ጠቅላይ ሚንስትሩ በጅምላ ግድያው ዙሪያ በፓርላማ ተገኝተው ማብራሪያ እንዲሰጡ ም/ቤቱ አሳሳበ
ኢዜጋ ሪፖርተር
November 3, 2020 (Ezega.com) -- የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት 5ኛ ዘመን 6ኛ አመት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ለማካሄድ ነበር በዛሬው እለት የተሰየመው ያም ሆኖ ም/ቤቱ ለዛሬ እንዲወያይባቸው በአፈ ጉባኤው በኩል የቀረቡለትን አጀንዳዎች በተመለከተ ዜጎች ማንነታቸውን መሰረት ባደረገ ጥቃት እየተጨፈጨፉ በሌላ አጀንዳ ላይ አንወያይም በማለት አቋም የያዙ አባላት ምሬት አዘል ተቃውሞ ያቀረቡበት ሆኗል፡፡ በእምቢተኝነታቸው በፅናትም ለዕለቱ በተያዘውን አጀንዳ ዙሪያ ውይይት ከመጀመራቸው በፊት ከ2 ሰዓት በላይ ስለዚሁ ጉዳይ በእንባ ጭምር ሀሳባቸውን በስሜት ሲገልጹ በሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ጭምር ታይተዋል፡፡ "በመግለጫ ጋጋታ መፍትሄ አይመጣም፣ ድርጊትና እርምጃ ያስፈልጋል፣ ዛሬ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እየተጨፈጨፉ ዝም ካልን ነገ በሺዎች የሚቆጠሩ እንዲጨፈጨፉ መፍቀድ ነው" ሲሉ የሞገቱት አባላቱ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በተፈጸመው "አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ዙሪያ" ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ብሔራዊ የመረጃ ደህንነት፣ ሰላም ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ሚኒስትር እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በፓርላማ ተገኝተው ማብራሪያና ምላሽ እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡
ምክር ቤቱ ዛሬ ስብሰባውን በተለየ መንገድ ነው ነበር የጀመረው አፈ ጉባኤው የዕለቱን አጀንዳዎች በዝርዝር ከማቅረባቸው በፊት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ከትናንት በስቲያ በዜጎች ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ በተመለከተ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ የሚያሳስብ መግለጫ በንባብ ያቀረቡ ሲሆን በጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖችም የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል። "በዜጎች ላይ የብሔር ማንነትንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በየጊዜው እየተባባሰ በምን ሞራል ነው ሌላ አጀንዳ ላይ የምንነጋገረው? ሲሉ የጠየቁት አባላቱ "አልሸባብና አይ ኤስ ኤስን ለመመከት በሰው አገር ጭምር ሰላም የሚያስከብረው የመከላከያ ሰራዊታችን እውን ኦነግ ሸኔን ማሸነፍ አቅቶት ነው ወይ? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ "ከ2 ዓመት በፊት በለውጥ ስሜት ስራ ስንጀምር የነበረን ተስፋና ሞራል አሁን የለም ሲሉ በስሜትና በእንባ ታጅበው ሀሳባቸውን ሲገልፁ የተደመጡት አባላቱ የምዕራብ ወለጋ አካባቢ የሰላም የማጣት ችግር እንዳለበት እየታወቀ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከሚችል ሌላ አካል ጋር ርክክብ ሳይደረግ መከላከያው ለምን ከዛ ስፍራ ለቆ ወጣ? የሚለው መጠናትና ሪፖርት መቅረብ ያስፈልገዋል ከአስፈፃሚ የመንግስት አካላትም ማብራሪያ እንዲሰጠን እንፈልጋለን በማለትም አሳስበዋል፡፡
መንግስት ጥቃት በተፈፀመ ቁጥር ይህን ያደረገው ህወሃት ነው እያለ በተደጋጋሚ መግለጫ ሰጥቷል ጠላት ነው የተባለው ከታወቀ ለምን የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አልተቻለም? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ እንዲህ ባለ የጋለ ስሜት ከ2 ሰዓታት በላይ ከተወያዩ በኋላም በአጠረ ጊዜ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በምክር ቤቱ ተጠርተው ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡና አስፈላጊው ውሳኔ እንዲተላለፍ በመወሰን ወደ እለቱ አጀንዳቸው ተመልሰዋል ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዋጋ ቃንቃ ቀበሌ በንፁሀን ዜጐች ላይ አሰቃቂ ጥቃት ባደረሱ የጥፋት ሃይሎች ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስቧል፡፡ መላው የሀገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መንግስት በነዚህ የጥፋት ኃይሎችና አሸባሪዎች ላይ ለሚወስደው እርምጃ ከመንግስት ጐን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በአረመኔዊው ጥቃት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልፆ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን መመኘቱን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተመሳሳይ ፕሬዝዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንጹሀን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት "የሰማሁት አሰቃቂ ግድያ ልቤን በእጅጉ ሰብሮታል ንጹሀን ዜጎች በሌሎች እብደት ውድ ሕይወታቸውን የሚከፍሉበት ንብረታቸው የሚወድምበት መሄጃ አጥተው የሚንከራተቱበት ምንም ምክንያት የለም" ብለዋል። ፕሬዝዳንቷ "ዘርና ሀይማኖት ለፖለቲካ ጥቅም እንዲውሉ ሲደረግ ንጹሀን ዜጎቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ሲንከራተቱ ስናይ ስሜትን ለመግለጽ ቃላት ያጥራል ለቅሶ፣ ድንጋጤና ሥጋት የብዙዎችን በር አንኳኩቷል ሃዘናቸው ሃዘኔ/ሃዘናችን ነው" ያሉ ሲሆን "ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል አገራችንን ካንዣበበባት ክፉ አዳጋ ለማዳን ሁላችንም ሚና አለን የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ቀይ መስመሩም መጣስ የለበትም" በማለት መልእክታቸውን ደምድመዋል። በሌላ በኩል የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ባለፈው እሁድ ምሽት በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ የተፈፀመውን ጥቃት ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ ሊያወግዘው እንደሚገባ አስታዉቋል። የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሐም አለኸኝ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "የተፈፀመው ድርጊት ቀኝና ግራቸውን በማያውቁ ህፃናት፣ በእናቶችና በአዛውንቶች ላይ መሆኑን ድርጊቱን እጅግ አረመኔያዊ ያደርገዋል" ብለዋል። "ንፁህ ኢትዮጵያውያን የተገደሉት የፈፀሙት ወንጀል ኖሮ ሳይሆን አማራ በመሆናቸው ብቻ ነው ያሉት አቶ አብርሐም የድርጊቱ ፈፃሚዎችና አስተባባሪዎች ደግሞ በሽብር ተወልዶ፣ በሽብር ባደገውና ባረጀው ኦነግ ሸኔና በእርሳቸው አገላለፅ በለውጡ በተገፋው ሕወሓት" መሆኑን ተናግረዋል፡፡ …በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው ግልፅ ጭፍ ጨፋ፣ ግልፅ ጥቃት ዓለም ሁሉ ሊያወግዘው ይገባል፤ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሁሉም የክልል መንግስታት፣ ሁሉሙ የአማራ ክልል ብልፅግና ጽ/ቤቶች፣ የፌደራልና የክልል አመራሮች እንደዚሁም በአገራችንና በዓለም አቀፍ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ድርጊቱን ማውገዝ አለባቸው ነው ያሉት። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት ድርጊቱን የፖለቲካ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ፣ ለህዝብና ለሀገር በሚጠቅም መንገድ ለተገፋውና በአራቱም ማዕዘን እየተጨፈጨፈ ላለው፣ በማንነቱ ብቻ እየተገለለ ለሚገኘው የአማራ ማህበረሰብ ድምፅ ሁኑ ሲሉ ጥሪም አቅርበዋል። የድርጊቱ ጠንሳሸች "ኦነግና ትህነግ" ናቸው የሚል እምነት እናዳላቸዉ የተናገሩት አቶ አብርሐም በድርጊቱ ውስጥ በመንግስት፣ በፀጥታውና በፓርቲ መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ "ፍርፋሪ ለቃሚ ተኩላዎች" እንዳሉም አስረድተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት በኢትዮጵያ በንፁሃን ላይ የተፈፀመውን ግድያ አውግዘው የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀዋል፡፡ ሊቀ መንበሩ ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን እመኛለሁ ካሉ በኋላ መንግስት አጥፊዎችን ለህግ እንዲያቀርብም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አካታች ውይይት ያስፈልጋል የአፍሪካ ህብረትም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል ሊቀ መንበሩ፡፡ በሃገሪቱ ብሄር ተኮር ጥቃት እየተበራከተ መጥቷል ያሉት ሊቀ መንበሩ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ወደ ሰከነ ፖለቲካዊ ውይይት መምጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይም ሐገራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ አለመረጋጋት ለሃገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው አለመረጋጋት ምክንያት ይሆናልም ነው ያሉት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ፡፡ በኢትዮጵያ ለተጀመረው ሃገራዊ ለውጥ እና ሰላም አፍሪካ ህብረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ሊቀ መንበሩ መናገራቸውን ከአፍሪካ ህብረት ይፋዊ ገፅ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን