በአዲስ አበባ በዜጎችና መሰረተ ልማቶች ላይ የፈንጂ ጥቃት ለመፈጸም የተንቀሳቀሰ ቡድን ተያዘ - ብሄራዊ መረጃና ደህንነት
ኢዜጋ ሪፖርተር
November 6, 2020 (Ezega.com) -- ከህወሃት ተልእኮ ተሰጥቷቸው በአዲስ አበባ በሚኖሩ ንጹሃን ዜጎችና መሰረተ ልማቶች ላይ በተለይም በለገዳዲና ገፈርሳ የሚገኙ የውሃ ግድቦች እንዲሁም በለገጣፎ የሚያልፍ ከፍተኛ የውሃ ማስተላለፊያ መስመር ላይ የፈንጂ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ የኦነግ ሸኔ አባላት ለጥፋት ተልዕኳቸው ካዘጋጇቸው ተቀጣጣይ ፈንጂዎችና ሌሎች ቁሶች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ብሄራዊ መረጀና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡ የጥፋት ተልዕኮቸው "ባይከሽፍ ኖሮ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ሰብኣዊ ቀውስ" ያስከትል እንደነበር በመግለጫው ያስታወቀው ተቋሙ የጥፋት ተልእኳቸውን ሳይፈጽሙ የተያዙት ቶሎሳ አብዲሳ፣ ደጀኔ ፍቃዱ፣ ሀብታሙ፣ ተስፋየ መርጋ፤ ንጉሴ አሰፋና ፈልማት ታከለ የተባሉ ተጠርጣሪዎች መሆናቸውን አመልክቷል፡፡ በሌላም በኩል ጋዲሳ ሞሲሳ ባይሳ የተባለው የጥፋት ቡድኑ አባልና ግብርአበሮቹ ደግሞ በአዲስ አበባ በንጹሃን ዜጎች ላይ የቦንብ ጥቃት ለመፈጸም ካዘጋጇቸው ቦንቦች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስተውቋል፡፡
በተለይ "የወንበዴው የህዋሃት ቡድን ለጥፋት ተልዕኮው ሽፋን ንስር ጥበቃ ድርጅትን በመጠቀም ከወንበዴው ስልጠና የወስዱ ሃይሎችን በስሩ በማደራጀት በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ለመፋፀምና ጥፋት ለማድረስ በዝግጅት ላይ እያሉ" በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ብሏል ብሄራዊ መረጀና ደህንነት አገልግሎት ፡፡
"የህዋሃት የጥፋት ቡድን በትግራይ ክልል ሃግቦ በተባለ አካባቢ ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት የገዳይ እስኳድ ቡድን ባለቤትነቱ ሀይሉ በርሄ በቅፅል ስሙ ሀይሉ ሳንቲም ተብሎ በሚጠራው የጥፋት ቡድን አስተባባሪ ስም በተቋቋመው ንስር የግል ጥበቃ ኤጀንሲ ሽፋን ካስገባ በኃላ ነበር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፌደራል ፖሊስና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በቅንጅት ባደረጉት ጥብቅ ክትትል የቡዱኑ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለው" ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ አዲስ አበባ ሆኖ ለወንበዴው ለህዋሃት የጥፋት ቡድን የተለያዩ መረጃዎችን እያሰባሰበ ሲልክ የነበረና ከኦሮሚያ ወጣቶችን እየመለመለ ለስልጠና ወደ ትግራይ በመላክና የተለያዩ የአመፅ ተልዕኮዎችን ከጥፋት ቡድኑ በመቀበል ኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ የኦነግ ሸኔ የጥፋት ቡድኖች ሲያስተላልፍ የነበረው ቶማስ ገብረማሪያም የተባለው ተጠርጣሪም በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል ብሏል መግለጫው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጥፋት ቡድኑ ስር በኦሮሚያ ክልል በአዳማ፣ በሲዳማ ክልል ሃዋሳ፣ በደቡብ ክልል ደግሞ በወላይታ፣ ጋሞጎፋ፣ ሃድያ፣ ስልጤና ጌዲዮ ዞኖች እንዲሁም በሱማሌ ክልል ጅጅጋና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተመሳሳይ ትርምስና እልቂት በተላላኪዎች ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በድምሩ 21 ተጠርጣሪዎች ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና መሰል ቁሳቁሶች ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን አግልግሎት መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ከህዋሃት የጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በህዝብ እልቂት በማድረስ አገርን ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት አለም ደስታ፣ ሃየሎምና፣ ጋትክቦም የተባሉ የጥፋት ቡድኑ ተጠርጣሪዎች ባሉበት ታድነው" በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ተፈጽሞ የነበረውን ተመሳሳይ ጥፋት በአሶሳና ካማሼ ዞኖች ብሔር ብሄረሰቦችን በማጋጨት አካበቢውን የትርምስ ቀጠና በማድረግ በህዝብ ላይ እልቂት ለመፈጸም "ከወንበዴው ህዋሃት የጥፋት ቡድን አባል ከሆነው አባይ ፀሃዬ ተልዕኮ ወስደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጥርጣሪዎች" በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መገለፁ ይታወቃል፡፡ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በተጨማሪም አራት የህዋሃት የጥፋት ቡድን አባላት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል። የተያዙት አራት የዚህ የጥፋት ቡድን አባላት ተጠርጣሪዎችም ተክላይ ገብረ መድህን፣ ፍሰሃ ወልደ እግዚአብሄር፣ አብርሃ ገብረ ሚካኤል እና ተስፋ ገብረ ሚካኤል የተባሉ መሆናቸውን አገልግሎቱ በመግለጫው አስታውቋል። "ከህዋሃት የጥፋት ቡድን ተልዕኮ በመቀበል በህዝብ ላይ ጭፍጨፋ እንዲፈጸም ስምሪት የተሰጣቸው አራት ከላይ የተገለፁት የጥፋት ሃይሎች በእጃቸው 59 የሚሆኑ የባንክ ደብተሮች የያዙ ሲሆን ተክላይ ገብረ መድህን የተባለው ተጠርጣሪ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ባንኮች 19 የሂሳብ ደብተሮችን ከፍቶ ሲያንቀሳቅስ ከመቆየቱም በላይ በአንዱ የሂሳብ ደብተር ውስጥ ብቻ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱን መግለጫው ጠቁሟል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማነ ግርማይና ዮሃንስ ግርማይ የተባሉ የህዋሃት የጥፋት ቡድን ተላላኪዎችን ጨምሮ በድምሩ 23 ተጠርጥሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስተውቋል፡፡
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን