በህወሃት ላይ የተወሰደው የመጀመሪያ ዙር ኦፕሬሽን በስኬት ተጠናቋል - ዐቢይ አሕመድ
ኢዜጋ ሪፖርተር
November 6, 2020 (Ezega.com) -- በህወሓት ውስጥ "የመሸገው ኃይል ላይ የተወሰደው የመጀመሪያው ዙር ኦፕሬሽን በስኬት እንደተጠናቀቀ" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ። የመጀመሪያው የመከላከል እቅድ ሙሉ ለሙሉ በስኬት መጠናቀቁን የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ የእቅዱ ዋነኛ አላማዎች በሁሉም አቅጣጫ "የጥፋት ሃይሉ" ጥቃት እየሰነዘረ በህዝብ፣ በሰራዊቱ፣ በፖሊስ ላይ እና በአንዳንድ ወሳኝ የመሰረተ ልማቶች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት መግታት፣ የመከላከያ እና የፖሊስ ሰራዊት የደረሰበትን ጥቃት ተከትሎ ይህንን ኃይል የመታደግ እና ወሳኝ ሀገራዊ ሀብቶች አና ትጥቆች መታደግ እና "የጠላትን የማድረግ አቅም ማዳከም" ነው ብለዋል። "በተለያየ አካባቢ ይገኝ የነበረ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ወደ ስፍራው በማንቀሳቀስ የጠላትን ጉዞን ሙሉ ለሙሉ በማስቆም ተጨማሪ ጥቃት መሰንዘር ወደማይችልበት ደረጃ ማድረስ ተችሏል" ያሉት አብይ አህመድ በባድመ ግንባር፣ በፆረና እና በዛላንበሳ በዋና ዋና ስፍራ ተሰልፈው ያሉ የሰራዊት አባላት እና ትጥቆች ሙሉ ለሙሉ ከጠላት ፍላጎት ውጭ ለማድረግ ተችሏል ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል "የጠላት ኃይል የኢትዮጵያ ህዝብ ከሌለው ሀብት ላይ ቀንሶ ሀገሩን ለመከላከል የገዛቸውን ዋና ዋና ትጥቆች፣ ሚሳኤሎች፣ ሮኬቶች በመጠቀም ጥፋት ማካሄድ እንዳይችል አቅሙን ማዳከም ተችሏል" ያሉት ጠቅላይ ሚንስተሩ የአየር ሀይሉ በወሰደው እርምጃ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ የነበሩት ሮኬቶችን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ለማውደም መቻሉንም ገልፀዋል። እነዚህ ሮኬቶች እስከ 300 ኪሎ ሜትሮች መወንጨፍ የሚችሉ በመሆናቸው እና "በወንጀለኛው ቡድን ሮኬቶቹን የመጠቀም ፍላጎት መኖሩ በመረጃ በመረጋገጡ በመቀሌ እና አካባቢዋ በነበረው የከባድ መሳሪያ ማስቀመጫ ላይ የአየር ኃይሉ እርምጃ እንዲወስድ መደረጉ" ተገልጿል። በዚህም ሦስቱ ዓላማዎች መቶ በመቶ መሳካታቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ሌላ "በዳንሻ ግንባር ያለውን ጠላት ሙሉ ለሙሉ በመደምሰስ አካባቢውን መቆጣጠር መቻሉንም" አስታውቀዋል። በቀጣይም "ስግብግቡ ጁንታ ሙሉ ለሙሉ ለሕግ እስከሚቀርብ ድረስ" የሚደረገው እራስን እና ሀገርን የመከላከል ዘመቻ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አረጋግጠዋል።
በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀንና ለሊት ጭምር የአየር ጥቃት ስለሚኖር ነዋሪዎች በከተሞችና ሌሎች ኢላማ ሊሆኑ በሚችሉ አካባቢዎች እንዳይሰበሰቡ አስጠንቅቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በብሄራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው በትግርኛ ቋንቋ ለትግራይ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት የአየር ጥቃቱ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ እንዳልሆነና "አደገኛ" ብለው የጠሩትን ኃይል የያዛቸውን ቦታዎች ኢላማ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል። "በዚህም ሁኔታ ያልታሰበ አደጋ እንዳይመጣ ነዋሪዎች በከተማ አካባቢ ተሰብስባችሁ መንቀሳቀስ እንድትቀንሱ አሳስባለሁ" በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ከዚህ ሌላ የነዳጃና የጦር መሳሪያ ዴፖዎች፣ ካምፖችና ተፈላጊዎቹ "የህገወጥ ቡድኑ አባላት" የሚገኙባቸው አካባቢዎች ኢላማዎች በመሆናቸው ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌደራል መንግሥት በህወሃት ላይ የከፈተውን ጦርነት ህገ መንግሥቱን የማስከበር ሂደት ነው ካሉ በኋላ"ተገደን የገባንበት ጦርነት ነው" ብለዋል። "የተከበረው መከላከያ ሰራዊታችን ተኝቶ እያለ አጥቅተዋል። ዓለም እያየ ጥቃት ፈፅመዋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ "ሁሉም ህወሃት አይደለም ጠላታችን ጠላታችን በህወሃት ውስጥ ያለ ሃይል ነው" ሲሉ አክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጀምሮ አገርን ሰላም ለማድረግና ብልፅግና ለማምጣት ሲሰሩ መቆያታቸውን ጠቅሰው በዚህ ወቅት ግን "ህወሐት ውስጥ ያለው ከሃዲ ሃይል ጉዟችንን ሲያደናቅፍ ቆይቷል። ልማት ሲያደናቅፍ ነበር "ይህ ሃይል የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ተነጥሎ የሰላምና ብልጽግና ተካፋይ እንዳትሆን አድርጎሃል" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ህዝብ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲጠላ በስሙ ብዙ መጥፎ ነገሮች ተሰርቷል ያሉ ሲሆን ህገ መንግስቱም በተደጋጋሚ ተጥሷል ሲሉ ከሰውታል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን