በደቡብ ክልል 12 አርሶ አደሮች በታጣቂዎች ተገደሉ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Gura-Ferda-EthiopiaOctober 21, 2020 (Ezega.com) -- በደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኘው ቤንች ሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ "ማንነታቸው ያልታወቀ" የተባሉ ታጣቂዎች 1 ህጻንን ጨምሮ 12 ንጹሃን ዜጎችን በጥይት መግደላቸው ተሰማ። የወረዳው ባለስልጣናት ለጀርመን ድምጽ እንዳስታወቁት ታጣቂዎቹ ግድያውን የፈጸሙት ባለፈው ሰኞ ምሽት በወረዳው ውስጥ በሚገኘውና ለዩ ስሙ ሹቢ በተባለው የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው። እንድ ባለስልጣናቱ መረጃ ከሆነ ታጣቂዎቹ በቀበሌው በሚገኙ መንደሮች ውስጥ ዘልቀው በመግባት በድንገት በከፈቱት የተኩስ እሩምታ አንድ ህጻንን ጨምሮ 12 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 5 ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።  የጉራ ፈርዳ ወረዳ ፖሊስ ዋና አዛዥ ኢንስፔክተር በቀለ በየነ ለጣቢያው በሰጡት ቃልም ይሄንኑ አረጋግጠዋል። "ጥቃቱ የደረሰባቸው በሙሉ አርሶ አደሮች ናቸው ባልታሰበ ሰዓት ምሽት ላይ በየቤታቸው ተቀምጠው ባሉበት ወቅት ነው የተገደሉት። አሁን የወረዳ፣ የክልል እና የፌዴራል የፀጥታ ሃላፊዎችና የሰራዊቱ አባላት በስፍራው ደርሰን አካባቢውን እያረጋጋን እንገኛለን። በትናንትናው እለትም የሟቾቹ አስክሬን እንዲቀበርና የቆሰሉትም ወደ ህክምና እንዲወሰዱ አድርገናል " ሲሉም ኢንስፔክተር በቀለ ተናግረዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው አካባቢው እስከ አሁን ሰላማዊ፣ የተረጋጋና የልማት ቀጠና ነበር በማለት ተናግረው በአሁኑ ወቅት ጥቃት አድራሾቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል በዞኑ ውስጥ በሚገኘው የኮማንድ ፖስት አማካኝነት የተቀናጀ የጸጥታ ሀይል ክትትል በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል። በተጨማሪም በሁኔታው ተደናግጠው ወደ አጎራባች ቀበሌያት የሸሹ ነዋሪዎችን የማረጋጋት፣ ወደ ቦታቸው የመመልስ እና የተለያዩ አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፎችን የማቅረብ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው አቶ ፍቅሬ አማን አስታውቀዋል። ጥቃቱ ተፈጽሟል በተባለበት በዚሁ የቤንች ሸኮ ዞን በስራ ጉብኝት ላይ የነበሩት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ "በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶኛል፣ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ይዘን ለህግ ለማቅረብ እንሰራለን" ሲሉ የክልሉ መንግስት ንብረት ለሆነው የደቡብ ቴሌቪዥን መናገራቸውም ተሰምቷል። በቤንች ሸኮ ዞን መስተዳድር ስር በሚገኘው የጉራ ፈርዳ ወረዳ ውስጥ ተሰባጥረው ከሚገኙት የቤንች፣ የሸኮ እና የሜኒት ጎሳዎች በተጨማሪ ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመንደር ማሰባሰብ የመጡ ማህበረሰቦችም ይኖሩበታል ተብሏል። የቀድሞው የቤንች ማጂ ዞን መስተዳድር ምዕራብ ኦሞ እና ቤንች ሸኮ ዞን በሚል ለሁለት ሲከፈል የጉራ ፈርዳ ወረዳ በየትኛው የዞን መስተዳድር ይጠቃለል የሚለው ጥያቄ የአካባቢው ፖለቲከኞችን ሲያነታርክ መክረሙ ይታወሳል። የአሁኑ ጥቃት ከወረዳው የአከላለል ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑ እስከአሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም የዞን ባለስልጣናት ግን ጥቃት አድራሾቹ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሰሩ ቡድኖች ናቸው እያሉ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ግድያ በዘላቂነት ለመፍታት ውይይቶች እየተካሄዱ ነው ተብሏል፡፡ በውይይቶቹ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰንን እና የፌደራል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ከግልገል በለስ ከተማ እና ከማንዱራ ወረዳ ሁሉም ቀበሌዎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች እየተሳተፉ እንደሚግኙ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ በመተከል ዞን እየተከሰተ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የህብረተሰቡን የአብሮነት ዕሴቶች የበለጠ የማጠናከር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን በውይይቱ ላይ ተናግረዋል፡፡ በቀጠናው በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን የሰዎች ሞት እና ንብረት መውደም በዘላቂነት መፍትሄ ለማበጀት በዞኑ ስር ባሉ ሁሉም ወረዳዎች የህዝብ ለህዝብ ውይይቶችን በማካሄድ የማህበረሰቡን አብሮነት መልሶ ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ዘገባዎቹ አመልክተዋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :