የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወሰነ

ኢዜጋ ሪፖርተር

House-Federaion-EthiopiaNovember 7, 2020 (Ezega.com) -- የፌዴሬሽን ም/ቤት ዛሬ ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ "ሕገወጡ የትግራይ ክልል መንግስት ወደ ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱ እንዲመለስ የተሰጠውን በቂ እድል መጠቀም ባለመቻሉ በክልሉ በሚገኘው ጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አስነዋሪ ጥቃት ፈጽሟል በተጨማሪም በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በንፁሃን ዜጎችና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል" ያለው ም/ቤቱ  የፌዴራል መንግስት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 12 በአንድ የክልል መንግስት ተሳትፎ ወይም ዕውቅና ሕገመንግስቱን ወይም ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት በተለይም በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ክልል ብሔር፣ ብሄረሰብ ወይም ሕዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍታት፣ የፌዴራሉን ሰላምና ጸጥታ ማናጋት ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ እንደሚቆጠር ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ አንጻር "ሕገወጡ የትግራይ ክልል መንግስት የፈጸመው እና እየፈጸመ ያለው ድርጊት ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ" ተጨማሪ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ ተረጋግጧል ብሏል፡፡

በዚሁ መሰረት የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ም/ቤት በሕገመንግስቱ አንቀጽ 62 (9) ማንኛውም ክልል ሕገመንግስቱን በመጣስ ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ሥልጣን እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 36 መሰረት የፌዴሬሽን ም/ቤት በአንድ ክልል ውስጥ ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ ሲያምን የፌዴራሉ መንግስት ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዝ እንደሚችል እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 13 (4) ም/ቤቱ የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ጣልቃ እንዲገባ ሊያዝ እንደሚችል በመደንገጉ "ሕገወጡ የትግራይ ክልል መንግስት ሕገመንግስታዊ እና የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመፈጸም የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ስለሆነ ይህንን ድርጊት ማስቆም ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል" ብሏል፡፡ በመሆኑም፦

1. ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት ለማስቆም የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ ትዕዛዝ ሰጥቷል እንዲሁም አደጋውን ለማስወገድ እንዲቻል የፌደራል ፖሊስን ወይም የሃገር መከላከያ ሠራዊትን ወይንም ሁለቱንም በክልሉ እንዲያሰማራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

2. "ሕገወጡን የክልሉ ምክር ቤት እና የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ታግዶ ለፌደራል መንግስቱ ተጠሪ የሆነና በአዋጅ 359/1995 አንቀጽ 15 ላይ የጠቀመጡት ሥልጣንና ተግባራት የሚኖሩት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም" ወስኗል፡፡

3. ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን የምክር ቤቱ ውሳኔዎች አፈጻጸምና ክልሉ ሰለሚገኝበት ሁኔታ በተመለከተ  የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ አስፈላጊነቱ ለፌዴሬሽን ም/ቤት በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ በማለት ወስኗል፡፡

ውሳኔው በተሰማ በሰአታት ልዩነት ውስጥ ምላሹን የሰጠው የትግራይ ክልል መንግስት በበኩሉ "ይህ የቁም ቅዠት በትግራይ ሊተገበር ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል ነው" ሲል አጣጥሎታል። "በፈለገው ጊዜና ቦታ፣ የሚፈልገውን እርምጃ የመውሰድ ብቃትና ችሎታ ያለውና የአላማ ፅናት የተለበሰው የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሚመራው የትግራይ ህዝብ አዲስ ተጨማሪ ደማቅ ታሪክ እንደሚፅፍ በአጠቃላይ ወዳጅም ጠላትም በዋነኛነት የኢትዮዽያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፈፅሞ ሃሳብ ሊገባቸው እንደማይገባ ሊሰመርበት ይገባል" ያለው የክልሉ መግለጫ "ሰማይና መሬት ቢገላበጥ የትግራይ ህዝብ ማንነቱን አሳልፎ ለማንም ምድራዊ ሃይል እንደማይሰጥ በተግባር ያስመሰከረ ህዝብ ነው" ብሏል።  "የኢትዮዽያና የኤርትራ ህዝቦች ቀንደኛ ጠላት የሆነው የሻእቢያ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ" ኢትዮጵያን የማፈራረስ እኩይ ተግባሩን እያፋጠነ ነው ያለው መግለጫው "ፋሽስቱና አሸባሪው አሃዳዊው አምባገነን ቡድን በትግራይ ህዝብ ላይ ያወጀው ጦርነት የትግራይ ህዝብን ብቻ አይጎዳም ኢትዮጵያን የሚበታትን፣ ስድስት የምስራቅ አፍሪካ ሃገራትን፣ የሚያፈራርስና የአሸባሪዎች መፈንጫ የሚያደርግ አደገኛ የሽብር ጦርነት ነው" ብሎታል

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች "የራሳችሁን እድል በራሳችሁ ለመወሰን የጀመራችሁትን ትግል በተደራጀ አኳኋን አጠናክሯችሁ ልትቀጥሉበት ይገባል" ያለ ሲሆን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበር "ዋልታና መከታ የሆንከው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም ከማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ጋር ደም ልትቃባ አይገባም ይልቁንም የሰሜን እዝ አመራሮችና የሰራዊት አባሎች የወሰዱትን አቋም እንደምሳሌ ወስደህ ልትተገብር ይገባል" ሲል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ በተጨማሪም የትግራይ ህዝብና ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የትላንት፣ የዛሬም ሆነ የነገ ፍላጎትና ምኞት የተፈጠሩ ችግሮች በሰላምና በውይይት ብቻ እንዲፈቱ ነው ያለው ህወሃት ምንም እንኳን "በአሸባሪውና በጦር አምላኪው አሀዳዊ አምባገነን ቡድን አሻፈረኝ ባይነት የሰላም በር የተዘጋ ቢሆንም እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ጥረቱ ይቀጥላል" ሲል አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ "የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ሃይሎች ጥምረት ያወጡት የሰላም ጥሪ ተግባራዊ እንዲሆኑ፣ ፋሽስታዊ አምባገነናዊ ቡዱንም ይህን የሰላም አማራጭ ወዶ ሳይሆን ተገዶ እንዲቀበለው እንድታደርጉ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን' ብሏል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :