መከላከያ ሠራዊት በሕወሃት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ ታዘዘ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Defense-Ministry-EthiopiaNovember 3, 2020 (Ezega.com) -- ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የአገር መከላከያ ሠራዊት በህወሃት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መሰጠታቸውን ይፋ አደረጉ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለሊቱን በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው "ይህንን ጡት ነካሽ ኃይል ለማሳፈር እና ለመደምሰስ አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን እገልጻለሁ" በማለት በይፋ ጦርነት መከፈቱን አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ መከላከያ ሠራዊት አገር የማዳን ግዳጅ እንደተሰጠውም ያስታወቁ ሲሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከመቀሌ ጀምሮ በበርካታ ስፍራዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሞበታል ብለዋል፡፡ ይህ ጥቃት በሀገራችን እስካሁን ከደረሱ ጥቃቶች እጅግ አስነዋሪ የሚያደርገው ሠላም ለማስከበር በተሰማራው መከላከያ ሠራዊት በውጭ ሀይሎች ያልደረሰበትን ጥቃት በገዛ ወገኖቹ ከጀርባው እንዲመታ፣ ብዙዎች እንዲሰው ፣እንዲቆስሉ፣ ንብረቶች እንዲወድሙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ "ሕወሐት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል፡፡ ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል" በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ ለጦርነቱ መጀመር ዋነኛው መነሻ ይህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ጠቅላይ ሚንስትሩ ሠራዊቱ ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ መሆኑን ገልፀው በቦታው የሚገኘውም የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው ያሉ ሲሆን "ሕወሐት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል" ብለዋል፡፡

አክለውም "የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብም ታልፏል፡፡ ጦርነት ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል" በማለት ገልፀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ ህወሃት በዳንሻ በኩል በአማራ ክልል ላይ የፈፀመው ጥቃት በአማራ ክልል በነበረው ኃይል ተመክቷል ብለዋል፡፡ ሕወሃት ቀድሞ ባሰለጠኑት፣ ባሰማሩት እና ባዘጋጁት ኃይል በተለያየ ቦታ፣ በተለያየ ከተማ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ሊፈፀም ስለሚችል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚሊሻው፣ ከፖሊስ ሰራዊት፣ እንዲሁም በአካባቢያቸው ከሚገኝ የመከለካያ ሰራዊት ጋር በመተባበር አካባቢውን እንዲጠብቅም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሳስበዋል፡፡ የመከላከያ ሰራዊቱ ከጠቅላይ ሰፈር በሚሰጥ ትዕዛዝ መለዮውን ሀገሩንና ሕዝቡን እንዲከላከል ለሚከፍለው መስዋዕትነት ዛሬም እንደተለመደው በታሪኩ ውስጥ የሚታሰብ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ   ይህ እኩይ ኃይል መጥፊያው በመድረሱ በሰላም፣ በንግግር እና በውይይት ሊፈቱ የሚችሉ ነገሮችን ባለፉት ጥቂት ቀናት ካለምንም ሀፍረት በሚዲያ በመውጣት “ከየትኛውም የውጭ ኃይል ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን እወጋለሁ” ብሎ ሲያውጅ የነበረው ኃይል ንግግሩን በተግባር አውሎታል ብለዋለ፡፡

“የትግራይ ህዝብ ወገኔ፣ ዘመዴ እና ሕዝቤ ብሎ ላለፉት 20 ዓመታት በቀበሮ ምሽግ ውስጥ በመሆን መስዋዕትነት የከፈለው እና ሰላሙን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ ያደረገው የመከላከያ ሰራዊት የደረሰበት ጥቃት ጥቃትህ መሆኑን በመገንዘብ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ሀገርህን ከነዚህ ከሃዲ ኃይሎች እንድትከላከልና በንቃት እንድትጠብቅ አሳስባለሁ” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ይህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ አሳዘኝ እና አሳፋሪ ተግባር ቢሆንም ዛሬም እንደተለመደው በተደመረና በተባበረ ክንድ ይህንን “ከሃዲ ጡት ነካሽ” ኃይል ለማሳፈርና ለመደምሰስ አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡“ይህ አሳፈሪ ተግባር በማይደገምበት ሁኔታ የሚቀለበስበትን ተግባር መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የሀገር መከላከያ ሰራዊት በመተባበር የሚፈፅሙት ይሆናል ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች አስፈላጊውን መረጃ በየጊዜው በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚሰጥ መሆኑን እገልፃለሁ” ብለዋል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፡፡

በተያያዘ በሺህዎች የሚቆጠሩ የህወሓት ልዩ ሀይል አባላት ለኤርትራ ወታደሮች እጃቸውን ሰጡ ሲሉ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ በሁመራ በኩል አቋርጠው ወደ ኤርትራ ድንበር የዘለቁ በሺኅዎች የሚቆጠሩ የህውሐት ልዩ ሀይል አባላት ለኤርትራ ወታደር እጃቸውን መስጠታቸውን ኤርትሪያን ፕሬስም አስነብቧል፡፡ የህወሓት ልዩ ሀይል አባላት እጃቸውን የሰጡት ህወሓት በመከላከያ ሀይልና በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መከላከያ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡ ያም ሆኖ በክስተቱ ዙሪያ ከህውሃት በኩል እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡ ከፌደራሉ መንግስት ጋር ውጥረት ላይ የሚገኘው የትግራይ ክልል መንግሥት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት "በትግራይ ላይ የኃይል እርምጃ ወደ መውሰድ እየተሸጋገረ ነው" ሲል መግለጫ የሰጠው ሰኞ እለት ነበር የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ መንግሥት በትግራይ ላይ የሃይል እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል በመግለጽ 'ሕብረተሰቡ ዝግጅቱን አጠናክሮ ይቀጥል' ብለዋል፡፡ "ብዙ ጫናዎች ብዙ የሚድያ ዘመቻዎች ብዜ የኢኮኖሚ ዱላዎች ያደረሰብን ሳይበቃው አሁን ደግሞ በኃይል እጨፈልቃለሁ ብሎ እየተንቀሳቀሰ ነው። ብዙ ምልክቶችም አሉ" ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ሲናገሩ ከትግራይ ክልል ጋር የተከሰተው አለመግባባት "በሕግ እና ሕግ ብቻ የሚመለስ ይሆናል" በማለት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :