ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም - ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት
ኢዜጋ ሪፖርተር
October 25, 2020 (Ezega.com) -- "ግብጽ ግድቡን ታጋየዋለች!" የሚለው አስደንጋጩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግር ከተሰማበት ቅጽበት አንስቶ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ቁጣቸውንና ተቃውሟቸውን በተለያየ አግባብ ሲገልጹ ውለዋል። የፌደራልና የክልል ባለስልጣናትም በፕሬዝዳንቱ "ጠብ አጫሪ" ንግግር ዙሪያ በርከት ያሉ መግለጫዎችን አውጥተዋል። በተጨማሪም መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በኩል የአሜሪካውን አምባሳደር አስጠርቶ የትራምፕ አባባል ላይ ማብራሪያ ጠይቋል። አስቀድመን ከጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት የተሰጠውንና በቀጥታ የፕሬዝዳንቱን ንግግር ከማውገዝ ይልቅ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክና በግድቡ ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም ማንጸባረቅን የመረጠውን መግለጫ ይዘት እንመልከት። መግለጫው "ማንም ገዝቶን አያውቅም ወደፊትም ማንም አይገዛንም ታሪክ የሠሩ እጆች ዛሬም አሉ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸውን ለማክበር እንጂ ጠላቶቻቸውን ለመታዘዝ ተንበርክከው አያውቁም ዛሬም ወደፊትም አናደርገውም" በሚል ይጀምራል። በመቀጠልም ኢትዮጵያ በፍጣሪዋ ታምና በሕዝቧ አንድነትና ጽናት የቆመች ሀገር ናት። ጥቂት ሰጥተው ብዙ ሊያዟት በሚሞክሩ ተማምና አታውቅም። ሕይወታቸውን ሰጥተው ሊታዘዟት በተዘጋጁ ልጆቿ እንጂ። ኢትዮጵያን የፈጠራት አምላኳ ነው። ያለው መግለጫው ልጆቿ በከፈሉት መሥዋዕትነት ዓለምን ጉድ ያሰኙ ታሪኮችን ሠርታለች ብሏል።
እነዚህን አስደናቂ ታሪኮችን ስትሠራ አብረዋት ታሪክ የሠሩ ወዳጆች ነበሯት "የከዷት ወዳጆችም ነበሩ" ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። ነገር ግን የዓለም ታሪክ ያረጋገጣቸው ሁለት ሐቆች አሉ እነሱም "ኢትዮጵያን ነክቶ በሰላም የኖረ የለም" የሚለው ቀዳሚው ነው። "ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለአንድ ዓላማ ከቆሙ ድል ማድረጋቸው አይቀርም" የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ሲል መግለጫው አስነብቧል። ከዚህ ሌላ "የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ግድብ ነው። ኢትዮጵያውያን አሰቡት፤ ኢትዮጵያውያን ጀመሩት፤ ኢትዮጵያውያን ገነቡት፤ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ይጨርሱታል። አይቀሬ ነው" ሲልም አቋሙን አስረግጦ አሳውቋል። "የሚያዋጣን ኅብረት አንድነታችን ነው" ያለው መግለጫው "ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ለኢትዮጵያ እንቁም ከባዱ ፈተና ከውጭ የሚመጣው አይደለም። ከባዱ ፈተና ተለያይተን ችግሩን ከተጋፈጥነው ነው። ክንዳችንን እናበርታ። ትከሻችንን እናስፋ። ልባችንንም እናጽና። ከውጭና ከውስጥ የተሠነዘረብንን ጥቃት ድል አድርገን መሻገር ብርቃችን እንዳልሆነ እናስመስክር" ብሏል። በመጨረሻም "በምንምና በማንም ካሰብነው መንገድ እንቀርም ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም" በማለት ሁሉም ዜጋ በየቦታው 24 ሰዓት ለኢትዮጵያ እንዲቆም ጥሪውን አስተላልፏል።
በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይነርን በጽ/ቤታቸው አስጠርተው አነጋግረዋቸዋል፡፡ "በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ጦርነት ማወጅ በስልጣን ላይ ካለ አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሚጠበቅ አይደለም" ያሉት አቶ ገዱ፡፡ ንግግሩ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል የቆየውን ወዳጅነት እና ስትራቴጂያዊ አጋርነትም አይመጥንም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የመንግስታት ግንኙነትን በሚገዛው ዓለም አቀፍ ሕግም ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አክለውም "ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ ለሚቃጡ ጥቃቶች ተምበርክካ አታውቅም ወደፊትም አትምበረከክም" ብለው ሀገሪቱ ከሱዳን እና ግብፅ ጋር በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት ስታደርግ የቆየችውን የሶስትዮሽ ድርድር ለመቀጠል ግን አሁንም ዝግጁ ናት ሲሉ የመንግስታቸውን አቋም አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም ኢትዮጵያ ለድርድር፣ ፍትሀዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት እንደ ከዚህ ቀደሙ ትሰራለች ከዚህ ውጪ "በህዳሴ ግድቡ ላይ በማስፈራሪያና በዛቻ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም" ብሏል፡፡ በህዳሴ ግድብ ላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መዳፈር ለማንም አይጠቅምም ያለው መግለጫው "ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ የኖረች፣ ወደፊትም የምትኖር ታላቅ ሀገር ናት" ሲልም በቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በኩል ገልጿል፡፡
"የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር ለግብጽ የወገነና ኢትዮጵያዊያንን በአግባቡ ካለማወቅ የተሰነዘረ ነው " ያሉት ደግሞ በቅርቡ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ናቸው። "ግድቡ የተጀመረውና እዚህ የደረሰው በህዝብ ድጋፍ ነው፤ ዳር የሚደርሰውም በህዝብ ድጋፍ ነው፤ አሁንም ከተባበርን ይሄን አይደለም ሌላ ግድብ መስራት እንችላለን" ያሉት ዶ/ር አረጋዊ ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ለግድቡ ያለውን ድጋፍና ተሳትፎ በአግባቡ እንዳልተረዱት ንግግራቸው ያሳያል ብለዋል። አክለውም "ኢትዮጵያን የወረረው ጣሊያን አድዋ ላይ ድል የተነሳው በኢትዮጵያዊያን ትብብር እንጂ በውጭ ሀይል ድጋፍ አይደለም" ያሉት ዳይሬክተሩ "አሁንም ከ70 በመቶ በላይ የደረሰውን ግድብ ለማጠናቀቅ የሚያቆመን ምንም አይነት ሀይል የለም" ሲሉ ነው የመንግስትንና የህዝቡን የትብብር መንፈስ ያስረዱት። "በውስጥም በውጭም ያለን ኢትዮጵያዊያን ተባብረን ግድቡን ከዳር ለማድረስ መፍትሄው በእጃችን ነውና አሁን ካለውም በላይ መተባበር አለብን" ሲሉም ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ጥሪ አቅርበዋል።
አወዛጋቢው የትራምፕ ንግግር የአውሮፓ ህብረትንም ያሳሰበው ይመስላል። ህብረቱ በጉዳዩ ዙሪያ አቋሙን ያሳወቀ ሲሆን በእዚህም "ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት ለችግራቸው ዕልባት ለመስጠት እየሄዱበት ያለውን መንገድ የምንደግፍበት እንጂ አላስፈላጊ ውጥረት የምንፈጥርበት ጊዜ አይደለም" ሲል የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተችቷል። ከ250 ሚሊየን ህዝብ በላይ በሚኖርበት በአባይ ተፋሰስ ቅድሚያ የሚሰጠው ሊደገፍ የሚገባውም ድርድር ብቻ ነው ያለው ህብረቱ አሁን ግዜው እንዲህ ዓይነቱ ድርድር ለመደገፍ የምንነሳበት እንጂ አላስፈላጊ ውጥረት በቀጠናው እንዲፈጠር የምናደርግበት ጊዜ አይደለም ከማለቱም በላይ በደቡብ አፍሪካ አደራደሪነት ሶስቱ ሀገራት ልዩነታቸውን በውይይት ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍም በድጋሚ አረጋግጧል።
በተመሳሳይ የአሜሪካው ሴናተር ጄሰን ክሮው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያደረጉትን ንግግር ተቃወመዋል፡፡ የኮሎራዶው ሴናተር በትዊተር ገፃቸው እንዳስታወቁት የፕሬዚዳንት ትራምፕ "ግብፅ የህዳሴ ግድብን ልታጋይ ትችላለች'' ንግግር ከእርሳቸው የማይጠበቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡የፕሬዚዳንቱ ንግግር የግድቡን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከግንዛቤ ያላስገባ ነውም ብለዋል፡፡ ሴናተሩ ኢትዮጵያ የአሜሪካ የረዥም ዘመናት የልብ ወዳጅ መሆኗን ገልፀው አሜሪካ ስለ ህዳሴው ግድብ አደራዳሪ እንጂ የአድልዎ ጣልቃ ገብነት አያስፈልጋትም ነው ያሉት፡፡ ጉዳዩ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲያልቅ መስራት እንጂ እርዳታን እናቋርጣለን በሚል ማስፈራሪያ መሸበብ የለበትም ሲሉም የትራምፕን ንግግር ተቃውመዋል፡፡
እንደሚታወቀው በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ የኢትዮጵያ መንግስት "ከደህንነት ጋር በተያያዘ" ግድቡ በሚገነባበት አካባቢ ማንኛውም አይነት የአየር በረራ እንዳይካሄድ አግዷል። በተጨማሪም በግድቡ ዙሪያ ከማንኛውም አካል ሊሰነዘር የሚችልን የአየር ጥቃት ለማክሸፍና እንዳስፈላጊነቱ የመልሶ ማጥቃት ለመሰንዘር የሚችል የአየር ሃይል ክፍል በተጠንቀቅ ላይ እንዳለ ተሰምቷል። የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ይልማ መርዳሳም ሰራዊቱ ግድቡን ከየትኛውም አካል ሊቃጣ ከሚችል ጥቃት ለመጠበቅ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑን ማስታወቃቸው ይታወሳል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን