ህወሃት በማይካድራ በንፁኃን ዜጎች ላይ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ፈፀሟል - ደመቀ መኮንን
ኢዜጋ ሪፖርተር
November 11, 2020 (Ezega.com) -- በትግራይ ክልል ማይካድራ አካባቢ "በንፁኃን ዜጎቻችን ላይ የደረሰው እጅግ ልብ ሰባሪ፣ ኢሰብዓዊ እና ፍፁም አሳዛኝ ዘር-ተኮር ጭፍጨፋ በከሃዲው ቡድን አስተባባሪነት የተፈፀመ ይቅር የማይባል ወንጀል ነው" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡ አቶ ደመቀ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት "ይህ ጭፍጨፋ እጅግ ሰው መሆንን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ዘግናኝ ድርጊት ነው።" አክለውም በምድር ላይ ያሉ የመጨረሻ የክፋት መገለጫዎችን ከመፈፀም ወደ ኋላ የማይመለሰው ይህ "ከሃዲ ቡድን በተለያዩ ክልሎች ፅንፈኞች እና አሸባሪዎችን እያስተባበረ ስምሪት እየሰጠ እና በፋይናንስ እየደገፈ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጭፍጨፋ መፈፀሙን ቀጥሎበታል" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ከሃዲው ቡድን ከቀናት በፊት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊታችን አባላት ላይ የፈፀመው አሳዛኝ ጭፍጨፋ ሳይበቃው አሁንም በንፁኃን ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ ገፍቶበታል ይህን እኩይ ድርጊቱን የቀጠለበት ምክንያት የኢትዮጵያውያንን አንድነት እና የአብሮነት ክብር ለማዋረድ ቆርጦ የተነሳበትን ዓላማ እስከመጨሻዋ ሰዓት ድረስ ለማስፈፀም ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ "ኢትዮጵያ በዘመናት ገፀ-ብዙ ፈተናዎች ያሳለፈች ሃገር ብትሆንም፤ በታሪኳ እንደህውሃት ዓይነት የወጣለት አረመኔ እና የጭካኔ ጫፍ የተቆናጠጠ ወንጀለኛ ቡድን ገጥሟት አያውቅም" ያሉት ሚኒስትሩ ቡድኑ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ የተግባር ስሪት አራማጅ እንዲሁም ፀረ-አማራ የሆነ የአስተሳሰብ ቅኝት ወላጅ ሆኖ ለበርካታ ዓመታት ሰፊውን ማህበረሰብ ሲያደናግር ቆይቷል" ብለዋል፡፡ በተፈጠረበት ቅኝት እና ባደገበት ስሪት ሁልጊዜ "የበላይ" ሆኖ ለመኖር ካለው የተንጠራራ ምኞት የተነሳም ከሌሎች የሃገራችን ህዝቦች ጋር
በእኩልነት መራመድ ውርደት ስለሚመስለው ጥፋትን የስነ-ልቦና ስብራቱ ማካካሻ አድርጎት ዘልቋል ሲሉም አቶ ደመቀ አብራርተዋል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው እንደገለጹት "በአሁኑ ሰዓት ሃገራችን በእጅጉ ፍትህን ተጠምታለች ህዝብ እና መንግስት በጀመሩት የጋራ ርብርብ የከሃዲያኑን ስብስብ በፍጥነት ወደ ህግ ያቀርቡታል እንዲሁም በማያዳግም ሁኔታ ያስወግዱታል" ያሉ ሲሆን አሁንም ከሃዲ ቡድኑ በአንድ በኩል ሰላም በሌላ በኩል ጥፋት እያጣቀሰ ጊዜ ለመግዛት የሚያደርገው ጥረት ብዙ ርቀት የሚያደርስ ባለመሆኑ "ለዕውነት እና ለፍትህ መረጋገጥ ሲባል መንግስት የጀመረው ህግና ስርዓት የማስከበር ኦፕሬሽን እስከመጨረሻው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል" ነው ያሉት፡፡
በተያያዘ ዜና በሁመራ አቅራቢያ በምትገኘው ማይካድራ ከተማ ነዋሪ በሆኑ የአማራ ወገኖች ላይ በተሸናፊው የትህነግ ጦር አማካኝነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል ሲል የአማራ ክልል አስታውቋል። የሟቾቹ ቁጥሩ "በሂደት ተጣርቶ ይፋ የሚደረግ መሆኑን እያሳወቅን ድርጊቱ ግን በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን እናምናለን" ያለው የክልሉ መግለጫ "እየሞትንም ቢሆን እናሸንፋለን ትህነግ በወገኖቻችን ላይ ይሄን አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈፀመው በህዝቦች መካከል የእርስ በርስ ጦርነት (Civil War) እንዲቀሰቀስ አስቦ መሆኑንም እናውቃለን" ብሏል። የአማራ ክልል ህዝብ "በተለመደው አስተዋይ ባህሪህ ምስኪኑን የትግራይ ህዝብ እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም ከየትኛውም ጥቃት ጥላ ከለላ ሁነህ ይህን ጊዜ እንድታሳልፈው ይሁን በባህል፣ በሃይማኖት፣ በማህበራዊ ትስስር፣ አልፎም በረዥሙ የአገር ግንባታ ጉዞ ከአማራ ሕዝብ ጋር የጋራ ታሪክ ያለውን የትግራይ ሕዝብ መከታና ጋሻ ሆነው አስተዋይነትና አብሮነት የምንጊዜም ምርጫህ እንደሆነ ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተግባር እንድታሳይም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን" ያለ ሲሆን የትግራይ ሕዝብ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም ሆነ ነገ አብሮህ ይኖራል። ዝንታለም ጠላትህ ትህነግና ወገኖችህን የጨረሰው የትህነግ ሰራዊት ነው። ስለዚህ ትህነግ ካጠመደልህ ወጥመድ ሳትገባ የወገኖችህን ደም የምትመልሰው ትህነግንና ገዳይ ሰራዊቱን እስከመጨረሻው በመፋለም መደምሰስ ሲቻል መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን ሲልም ጥሪውን አስተላልፏል።
በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ም "ዛሬም እንደ ትላንቱ አሸባሪው የትሕነግ ቡድን በሰላማዊ ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሟል! ሲል ከስሷል። ንቅናቄው በክስተቱ ላይ ባወጣው መግለጫ "በማይካድራ ከተማና አካባቢው በነበረው የትሕነግ ጦር ላይ በተከፈተው መጠነ ሰፊ ጥቃት ምክንያት ሸሽቶ የፈረጠጠው የትሕነግ ጦር ከተማዋን ከመልቀቁ በፊት ንፁሀን ሰላማዊ ዜጎችን በአማራ ማንነታቸው ብቻ ለይቶ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደፈፀመባቸው ተረጋግጧል" ነው ያለው። የትሕነግ ጦር የአካባቢውን "አማራ ህፃናትና እናቶች ሳይቀሩ ገጀራ፣ የተለያዩ ስለት ያላቸውንና ማነቂያ ገመድ በመጠቀም ጭምር በጅምላ ጨፍጭፎ ከቦታው ለቆ መውጣቱ ታውቋል በርካታ አስክሬኖችን በትራክተር ለማጓጓዝ ሙከራ እያደረገ ባለበት ሁኔታም የመከላከያ ሰራዊትና የአማራ ሀይል ስለደረሱበት አስከሬኖችን በየቦታውና በየቱቦው ጥሎ ሄዷል" ሲል አብን አስታውቋል። ስለሆነም ከጠቅላይ ሰፈር በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረት መንግስት በጎንደር - ወልቃይት፣ ፀገዴ፣ ሁመራና በቀሪዎቹ አካባቢዎች እና በራያ በተለያዩ አካባቢዎች ትሕነግ ከመሸሹ በፊት ተመሳሳይ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን እንደሚፈፅም ታሳቢ በማድረግ የቅድመ መከላከልና ንፁሀንን የመታደግ ስራ ላይ ትኩረት እንዲደረግ በአፅንኦት እንጠይቃለን ብሏል።
"አሁን የትሕነግ ኃይል በተቃራኒ ጎራ በጦርነት የተሰለፈ ጠላት ብቻ ሳይሆን በዓለምአቀፍ የጦር ሕግጋት ፍፁም የማይገዛ ፀረ-ሰው ኃይል ነው" ያለው የንቅናቄው መግለጫ "አሸባሪውን የትሕነግ ቡድን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው ተጋድሎ የጀግናው መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እንዲሁም የአማራ ሚሊሻና ፋኖ እያገደረጉት ባለው የማጥቃት እርምጃ እግሬ አውጭኝ ብሎ እየፈረጠጠ ይገኛል" ሆኖም ይህ "ኢ-ሰብአዊና የታሪክ አተላ ስብስብ በአማራ ሕዝብ ላይ እስካሁን ሲያደርስበት በነበረው ግፍ ባለመርካቱ ንፁሀን አማራዊ ወገኖቻችንን ዛሬም በጅምላ መጨፈጨፉን ቀጥሏል" ሲል አብራርቷል። ትሕነግ በማያቋርጥ ሽሽትና ሽንፈት ውስጥ እንኳ ሆኖ ፊት ለፊት ሊገጥመው ያልቻለውን ሕዝብ ወገን ናቸው የሚላቸውን አማሮች በመለየት የዘር ፍጅት እንደሚገኝ ሊታወቅ ይገባል ያለው ንቅናቄው በመንግስት በኩል በትሕነግ ኃይል ላይ የተከፈተውን አገራዊ ጦርነት በፍጥነትና በተሟላ ስኬት ለማጠናቀቅ ከሚደረገው የማጥቃት ስራ ጎን ለጎን በጁንታው ኃይል ታግተው የሚገኙ ንፁሀንን መታደግ ይገባል ብሏል። በተጨማሪ በዚህ ሂደት በትሕነግ ኃይል እየተፈፀሙ ያሉትን ባጠቃላይ በስብዕና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በልዩ ሁኔታ ደግሞ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙትን የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን በተመለከተ የተጠናከሩ ማስረጃ የማሰባሰብ ስራዎች በፍጥነት እንዲካሄዱ የጠየቀው አብን የትሕነግ ኃይል ከተደመሰሰ በኋላ በየአካባቢዎቹ የቀሩና በሰፊው ያስታጠቃቸውን ኃይሎች በአስቸኳይ ትጥቅ የማስፈታት ስራ እንዲሰራም አሳሰቧል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን