ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)
October 20, 2020
“የአቶ ልደቱ እስርና መንግስት የፍርድ ቤት ትዕዛዝን በተደጋጋሚ አለማክበርና መጣስ የፍትህ ሥርዓቱ አደጋ ላይ መውደቁን፣ የወይዘሮ መዓዛ ጥረት መክሸፉን፣ የሹሞቹ ባህሪ ዛሬም አለመቀየሩን፣ ፍትህ ዛሬም በጉልበተኞች ጫማ ስር መውደቋን የሚያሳይ መጥፎ ምልክት ነው። ከዚህ በኋላ ፀቡ ከአቶ ልደቱ ሳይሆን ከፍትህና ለፍትህ ከሚወግኑ ሁሉ ጋር ነው።”
(አቶ ያሬድ ኃ/ማርያም - የሠብዓዊ መብቶች ተሟጋች)
የደውሉ “ድምፅ” ለሁላችንም ነው!
በቀደሙት ሁለት ክፍሎች የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ብሔራዊ ምክር ቤት አባልና አመራር አባል ስለሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ፍትህ ማጣትና ሰቆቃአንስተን መሰል የህገ-ወጥ አያያዝ ሰለባዎችን ጉዳይ ካወሳሳን በኋላ በተፈጠሩ ተያያዥ ጉዳዮች መግቢያዬን ላደርግና በዚህ ክፍልም ርዕሱን ልቋጨው ወደድኩ፡፡ ከነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በቀር ስለሁላችንም ነፃነትና የሰብዓዊ መብቶቻችን መከበር እንዲሁም ስለፍትህ ቆመናል ከሚሉት የፖለቲካ ማህበራት በኩልም ቢሆን አንድም የአጋርነት መግለጫ አለመሰጠቱና እንዲያውም “ይበለው!” ማለታቸውን ታዝበናል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔን (ሰመጉ) ዝምታን መውቀሳችንም አይዘነጋም፡፡
በሸኘነው ሳምንት “የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ-ኢዜማ” አመራር አባላት የሆኑት አቶ አንዷለም አራጌና አቶ የሺዋስ አሰፋ ይህንን የፍትህ ኪሳራ አስመልክተው በይፋ ተቃውሟቸውን በመግለፅ ስልፍትህና ስለአቶ ልደቱ ሰቆቃ አጋርነታቸውን ማሳየታቸው ባይዘነጋም እንደፖለቲካ ማህበሩ አቋም የሚወሰድ አይደለም፡፡ ዶ/ር በድሉ ዋቅጂራ በበኩላቸው ለውጥ ያስፈለገበት ምክንያት የፍትህ ተቋማት ላይ ጉልበተኞች የሆኑትን ጉልበት ለመቀነስ እንደሆነ ፅፈዋል፡፡ የየኔታ መስፍን ወ/ማርያም መዘከሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔም “አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ” በማውጣትና ከተከታተላቸው ጉዳዮች ውስጥም የአቶ ልደቱ አያሌውን ሰቆቃ በአይነተኛ ማሳያነት በመጥቀስ የፍርድ ቤት ትዕዛዛት እንዲከበሩና የህግ አስፈፃሚ አካላትም የህግ የበላይነት መከበር ላይ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል፡፡ ይህንን ሁሉ የምጠቅሰው በፍፁም ልንለያይበት በማይገባው የፍትህ ሥርዓታችን ላይ የተደረገ መልካም ተጋድሎና የነጌያችን ዋስትና ጉዳይም ስለሆነ ነው፡፡
በቀደሙት ፅሁፎች የጠቀስናቸው ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ታሳሪዎች ህገ ወጥ እስር እንደተጠበቀ ሆኖ ለዓመታት ሲታሰርና ሲፈታ የኖረው የ“ፍትህ” መፅሄቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ተመስጌን ደሳለኝና ዋና አዘጋጁ አቶ ምስጋን ዝናቤ እስርና “ስንፈልጋችሁ ትመጣላችሁ!” ፍቺ ጉዳዩን ማድፈንፈኑ እንዳለ ሆኖ የአቶ ልደቱ አያሌው ጉዳይ ላይ የህትመት ሚዲያውም ሆነ ህግና ሥርዓትን ይጠይቅ የነበረው ሁሉ ጨምቶ ከነበረበት እየነቃ መምጣቱ መልካም ጅምር ይመስለኛል፡፡ በዚሁ ሰሞን ስለፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበርና ውሳኔዎች አለመፈፀም ለመነጋገር በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተደረገና አምስቱ “የፍትህ አካላት” የተሳተፉበት ስብሰባ ነበር፡፡ ተቋሙን ማቅናት ባልቻሉት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በመሩት በዚሁ ስብሰባ ላይ ስማቸው ያልተጠቀሱ ክልሎች ላይ ግድፈቶች ቢኖሩም “ችግሮቹ በሂደት እየተቀረፉ መጥተዋል!” የሚል ድምደማ ላይ ቢደርሱም ሴትዮዋ ይህንን ከማለታቸው ሁለት ቀን በፊት ግን የባልደራሱ አቶ እስክንድር ነጋ ህገ-መንግሥቱ በሚፈቅድለት መሠረት ቤተሰቦቹን ለማግኘት ጠይቆ መከልከሉን ሰምተናል፡፡
የአቶ ልደቱ አያሌው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ በፊርማዋ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ህግጋትና የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶችም ሆነ ከራሷ ህገ-መነግሥት አኳያ ስለፍትህ ሥርዓታችንና ሥርዓቱ እንዳይቀየር ስለመፈለጋችን አይነተኛ (Typical) የሚባል ማሳያ ነው፡፡ ሰውዬውን በሁለት መዝገቦችና ሁለት ችሎቶች በማንከራተትና ይህንንም ደጋግሞ በመንገር ሊተላለፍ የተፈለገው ፖለቲካዊ መልዕክት ግልፅ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ከተማ ዓቃቤ ህግ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት በሰኘው ክሱ ምስክሮች ባለመቅረባቸው ምስክርነቱም ሳይሰማ ቀርቶ ነበር፡፡ በዚሁ ጊዜ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ምስክሮቹ ተገድደው እንዲቀርቡ በሰጠው ቀጠሮ ላይና በኋላም ሲሰሙ በተፈቀደላቸው ዋስትና ያለመፈታታቸውን ምክንያት ጠይቋል፡፡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለማክበር እምቢታው የፀናውን የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ላይም ፍርድ ቤቱ እርምጃ እንደሚወስድ ገልፆ ሳለና ይሄንኑ ትዕዛዝ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሰጥቶም ቢሆን ተከሳሹ ባለመፈታታቸው ፍርድ ቤቱ ምንም ማድረግ ያለመቻል አቅሙንም ተረድቷል - ለዜጎች አርድቶናልም፡፡
ይህ ፅሁፍ በመጠናቀር ላይ ሳለ ህጋዊ ቅቡልነታቸው ያከተመው ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በርዕሰ ብሔራችን የምክር ቤቶች ንግግር ላይ በሰጡት ማብራሪያ ዜጎች ሁሉ የፍርድ ቤት ብያኔዎችን ምንም ሳናወላዳ መቀበል እንዳለብን፣ መንግሥት ያለከበረውን ፍርድ ቤትም ህዝቡ እንደሚያቀለው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ሰውዬው ይህንን ይበሉ እንጂ አቶ ልደቱ የታሰሩበትና አሁን በሁከትና መንግሥት ላይ አመፅ በማነሳሳት ወንጀል የተከሰሱበት የሽግግር መንግሥት አማራጭ ሰነድ የቀረበው ዓብይ ራሳቸው ባሉበትና የሌሎች የፖለቲካ ማህበራት ተወካዮችም በተገኙበት የኢሲኤ አዳራሽ ሲሆን የአሁኖቹ የፖለቲካ እስረኞችም በአፈሳ መልክ ለእስር ከመዳረጋቸው ወራት በፊት መሆኑ ነው፡፡
ነገረ ልደቱ አያሌው ምህረቱ….
የአቶ ልደቱ አያሌው ሁለተኛ ክስ በሆነው መንግስት ላይ አመፅ ማነሳሳትና ህገ-መንግሥቱን በሃይል መናድ ወንጀል በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት የሥርዓቱ ልሳንነቱን ደጋግሞ ያስመሰከረው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ክሱ እንደደረሳቸውና መጥሪያም እንደተቀበሉ አድርጎ ዘግቦ የነበረ ሲሆን በሌላ ወቅት ግን ይኸው ራዲዮ ጣቢያ የዋስትናቸውን ጉዳይ ባላየና ባልሰማ አልፎት ነበር፡፡ የችሎት ዘገባው ጉዳይ ራሱን የቻለ አንድ ርዕስ ነውና ይቆየን፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ ባለን መረጃ የአቶ ልደቱ አያሌውን የዋስትና መብት በተመለከተ ይህ ክስ የቀረበለት ፍርድ ቤትም ቢሆን የታች ፍርድ ቤት ውሳኔ እስካልተከበረ ድረስ ይህንን ክስ መስማት እንደማይኖርበት ግልፅ ነበር፡፡
በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን ዐቃቤ ህግ በአቶ ልደቱ ላይ የመሰረተው የህገ-መንግሥት ንደትና ለውጥን ያለመቀበል ክስ የንግግርና ሃሳብ ነፃነትን ሊቃረን በንባብ ቀርቧል፡፡ ለክሱ መቃወሚያ ለማቅረብም ለጥቅምት 13/2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ለቀዳሚው የህገ-ወጠይ ጦር መሳሪያ መያዝ ወንጀል ብይን ለመስጠትም በሌላው ችሎት ለጥቅምት 9/2013 ቀጠሮ አላቸው፡፡ “ይህንን ሥርዓት ገደል የሚከተው አድር ባይ ምሁር ነው!” የሚሉትን አቶ ልደቱ አያሌውን እንዲያስፈታ የታዘዘው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንም ዝምታን መርጧል፡፡ ምናልባት የአሳሪውን አንድ የስልክ ጥሪ እየጠበቀ ከሆነ ከሰሞኑ መፍትሄ ይኖር ይሆናል፡፡
ገና ከማተሚያ ቤት ባልወጣና ከረቂቁ በቀር ባልተነበበ መፅሐፍ “አመፅ ቀስቃሽ” ስለመሆኑ የሚሰጋ፣ የቅድመ ምርጫ ግመታው “ሻሞ” ትንተናን በሃሳብና በሌላ ትንተና ከመሞገት ይልቅ የሚፈራ፣ ከቀደመው ሥርዓት ረገድም “ከድጡ ወደማጡ!” የሆነ አምባገነናዊ ፖለቲካዊ ሥርዓት፣ ፍርድ ቤት ፊት በሚቀርብባቸው ግዜያት ሁሉ የሚቀያይርና ጉዳዩን የመረመረበትን መዝገብ እንዲያቀርብ በችሎት ሲጠየቅ “ወደ ፌዴራል ልኬዋለሁ!” ብሎ ከሚመልስ ዓቃቤ-መንግሥትና ፖሊስም ሆነ ይህንን ሰበብ “በቂ ምክንያት” አድርጎ ከሚቀበል ፍርድ ቤት ዳኛ፣ ከሁሉም በላይ እዚህ ገፃችን ላይ አብዝተን የምንተቸውና አምባገነኖችን “ደግ አደረግክ!” ከሚል ሥርዓተ ማህበርጋ “አልደመርም!” ማለት የፍትሀውያን ሁሉ መርህ ሊሆን የተገባ ነው፡፡
ጥሎብኝ ከኔ ተቃራኒ የሆነ ሃሳብ እያራመዱ እንኳን ከኮሮና ተህዋሲ ስርጭት አንፃር የጤናቸውን ሁኔታ ባላገናዘበ መልኩ የሚጉላሉትንና “አስተባብረሃቸዋል!” የተባሉት ተባባሪዎች ሳይያዙ በአስተባባሪነት እንደተያዙት እንደአቶ ልደቱ ያሉ “እምቢ!” ማለትንም የሚደፍሩ የመርህ ሰዎችን እወዳለሁ፡፡ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያው ክስ ቢሾፍቱን ተሸግሮ አዳማ ሲዘልቅም ሆነ በቀደመው ወቅት አንዳንድ በጥብቅናው ስራ ላይ የተሰማሩ “የህግ ባለሙያዎች” ለአቶልደቱጥብቅና ለመቆም የመንግሥትን ተለዋዋጭ ፊት እያስተዋሉ ሲያንገራግሩ ጠበቃዎቹ የአቶ አብዱል ጀባር ሁሴን ቡድኖች አቶ መሀመድ ጅማ እንዲሁም ኦቦ ገመቹ ጉተማን በፍትህ ሂደቱ ተስፋ ቆርጠው እስኪያሰናብቷቸው ድረስ በነፃ እንደተከራከሩላቸው ተሰምቷልና ለእነዚህ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡ አርስቶትል እንደሚለውም “ከፍትህ በስተፊት የሚቀድም ምንም ነገር የለምና፡፡
በኢህአዴግ ጫና ምክንያት በይፋ በፅሁፍ እሳተፍባት ከነበረችው “አውራምባ ታይምስ” ጋዜጣ ላይ “ብዕሬን ሰቅያለሁ!” ሲል በመፃፍ ሃሳብን በመግለፅ ነፃነት ላይ ያለውን ሥርዓታዊ አፈና ያስመለከተን ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ (ፋሲል) “እውነትን ስቀሏት” በሚለው ቀዳሚ የግጥም መድብሉ ስር ያካተተውና “ስንቅ የሚያቀብሉኝ እስረኞቹ ናቸው” የሚል ርዕስ የሰጠው ግጥም አለ፡፡ ለብዙዎቹ የህሊናና ፖለቲካ እስረኞች የተመጠነ በሚመስለው በዚህ ግጥሙ ከመኖሪያቸው አዲስ አበባ ተወስደው በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ለታሰሩት ለአቶ ልደቱ አያሌውና ሰቆቃው ብዙ ላልተነገረለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ትምህርትና ባህሪ ጥናት ኮሌጅ ዲን ለሆነው ዶ/ር ሁሴን ከድር ኸሊል ማመስገኛ በማድረግ ልሰናበታችሁ፡-
“እስረኛ ነኝ እኔ - መብቱ የጎደለ፣
ነፃ እርግብ ለመሆን - ከቶም ያልታደለ፡፡
በአጥር - በጠመንጃ - በዘብ ተጠብቄ
በአንዲት ጠባብ ክፍል - ምኞቴን አምቄ
ታስሬ እኖራለሁ - በመፅሐፍ ቅጠል ዓለምን እያየሁ፡፡
የለም ነፃ ሰው ነኝ! እስረኛ አይደለሁም!
ጭንቅና ሰቀቀን - ከእኔ ጋራ የሉም፡፡
‘እታሰር ይሆን ወይ?’ ብዬ መች ልፈራ
ታስሬያለሁና - ከራሴ እውነት ጋራ፡፡
የሚዳቋ ስጋት፤ ጭንቅ የሞላባቸው
የታሰሩትማ - በደጅ ያሉ ናቸው፡፡
እኔ ነፃ ሰው ነኝ - ያሻኝን ሰርቼ - የልቤን አውርቼ
ይኸው እዚህ አለሁ - ነፃነት አግኝቼ፡፡
የታሰሩትማ በውጭ ያሉ ናቸው!
የልብን ለማውራት - የልብን ለመስራት ወኔ የከዳቸው፤
የሚደናበሩ በገዛ ጥላቸው፣
እኔ ነፃ ሰው ነኝ - የታሰሩትማ ያልታሰሩት ናቸው፡፡
-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን