ግብጽ የህዳሴውን ግድብ ታፈነዳዋለች - ዶናልድ ትራምፕ
ኢዜጋ ሪፖርተር
October 23, 2020 (Ezega.com) -- የአሜሪካው አወዛጋቢ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ስምምነትን ጥላ መውጣት አልነበረባትም፣ ያንን በማድረጓ ከባድ ስህተት ሰርታለች ግብጽ በዚህ ሁኔታ መኖር ስለማትችል "ግድቡን ታፈነዳዋላች" ሲሉ በይፋ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ሃምዶክ እና ከእስራኤሉ አቻቸው ቤንያሚን ኔይተናሁ ጋር በቀጥታ የስልክ ውይይት እያደረጉ በነበረበት ወቅት ነው። የቀጥታ የስልክ ውይይቱ ሲካሄድ ጋዜጠኞች ተገኝተው የነበረ ሲሆን የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው ግድቡን በሚመለከት በቅርቡ በሶስቱ አገራት መካከል ስምምነት ይደረሳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሁለቱ መሪዎች ጋር የተወያዩት ሱዳንና እስራኤል በቅርቡ ግንኑነታቸውን ለማሻሻል መስማማታቸውን በማስመልከት ነበር። ምንም እንኳን የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር "በቅርቡ ስምምነት ላይ እንደርሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ቢሉም በርካታ ጋዜጠኞች በተሰበሰቡበት ሁለቱን መሪዎች የሚያናግሩት ትራምፕ ግን ለግብጽም ተመሳሳይ ነገር መናገራቸውን በመጥቀስ ሁኔታው አደገኛ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ግብጽም "ግድቡን ታፈነዳዋለች" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሃውስ በነበረው የስልክ ውይይት ወቅት ሲናገሩ እንደተደመጡት ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ወደ ስምምነቱ መመለስ አለባት በኢትዮጵያ ድርጊት ግብጽ ብስጭት ቢገባት ልትኮነን አይገባም ስለሆነም "ያን ግድብ ልታፈነዳው ትችላለች" በማለት ደጋግመው ተናግረዋል። ዶናልድ ትራምፕ ጨምረውም "እኔ የስምምነቱን ጉዳይ ጨርሼው ነበር ነገር ግን ኢትዮጵያ ጥላ ወጣች ተግባራዊም አላረገችውም" ብለዋል። ፕሬዝደንት ትራምፕ የሱዳኑን ጠቅላይ ሚንስትር አብዱል ሃምዶክ በስልክ በመስመሩ ላይ እያሉ "ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ እንዴት እየሆነ ነው? በማለት የጠየቁ ሲሆን ወዲያውም ራሳቸው ግድቡ ውሃ ወደ ታችኛው የተፋሰስ አገራት እንዳይፈስ መከልከሉን ሲናገሩ ይደመጣል። አክለውም "ከግብጽ እና ኢትዮጵያ ጋር ሶስተኛ ወገን ሆናችሁ ጉዳዩን በቅርብት እየተመለከታችሁ ነው እና ስምምነቱ ከምን ደረሰ?" ሲሉ ጠይቀዋል ፕሬዝዳንቱ። ትራምፕ ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ሳይጠብቁም "ስምምነት እንዲደርሱ አድርጌ ነበር። ኢትዮጵያ ግን ስምምነቱን ጥላ ወጣች ያን ግን ማድረግ አልነበረባቸውም ትልቅ ስህተት ነው የሰሩት። "በዚህም ብዙ የእርዳታ ገንዘብ አቋርጠንባቸዋል ለስምምነቱ ተገዢ እስካልሆኑ ድረስ ያን ገንዘብ መቼም አያገኙትም" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለችው የህዳሴ ግድብ እጅግ ግዙፍ እንደሆነ የተናገሩት ትራምፕ "ውሃው ወደ ናይል ወንዝ እንዳይፈስ የሚያቆም ግድብ ገነብታለች ግብጽ በዚህ ብትበሳጭ መኮነን የለባትም። እንዴት እየሆነ ነው? ምን ያውቃሉ?" ሲሉ ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር በድጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል። በዚህ መካከል በስልክ መስመር ላይ የነበሩት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ጣልቃ ገብተው መናገር ሲጀምሩ ታዲያ ትራምፕ ጥያቄውን ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር ወይም ለሱዳን ሰዎች ያቀረቡት መሆኑን ተናግረው የኔታኒያሁን ንግግር አቋርጠዋል። ስልኩ ወደ ሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር እየሄደ በነበረብት ቅጽበትም ትራምፕ የሱዳንን ጠቅላይ ሚንስትር "ለዚህ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚፈልግ አይመስለኝም" በማለት ፈገግ ሲሉ ተስተውለዋል። የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር በበኩላቸው "ሁሉንም ሊጠቅም የሚችል ሁሉን አካታች ስምምነት በቅርቡ እንደርሳለን ብለን እናስባለን" በማለት የመለሱ ቢሆንም ትራምፕ ንግግራቸውን አቋርጠው "እንደዛ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም ስምምቱን አፍርሰዋል ይህን ደግሞ ከፍተኛ አጣብቂኝ ፈጥሯል ግብጽ በዚህ ሁኔታ መኖር አትችልም ግብጽ ያንን ግድብ ልታፈነዳው ትችላለች ደግሜ እናገራለሁ ግብጽ ግድቡን ታፈነዳዋለች" ሲሉ ተናግረዋል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን