በአፋር ክልል 10 ሰዎች 'በአሸባሪዎች' ተገደሉ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Afar-EthiopiaOctober 28, 2020 (Ezega.com) -- ባለፉት ሁለት ቀናት በአፋር ክልል  ገዳማይቱ በመባል በሚታወቀው አካባቢና በክልሉ ዞን ሶስት በሚገኘው ገለአሎ ወረዳ ሰርከሞና ቴሌ ቀበሌ መንደር ውስጥ 10 ንጹሃን ዜጎች በአሸባሪዎች መገደላቸውን የአፋር ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አህመድ ካሎይታ አስታውቀዋል። ሃላፊው ለቢቢሲ እንደተናገሩት በተለይ ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሁኔታ ለመቆጣጠር የተሰማሩ አቶ ሙላት ፀጋዩ እና አቶ አበባው አያልነህ የተባሉ ሁለት የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በትምህርት ቤት ውስጥ በተተኮሰባቸው ጥይት ተገድለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት በገለአሎ ወረዳ ሰርከሞና ቴሌ ቀበሌ መንደር ውስጥ በሚገኙ የአርብቶ አደር ማሕበረሰብ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ስምንት ሰዎች "አሸባሪ በሚባሉ ሃይሎች ተገድለዋል" ሲሉ አቶ አህመድ አረጋግጠዋል። 'የሽብር ጥቃቱ' በሴቶችና ህፃናት ላይ እንዳነጣጠረ የጠቀሱት የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ በክልሉ የተለያዩ ግጭቶች የሚያጋጥሙ ቢሆንም እንዲህ አይነት "የሽብር ጥቃት" ሲያጋጥም ግን ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ። የመጀመሪያው ባለፈው አመት ውስጥ በአፋምቦ ወረዳ ኦግኖ ቀበሌ በተመሳሳይ መልኩ ሌሊት ላይ ሴቶችና ህፃናት ላይ ያነጣጠረ የሽብር ጥቃት ተፈፅሞ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን አቶ አህመድ ያስታውሳሉ።

ጥቃት የደረሰበት አካባቢ የኢትዮ-ጂቡቲ አውራ ጎዳናና አለም አቀፍ መተላለፊያ ድንበር እንደሆነ የገለጹት ሃላፊው ጥቃቱን ያደረሱትን አካላት ማንነት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በህገ ወጥ ንግድ በኮንትሮባንድ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩና ያ እንቅስቃሴያቸው የተገታባቸው ኃይሎች በአካባቢው የሚኖሩ "የሶማሌ ኢሳ ጎሳ ማህበረሰቦችን ከለላ በማድረግ" ህዝቡን እያጠቁ ይገኛሉ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። "አሸባሪ ለየትኛውም አካል አይወግንም እነሱን (የሶማሌ ኢሳ ጎሳ ማህበረሰቦችን) ከለላ አድርጎ ከመጣ የነሱንም ሰላም ሊያውክ የሚችል ኃይል እንደሆነ ታውቆ እራሳቸው እዛ ቦታ ላይ ሽብር ሊፈጥሩ የሚችሉ ኃይሎችን ቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር መቻል አለባቸው" ይላሉ አቶ አህመድ። በአካባቢው ተመሳሳይ ጥቃት እየተደጋገመ መምጣቱን የሚናገሩት አቶ አህመድ በቅርቡም በክልሉ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ምክኒያት ድጋፍ ለማድረግ የተንቀሳቀሱ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ልዑካኖች ላይ በደረሰው ጥቃት የአንድ ፀጥታ ኃይል ህይወት ማለፉንና አንድ ሌላ አባል ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል።

የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አህመድ ካሎይታ አክለውም "አገሪቷ ላይ የመጣውን ለውጥ የማይደግፉና የሚፃረሩ ከውጭም የራሳቸው የሆነ ተልእኮ ያላቸው ኃይሎች አገሪቷ የጀመረችውን የብልፅግናና የአንድነት ጉዞ ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ናቸው" ያሉ ሲሆን በክልሉ የሚፈፀመው ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃትም በእነዚሁ ኃይሎች ድጋፍም ጭምር የሚፈጸም ነው ይላሉ። "እነዚህ አሸባሪ ኃይሎች በድንገተኛ ሁኔታ ጥቃት እያደረሱ የሚገኙ ሲሆን በከባድ መኪና አሽከርካሪዎችም ላይ እንዲሁ ጥቃቱ እየተፈፀመ ይገኛሉ" በማለትም አቶ አህመድ ካሎይታ አብራርተዋል። እንደ ሃላፊው አባባል "ይሄ መስመር አለም አቀፍ መተላለፊያ ድንበር እንደመሆኑ መጠን የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት የፌደራል ፖሊስና መከላከያ ኃይል ነው። እነሱም የሚችሉትን እያደረጉ ይገኛሉ።" በማስከተልም "የኮንትሮባንድ ንግድ የተቋረጠባቸው አካላት ሊኖሩ ይችላሉ እነዚሁ ኃይሎች ናቸው ተደራጅተው የሽብር ጥቃት ፈፅመው የሚመለሱት"ያሉት ኃላፊው እንደዚህ አይነት ጥቃት የሚፈፅሙ ኃይሎችን አጎራባቹ የሶማሌ ክልልም ይሁን ሁሉም ሊያወግዝ ይገባል ብለዋል። ከዚህ ባለፈም "የኢሳ ማህበረሰብም በተለይም ገዳማይቱ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ከውስጣቸው ወጥቶ ሌሎች ላይ ጉዳት አድርሶ የሚመለሱ ኃይሎችን መታገል አለባቸው። ፀጉረ ልውጦችም ከታዩ ቀድሞ ለፀጥታ ኃይል መረጃ መስጠት ያስፈልጋል ሽፋን ከመሆን ይልቅ መከላከል ይገባል" የሚሉት አቶ አህመድ ባለፈው አመትም እንዲሁ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞ ከሰላም ሚኒስቴር እንዲሁም ከሶማሌ ክልል ጋር ችግሩን ለመፍታት ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙና አሁንም ግድያውን በጥልቀት ከማጣራት ሰራው ጎን ለጎን  የህዝብ ለህዝብ ውይይቱም ይቀጥላል ብለዋል።

በተያያዘ መረጃ በአፋር ክልል በሰራ ላይ እያሉ በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸውን ላጡት ሁለት የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በዛሬው ዕለት ሽኝት መደረጉን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። ሰራተኞቹ ወደ አፋር የተንቀሳቀሱት ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ሲሆን በትናንትናው ዕለትም በሚሰሩበት ቦታ ገዳማይቱ በምትባል አካባቢ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ እያሉ ነው ባልታወቁ ሰዎች በጥይት የተመቱት ሲሉ  የትምህርት ሚኒስቴር ኮሚዩኒኬሸን ጉዳዮች ዳይሬክተር ሐረጓ ማሞ ተናግረዋል። ሰራተኞቹ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ከማስቀጠልም በተጨማሪ በልጅነታቸው በመዳራቸውና በሌሎች ምክንያቶች ወደ ኋላ እየቀሩ ያሉ ሴቶችንም አትኩሮት በመስጠት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ወደ ቦታው መላካቸውን ያስረዱት ዳይሬክተሯ ከሄዱበት እለት ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ስራቸውን መስራት ችለው እንደነበርም ተናግረዋል። የሰራተኞቹ አስከሬን ከአፋር ክልል በዛሬው ዕለት ጥቅምት 18/ 2013 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ገብቷል። የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያን ጨምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ሰራተኞችም የማቾቹን አስከሬን ወደ የአካካቢያቸው መሸኘታቸውም ተጠቁሟል። በወቅቱም ሚንስትሩ ጌታሁን መኩሪያ የአበባ ጉንጉን ከማኖራቸው በተጨማሪ በሰራተኞቹ ሞት የተሰማቸውን ኃዘን ገልፀው ለወዳጅ፣ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል። ሁለቱ ሰራተኞች በተገደሉበት ወቅት የመቁሰል አደጋ ያጋጠመው ሌላኛው የሚኒስቴሩ ሰራተኛ አቶ ደምሴ ታምሬ ግን በክልሉ የቀዶ ህክም አድርጎ እያገገመ መሆኑን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያስረዳል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :