የዜጎች አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ 1 ሺህ ዶላር በላይ ደርሷል - ጠ/ሚ ዐብይ
ኢዜጋ ሪፖርተር
October 19, 2020 (Ezega.com) -- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ በዛሬው እለት ተካሂዷል። በስብሰባው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። አነጋጋሪ ሆነው ከዋሉት የጠቅላይ ሚንስትሩ ምላሾች መካከል የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታ በተመለከተ የቀረበው ይገኝበታል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በተጠናቀቀው የበጀት በኢትዮጵያ የ6 ነጥብ 1 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት መመዝገቡን አስታውቀዋል፡፡ የታሰበውን ያህል ባይሆንም ከወቅታዊው የኮቪድ 19 ወረርሺኝ አንጻር በበጀት አመቱ ተስፋ ሰጭ የምጣኔ ሀብት እድገት መመዝገቡን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች ለእድገቱ አይነተኛ ሚና ነበራቸው ብለዋል፡፡ ያም ሆኖ የገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሺዴ ከሳምንት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ወቅት ሀገሪቱ ያስመዘገበችው እድገት 7 በመቶ ነው ብለው መናገራቸው ሲታሰብ የጠቅላይ ሚንስትሩ ማብራሪያ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።
ባለፈው በጀት አመት በኢንዱስትሪው ዘርፍ 9 በመቶ፣ በአገልግሎት 5 ነጥብ 3 እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ 91 በመቶ እድገት ተመዝግቧል ይህም ከፍተኛው ሆኗል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በ2012 የበጀት ዓመት 3 ነጥብ 375 ትሪሊየን ብር ጠቅላላ ሃገራዊ ምርት መመዝገብ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡ በተያያዘም የኢትዮጵያውያን አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ 1 ሺህ ዶላር በላይ ደርሷል ያሉት ዐብይ አህመድ ዓመቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ለመመደብ የነበረው ጥረት የተመለሰበት እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡ ከዚህ ባለፈ ባለፈው በጀት አመት ባንኮች ተደራሽነታቸውን በማስፋት ከ1 ትሪሊየን ብር በላይ መሰብሰባቸውን፣ ከዚህ ውስጥም 271 ቢሊየን ብር ብድር መስጠታቸውንና ከእዚህ ውስጥም አብዛኛው ብድር ለግሉ ሴክተር የተሰጠ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ከአዲሱ የብር ኖት ቅያሪ ጋር ተያይዞ በርካታ አዳዲስ አካውንቶች መከፈታቸውን በማውሳትም ከዚህ ጋር ተያይዞ 37 ቢሊየን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ወደ ባንኮች መግባቱን ነው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የተናገሩት፡፡ ላለፉት ወራት ከፍ ብሎ የነበረው የዋጋ ግሽበት አሁን ላይ በተወሰዱ እርምጃዎችና ማሻሻያዎች ቅናሽ እያሳየ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም የዘንድሮው በጀት አመት በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ወሳኝ ስራዎች የሚሰሩበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የግድቡ ስራ እንዲደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለግድቡ ትልቅ ክትትልና ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም በመተባበር የግድቡን ስራ እንዲያሳካ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተያያዘ መልኩ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እንዳሉት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የፕሮጀክት ግንባታዎችን መንግስት ተገቢውን ጥናት በማድረግ በወሰዳቸው እርምጃዎች በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ በመላ ሀገሪቱ ተጀምረው ያላለቁ ስታዲየሞች፣ፓርኮችና መንገዶች በርካታ መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጅክቶቹ የስኳር ፋብሪካዎችን ጨምሮከ600 ቢሊየን ብር በላይ እዳ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡ ፕሮጀክቶቹ ካሉባቸው ውስብስብ ችግሮች አንፃር በአጭር ጊዜ መጨረስ ፈታኝ ቢሆንም የቆሙትን ወደ ስራ በማስገባት ያልጠተናቀቁትን ለመጨረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የበረሃ አንበጣ ጥቃት እንዳይስፋፋና የረሀብ አደጋ እንዳይከሰት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል። ዘንድሮ ካጋጠመው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጨማሪ አንበጣና ጎርፍ ተፈጥሯዊ ተግዳሮት መከሰቱንም አውስተዋል። አንበጣ ከአንድ እስከ አምስት ደረጃዎች እንዳሉት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ደረጃ ሶስት የነበረውን የአንበጣ መንጋ በአፋር ክልል ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርስ መከላከል መቻሉን አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጅ ደረጃ አምስት የሆነ የበረሃ አንበጣ ከቀይ ባህር አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል። በዚህም በከፊል አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ አፋር እና ሶማሌ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ የበረሀ አንበጣ ጉዳት ማድረሱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ በግብርና ሚኒስቴር የተመራ ቡድን በመጀመሪያው ዙር ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል ሥራ ያከናወነ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር የተከሰተው የበረህ አንበጣ ጉዳት ማስከተሉን አንስተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች አራት ሚሊየን ሄክታር መሬት የታረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 420 ሺህ ሄክታር የሚሆነው መሬት በአንበጣ መንጋው ጥቃት ደርሶበታል ነው ያሉት። ለቅኝት የሚሆኑ ሄሊኮፕተሮች እና ድሮኖች እንዲገቡ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው ቅኝት የሚያካሂዱ ሄሊኮፕተሮች ሃገር ውስጥ ከገቡ በኋላ የሚገጣጠሙ መሆኑ ጊዜ ፈጅቷል ሲሉ ተናግረዋል። መንግስትም ጉዳቱን ለመቀነስ የአውሮፕላን ርጭት እያደረገ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኬሚካል ርጭት ባለፈ አንበጣውን ለማስወገድ በእጅ የማጥፋት ሥራን ስለሚጠይቅ ማኅበረሰቡ ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል። አሁን ላይ በአንበጣ መንጋው የደረሰው ጉዳት ምርታማነትን ከአ
ምስት በመቶ በላይ እንዳይጎዳ መቆጣጠር ይቻላል የሚሉት ዶ/ር አብይ በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትናንሽ አውሮፕላኖችን የመጠቀም አቅሙን እንዲያጠናክር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ መጥቷል በሚል ለተነሳው ሃሳብም ጠቅላይ ሚንስትሩ የትግራይ ሕዝብ በከፍተኛ ችግር እና ድህነት ውስጥ ያለ ሕዝብ ነው በሠላም እና ልማታዊ ሆኖ የመኖር መብት አለው ከማለታቸውም በላይ በክልሉ ጥቂት "የማያስፈልጉ ግለሰቦች" አሉ ተብሎ ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንግስት የሚታገልላቸውን ዜጎች ታሳቢ ያደረግ ስራ ሲሰራ ቆየቷል ብለዋል። የህዝቡ ጉዳይ በትኩረት የሚሰራበት ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከዚያ መለስ ግን ከክልሉ ጋር የተከሰተው አለመግባባት "በሕግ እና ሕግ ብቻ የሚመለስ ይሆናል" የፌዴሬሽን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጡት ውሳኔ ላይ ብቻ በመመሠረት ጉዳዩ በሕግ የሚመለስ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስለሚፈጸሙ ግድያዎች የተጠየቁት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚከሰቱት ጥቃቶች ውስብስብ መሆናቸውን በሰጡት ምላሽ ወቅት አብራርተዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በክልሉ ያለው አለመረጋጋት ከሕዳሴ ግድብ ጋር እንደሚገናኝ ሲያስረዱም "ከሕዳሴ ጋር ይገናኛል የሕዳሴን መንገድ ከመቁረጥ ጋር ይያያዛል" ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ። በዚህም ምክንያት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥቃት የተፈጸመበት ቦታ ለመድረስ እስከ 7 ሰዓት ድረስ በረዣዥም ሳር ውስጥ በእግራቸው እንደሚጓዙ አስረድተዋል። "ጥቃቱ የሚፈጸመው በቀስት ነው። ሳቫና ግራስ ላንድ ውስጥ። ብዙ መስዋእትነት ተከፍሏል" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መማረካቸውን እና ብዙዎቹ ጥቃት አድራሾች ደግሞ መሸሻቸውን ተናግረዋል። "ችግሩ አሁንም ከምንጩ ካልደረቀ ዳግም ችግር ይከሰታል" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥታቸው ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ከዚህ ሌላ የፍትህ ስርዓቱ ነጻ እና ገለልተኛ መሆን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሰኔ 16፣ ሰኔ 15 እና ሰኔ 23 የተያዙ ጉዳዮች የደረሱበትን ደረጃ አብራርተዋል። በጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋፍ በተጠራው ሰልፍ ላይ ለተደረው "የግድያ ሙከራ" ወንጀል ክስ በተመሰረተባቸው ግለሰቦች ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን በሙሉ መስማታቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል። ተከሳሾችም መከላከያዎቻቸውን ማቅረባቸውን ተናግረው በቅርቡ ብይን ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ተከሳሾች ዙሪያ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ሙሉ ለሙሉ መሰማታቸውን ተከሳሾችም መከላከያዎቻቸውን እያሰሙ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል። በአማራ ክልል ለተከሰተው ወንጀልንም በተመለከተ ሲናገሩ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እያሰማ ይገኛል ብለዋል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን