የክልሉን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በክልሉ ተዋቅሮ ያለውን የኮማንድ ፖስት አፈፃፀም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር በመሆን መገምገማቸውንም ነው አቶ አሻድሊ የተናገሩት፡፡የመከላከያ ኃይሉ በአካባቢው የመሸጉ ታጣቂ ቡድኖችንና ሽፍቶችን "የመደምሰስ ሥራ እንደቀጠለ" መሆኑን የገለጹት ርእሰ መስተዳደሩ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ከአማራ ክልል የፀጥታ መዋቅር ጋር የጣምራ ሥራዎችን እየሠሩ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ በበኩላቸው "በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ነዋሪነታቸው በቤኒሻንጉል ክልል በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ደኅንነታቸውን ማስጠበቅ አለበት" ከማለታቸውም በላይ "ዋነኞቹ ተጠያቂዎቹም በየደረጃው ያሉ የክልሉ አመራሮች" መሆናቸውን አሳስበዋል፡፡ ሁለቱ ርእሳነ መሥተዳደሮች ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር የኮማንድ ፖስቱን ሥራ ከገመገሙ በኋላ በሰጡት መግለጫ ከየአካባቢው የተውጣጣ የሰላም ምክር ቤት ይቋቋማል ያሉ ሲሆን በርካታ ሚሊሻዎች ተመልምለው ስልጠና እንደሚወስዱም አስታውቀዋል። "ሕዝብ ለሕዘብ አልተጠላም ነገር ግን ሽፍቶቹ ልምድ ያላቸውና ከፊሎቹም ከሠራዊት የወጡ በመሆናቸዉ ነዉ ተከታታይ ጥቃት እየደረሰ ያለው" ብለዋል። "ማስታጠቅ ሲባል ጥቃት በሚደርስባቸዉ አካባቢዎች ከሕዝቡ የተወጣጡ እንደ ሚሊሻ ዓይነት አደረጃጀት እንዲኖር ይደረጋል ማለት ነው" ያሉት አመራሮቹ ጥቃት አድራሾችን ትጥቅ ለማስፈታት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ቀደም ብለው ለቢቢሲ እንደገለጹት በክልሉ በመተከል ዞን ስር ባሉ ሰባት ወረዳዎች የሚሊሻ ስልጠናው  መሰጠቱን ተናግረዋል። አቶ መለሰ እንደገለፁት ከሆነ በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን አካባቢ አሁን በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን በመደበኛ የሕግ ማስከበር የሚቻል ስላልሆነ ከመስከረም 11/2013 ዓ. ም ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ የኮማንድ ፖስት ታውጇል። የኮማንድ ፖስቱ በመከላከያ ሰራዊት የሚመራ ሲሆን፣ የፌደራል እና የክልሉ ፖሊስ በጋራ ሰላም የማስከበሩን ስራ እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል። በዞኑ ከዚህ ቀደም የነበሩ የሚሊሻ አባላት እንዲሁም አዲስ ምልመላ ተካሂዶ ስልጠናው ላለፉት ሶስት ቀናት መሰጠቱን ኃላፊው ጨምረው የተናገሩ ሲሆን በዞኑ ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የተመለመሉት እነዚህ የሚሊሻ አባላት 'ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች' መመልመላቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ከስልጠናው በኋላ በቂ ትጥቅ አስታጥቆ ሚሊሻዎቹ የፀጥታ መዋቅሩን እንዲደግፉ እንደሚደረግም አቶ መለሰ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም የሚሊሻ አባል የነበሩና እድሜያቸው ያልገፉ አባላት በአሁኑ ስልጠና ላይ መካተታቸውን የገለፁት አቶ መለሰ እንደየቀበሌው ስፋት ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ አዳዲስ አባላት መመልመላቸውንም ተናግረዋል። ክልሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት በአካባቢው የሚፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ለመፍታት ምን መደረግ አለበት የሚለውን በተደጋጋሚ ውይይት ማካሄዱንም ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :