ጠቅላይ ሚንስትሩ ድንገተኛ ሹም ሽር አደረጉ

ኢዜጋ ሪፖርተር

PM-Abiy-Ahmed-ReshuffleNovmber 8, 2020 (Ezega.com) -- ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ዛሬ ቁልፍና ድንገተኛ የተባሉ ሹም ሽሮችን አካሄደዋል። ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እንደተፈጸሙ የተነገሩት ሹም ሽሮች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል መንግስት ባለስልጣናትን ማእከል ያደረጉ ናቸው በዚህም መሰረት፦  

- አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
- ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም
- ሌ/ጄኔራል አበባው ታደሰ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም
- አቶ ተመስገን ጥሩነህ የብሔራዊ መርጃና ድህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር
- አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ
- ኮሚሽነር ደመላሽ ገ/ሚካኤል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።

አዳዲሶቹ ሹመቶች የሀገሪቱን የጸጥታና የደኅንነት ብሎም የውጭ ግንኙነት አካላትን በማጠናከር የተጀመረውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ "በአጭር ጊዜ በብቃት ለመወጣት የተደረገ የአመራር ሽግሽግ" እንደሆነም ተገልጿል። ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ሲገደሉ የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሆነው የተሾሙት ጄኔራል አደም መሐመድ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ምክትላቸው የነበሩት ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሆነዋል። በተያያዘ ባለፈው ሳምንት ጥሪ ተደርጎላቸው የኢትዮጵያን ጦር የተቀላቀሉት ሌቴናል ጄኔራል አበባው ታደሰ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነው ተሹመዋል። በተጨማሪ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነዋል። በዛሬው ሹም ሽር የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ከኃላፊነታቸው ተነስተው በምትካቸው ኮሚሽነር ደመላሽ ገ/ሚካኤል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።

በተያያዘ ዜና የአማራ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው ስብሰባ በአቶ ተመስገን ምትክ የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩትን አቶ አገኘሁ ተሻገርን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል። የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ አቶ አገኘሁ ተሻገር በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መኃላ ፈፅመዋል። አቶ ተመስገን ጥሩነህ ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር "በተሠጣቸው ተልእኮ ምክንያት ፓርቲያቸው በተሠለፈበት ሀገርን የማዳን ስራ" ላይ የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት ስምሪቱን መቀበላቸውን ለምክር ቤቱ አባላት ገልፀዋል። አቶ ተመስገን ጥሩነህ ያቀረቡትን የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ የምክር ቤት አባላቱ በጉዳዩ ላይ ካካሄዱት ሠፊ ምክክር በኋላ ተቀብሏል።

በተመሳሳይ በወቅታዊ የሀገሪቱ እና የክልሉ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ የመከረው የአማራ ክልል ም/ቤት የአማራ ክልል መንግስት የክልሉ ህዝብ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ ጥፋት በፈፀሙ የጥፋት ሃይሎች ላይ ህግ ለማስከበር የወሰደውን እርምጃ እና በክልሉ ውስጥ የተገኘውን ሰላም በአዎንታ የሚያይ ሆኖ ከሃገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የውስጥ አቅምን በማጠናከር ህግ የማስከበሩ ስራ መቀጠል ይኖርበታል ሲል አሳስቧል። የአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና የሚሊሻ ሰራዊት "ህገ ወጡ የትህነግ ቡድን የፈፀመውን ጥቃት ለመከላከል ላደረጉት ቆራጥ ተጋድሎ" የክልሉ ምክር ቤት ክብር እና እውቅና እንዲሰጠው፣ "ትህነግ እና የእርሱ ተላላኪ የሆነው የኦነግ ሸኔ ቡድን ዘርን ማእከል በማድረግ በንፁሃን አማራዎች ላይ የፈጸሙውን ግድያ መንግስት እውቅና እንዲሰጥና ድርጊቱ ድጋሚ እንዳይፈፀም ብሎም ህገ መንግስታዊ መብታቸው እንዲከበር ከለላ እንዲሰጣቸው" ሃላፊነቱን እንዲወጣ፣ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ካሳ እንዲያገኙ እና የተፈናቀሉ ወገኖችም ወደመደበኛ ቦታቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ፣ የአማራ ክልል መንግስት ከክልሉ ውጭ በሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ላይ የሚፈፀም ወከባ፣ ግድያ እና መፈናቀል እንዲቆምና ዜጎች ተረጋግተው እንዲኖሩ ከፌደራል መንግስት እና ከሌሎች ክልል መንግስታት ጋር በቅንጅት ተቀራርቦ እንዲሰራ ጉዳዩንም በአንክሮ እንዲከታተልም ጠይቋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :